ሪፖርት | ሀዋሳ ከተማ ከተማ ከአርባምንጭ ከተማ ነጥብ ተጋርተዋል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 13ኛ ሳምንት ጨዋታ ሀዋሳ ከተማ አርባምንጭ ከተማን አስተናገዶ 1-1 በማጠናቀቅ በተከታታይ ለ3ኛ ጊዜ በሜዳው ነጥብ ተጋርቶ ወጥቷል፡፡

በሁለቱም ክለቦች በርከት ያሉ ደጋፊዎች በተገኙበት ጨዋታ ሀዋሳ ከተማ ኢትዮ ኤሌትሪክን ከገጠመበት የ11ኛ ሳምንት የመጀመርያ አሰላለፍ ሄኖክ ድልቢን በአዲስአለም ተስፋዬ ፣ በቀይ ካርድ የሶስት ጨዋታ ቅጣት የተጣለበት ፍሬው ሰለሞንን ከቅጣት በተመለሰው ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀን ዳዊት ፍቃዱን በእስራኤል እሸቱ ሲተካ በአንፃሩ አርባምንጮች አዳማ ከተማን በሜዳቸው ከረቱበት ስብስብ አስጨናቂ ፀጋዬን ከቅጣት በተመለሰው ምንተስኖት አበራ ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል፡፡

በልዩ የዳኝነት ብቃት በፌዴራል ዳኛ ዳንኤል ግርማይ በተመራው ጨዋታ በሁለቱም ክፍለ ጊዜ የሀዋሳ ከተማ ፍፁም የበላይነት ፣ የአርባምንጭ ከተማ ኃይል የተቀላቀለበት የመከላከል አቀራረብ ፣ የሙሉዓለም ረጋሳን ብስለት የተሞላበት እንቅስቃሴ ፣ ፅዮን መርዕድ በርካታ የግብ እድሎችን በማምከን ኮከብ ሆኖ የዋለበት ፣ በርከት ያሉ የዳኝነት ውሳኔን ያለመቀበል ችግሮች እና በስተመጨረሻም በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ላይ ደጋፊው ተቃውሞን ማሰማት የጨዋታው አጠቃላይ ገፅታ ነበር፡፡

ጨዋታው ከተጀመረበት ደቂቃ አንስቶ በአርባምንጭ የሜዳ አጋማሽ ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴን ሲያደርጉ የነበሩት ሀዋሳዎች ገና በ5ኛው ደቂቃ ላይ አዲስ አለም ተስፋዬ በአዞዎቹ የግራ የግቡ ጠርዝ አመቻችቶ የሰጠውን ኳስ ታፈሰ ሰለሞን ወደ ላይ የሰደዳት የመጀመርያዋ ሙከራ ነበረች፡፡ 10ኛው ደቂቃ ላይም የአርባምንጭን የተከላካይ ስፍራ ሲረብሽ የዋለው እና ከጉዳት የተመለሰው ወጣቱ አጥቂ እስራኤል እሸቱ ያቀበለውን ኳስ ታፈሰ ሰለሞን በድጋሚ ሳይጠቀምባት ቀርቷል፡፡ ከአንድ ደቂቃ በኃላ በ11ኛው ደቂቃ እስራኤል እሸቱ ከቀኝ መስመር ወደ ግቡ የላካትን ኳስ ከሶስት ጨዋታ ቅጣት በኃላ ወደ ጨዋታ የተመለሰው ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀን በግንባሩ በመግጨት አስቆጥሮ ሀዋሳዎችን ቀዳሚ አድርጓል፡፡

ከግቧ በኃላ ይበልጥ ተጭነው የተጫወቱት ሀዋሳዎች በተደጋጋሚ በአርባምንጭ የግብ ክልል ላይ አጋድለው ሲጫወቱ ቢታዩም የግብ ልዩነታቸውን ሊያሰፉባቸው የሚችሉባቸው የጎል እድሎች መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ አርባምንጭ ከተማ በኩል በአንፃሩ ገና ጨዋታው ሳይጋመስ በተለይ ምንተስኖት አበራ አማኑኤል ጎበናና በረከት ቦጋለ ሲፈፅሙ በነበረው አደገኛ አጨዋወት በደጋፊው ዘንድ ተቃውሞን አስከትሎባቸዋል፡፡

የአጥቂ መስመሩ የሳሳው አርባምንጭ ከተማ ባልተለመደ መልኩ ያለፉትን ሁለት ጨዋታዎች ከተከላካይ ስፍራ በማንሳት በአጥቂ ስፍራ ላይ ያሰለፈው ተመስገን ካስትሮ በግሉ በሚያደርገው ጥረት እና ከእንዳለ ከበደ በሚሻገሩለት ኳሶች የሀዋሳን የተከላካይ ክፍል ሲረብሽ ታይቷል፡፡ በ32ኛው ደቂቃ ላይም አዲስአለም ተስፋዬ ኳሷን ወደ አርባምንጭ የግብ ክልል ሊልካት ሲል በማጠሯ እንዳለ ከበደ አግኝቶ ከቀኝ መስመር ያሻገረለትን ኳስ ተመስገን ካስትሮ በአግባቡ በመጠቀም አርባምንጭ ከተማን አቻ ያደረገች ግብ ከመረብ አሳርፏል።

የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ 1 ደቂቃ ሲቀረው ፍቅረየሱስ ለታፈሰ ሰለሞን ያመቻቸለትን መልካም የግብ ማስቆጠር አጋጣሚ ታፈሰ ሳይረጋጋ መትቶ ያመከናት ኳስ ሀዋሳን በድጋሚ መሪ ልታደርግ የምትችል ነበረች፡፡

እምብዛም ሳቢ ባልነበረው ሁለተኛው አጋማሽ ክፍለ ጊዜ እንደ መጀመሪያው ሁሉ የሀዋሳ የበላይነት የታየበት ሲሆን አርባምንጭ ከተማ የአቻነት ውጤቱን ለማስጠበቅ የተከላካይ መስመሩን አጠናክሮ የገባበት ነበር፡፡

ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀን ያገኛትን መልካም አጋጣሚ ሳይጠቀም በቀረባት የግብ አጋጣሚ በጀመረው በዚህ አጋማሽ በ49ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ምት የተሸገረውን ኳስ እስራኤል እሸቱ ሞክሮ የግቡ ቋሚ የመለሰበት ፣ በ53ኛው ደቂቃ ላይ ከደስታ ዮሀንስ እና እስራኤል እሸቱ አንድ ሁለት ቅብብል ዮሀንስ ሱጌቦ ከግብ ጠባቂው ፅዮን መርዕድ ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ግብ ጠባቂው ያወጣበት እንዲሁም በ59ኛው ደቂቃ ላይ ደስታ ዮሀንስ ለ እስራኤል እሸቱ በጥሩ መልኩ አሾልኮ የሰጠውን ኳስ እስራኤል ሞክሮ ፅዮን በግሩም ሁኔታ ያወጣበት ኳስ ሀዋሳ ከተማ ለነበረው የበላይነት ማሳያ ነበሩ፡፡

በመጨረሻዎቹ 15 ደቂቃዎች አርባምንጮች አንዷን ነጥብ የፈለጉ በሚመስል መልኩ በጥልቀት አፈግፍገው የተጫወቱ ሲሆን ሀዋሳ ከተማዎችም እንደፈጠሩት ጫና ጠንካራ የግብ አጋጣሚ ሳይፈጥሩ ጨዋታው 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ በአምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ከድል የራቀው ሀዋሳ ከተማ ደጋፊዎች በአሰልጣኝ ውበቱ ደስተኛ አለመሆናቸውን የሚገልፅ ተቃውሞም አሰምተዋል፡፡

የአሰልጣኞች አስተያየት

ውበቱ አባተ- ሀዋሳ ከተማ

“ጨዋታው ከወትሮው ጊዜ የተለየ አይደለም፡፡ አጥቅተን ብንጫወትም እንዳለመታደል ሆኖ ግብ ማስቆጠር ላይ ክፍተት አለ፡፡ ግብ ካላስቆጠርክ ደግሞ ከተጋጣሚህ በመብለጥህ ብቻ ማሸነፍ አትችልም፡፡ ሜዳ ላይ የምናሳየው እንቅስቃሴ ጥሩ ነው፡፡ በቡድኑ የማንም ችግር የለም ፤ ኳስና መረብን የሚያገናኝ ሰው ነው የጠፋው፡፡ ዛሬ ዮሀንስ ፣ ታፈሰ እና እስራኤል ያገኙትን ኳስ ከጉጉት አንፃር አምክነውታል ብዬ አስባለሁ፡፡

ከውጤት መጥፋት ጋር ጫና አይኖርብኝም፡፡ እንደ አሰልጣኝ የወረደ አቋም ቢያሳይ ጫና ይኖርብኝ ነበር፡፡ በታዳጊ እየተጫወትን ጫና የሚባል አያሳስበኝም፡፡ ሀዋሳ የሚያደርገውን ማንም ቡድን የማያደርገው ነው ታዳጊ ላይ አምኖ ማጫወት፡፡ በቀጣይ ግን ያሉትን ክፍተት ላይ ሰርተን መገኘት ያስፈልገናል፡፡ የተጎዱም ሲመለሱ የተሻለ ነገር ባሉት ላይ ተጨምሮ ይሰራል፡፡ አንዳንዱ ክለቡን የሚደግፍ አለ ፣ አንዳንድ ያልተገቡ ደጋፊዎች ደግሞ አሉ፡፡ ቢታገሱ የተሻለ ነው፡፡ በትንሽ ወጪ የተሰበሰቡ ታዳጊዎች ናቸው፡፡ ቢያበረታቱ ይሻላል፡፡ እኔም ትልቅ ልምድ ያለኝ አሰልጣኝ ነኝ፡፡ ትልቅ ውጥረት ባለበት ቦታ አሰልጥኜ አልፌያለሁ፡፡ ዛሬም የተለየ ነገር የለውም፡፡ ደጋፊውም ያን ቢረዳ ደስ ይለኛል፡፡

እዮብ ማለ- አርባምንጭ ከተማ

ጨዋታው ደርቢ ነው ፤ ከባድ ነው፡፡ ግብ ገና በጊዜ ስተቆጠረብን ያንን ለማስጠበቅ ሳይሆን መልሰን ለማስቆጠር ነው የተንቀሳቀስነው፡፡ በኳስ ቁጥጥር በልጠውናል ፤ እኛ ደግሞ በመልሶ ለማጥቃት ሙከራ አድርገናል፡፡ በሁለት ጨዋታ በተረከብኩ 15 ቀን ውስጥ 4 ነጥብ ይዘናል፡፡ ከሜዳ ውጭ መጥፎ ሪከርድ አለብን፡፡ በሜዳችንም ከሜዳው ውጭ የተሻለ ለመሆን እንጥራለን፡፡ ዛሬ መከላከል ላይ ትኩረት ያደረግነው አንድ ነጥብ ለማግኘት ነበር፡፡

በሜዳችንም የተሸናፊነትን መንፈስ አጥፍተን በቀጣይ ለድሬዳዋው ጨዋታ እንቀርባለን፡፡ በእርግጠኝነት ባለው ነገር ታግለን ሙሉ ለሙሉ ከወራጅ ቀጠናው እንወጣለን፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *