ሪፖርት | ኢትዮጵያ ቡና ከሜዳው ውጪ የመጀመርያ ድሉን አስመዝግቧል

የኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ 13ኛ ሳምንት ጨዋታ ዛሬ ሲጀምር ወደ ድሬዳዋ ያመራው ኢትዮዽያ ቡና ድሬዳዋ ከተማን 2-0 በማሸነፍ ከአዲስ አበባ ውጪ የመጀመርያ ድሉን አስመዝግቧል።

በሁለተኛው ሳምንት ጅማ አባጅፋርን ከረታበት ጨዋታ ውጪ በሦስት ጨዋታ ሽንፈትን አስተናግዶ በስድስት ጨዋታዎች የአቻ ውጤት ያስመዘገበ ብቸኛ የሊጉ ቡድን የሆነው ድሬዳዋ በዘንድሮ አመት ካወጣው ከፍተኛ ሂሳብ በተቃራኒ በደካማ አቋም ወራጅ ቀጠና ውስጥ እንደመገኘቱ የዛሬውን ጨዋታ ማሸነፍ እጅግ ወሳኝ ነበር። በተመሳሳይ በ8ኛው ሳምንት ወልዲያን ከረቱበት ጨዋታ መልስ ካደረጉት ሦስት ተከታታይ ጨዋታ ማግኘት ከሚገባቸው ዘጠኝ ነጥቦች አንድ ብቻ በማሳካት በውጤት ቀውስ ውስጥ የሚገኙት ኢትዮጵያ ቡናዎች ወደ ድል ለመመለስ የሚያደረጉት ጨዋታ በመሆኑ የዛሬው ጨዋታውን ተጠባቂ አድርጎታል።

ፌደራል ዳኛ ማኑሄ ወ/ፃድቅ በመሩት ጨዋታ ገና በተጀመረ በ4ኛው ደቂቃ ሞገስ አስናቀ ከርቀት ወደ ድሬደዋ የግብ ክልል ያሻገረውን በረከት ሳሙኤል ኳሱን ለመራቅ ሲሞክር ሸርፎ ወደ ራሱ ግብ ክልል መቶት ጀማል ጣሰው እና የግቡ አግዳሚ በመለሰው ሙከራ የመጀመርያው ሙከራ ነበር። በ16ኛው ደቂቃ ላይ ጀማል ጣሰው ከጨዋታ ወረጪ በሚል የተሰጠውን ኳስ በፍጥነት ለማስጀመር ሲመታ ሳኑሚ ተደርቦ ያገኘውን ኳስ ወደ ግብነት ቢለውጥም ጎሉ ሳይፀድቅ በመቅረቱ ውዝግብ አስነስቶ ነበር።

ከዚህ ክስተት በኋላ በመጀመርያው አጋማሽ የሚጠቀሰረ የጎል ሙከራ ያልታየ ሲሆን በሁለቱም ቡድኖች በኩል በመሀል ሜዳ ላይ የተገደበ እንቅስቃሴ የተመለከትንበት እና ኳስን በሚገባ ተቀብሎ በሚገባ የሚያሰራጭ ጠፍቶ የሚባክኑት ኳሶች የጨዋታው አሰልቺ ገፅታ ሆነው ታይተዋል። አሰልቺው የመጀመርያ አጋማሽም አንድ የጎል ሙከራ ብቻ አስመልክቶን ያለ ጎል ወደ እረፍት አምርቷል ።

በሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በአንፃራዊነት ከመጀመርያው አጋማሽ የተሻለ እንቅስቃሴ ያየንበት ሲሆን 48ኛው ደቂቃ ላይ ዳኛቸው በጥሩ መንገድ የሰጠውን ኳስ ተቀብሎ አትራም ከዋሜ በግራ እግሩ በጥሩ ሁኔታ የመታውን ግብጠባቂው ሀሪሰን በግል ብቃቱ ተጠቅሞ ያዳነው ኳስ ድሬዎችን መሪ የምታደርግ የምታስቆጭ አጋጣሚ ነበረች። በዚህ የጎል ሙከራ ያልቆሙት ድሬዎች 56ኛው ደቂቃ ላይ ከመዐዘን የተሻገረን ኳስ በረከት ሳሙኤል በግንባሩ ገጭቶ በድጋሚ ግብጠባቂው ሀሪሰን በሚገርም መንገድ ያዳነው ኳስ ሌላኛው ለባለ ሜዳዎቹ መልካም የሚባል የጎል አጋጣሚ ነበር ።

ድሬዎች ደቂቃዎች በገፉ ቁጥር ከጠንካራ እንቅስቃሴያቸው እየተዳከሙ ሲመጡ በአንፃሩ ቡናዎች በሚያገኙት አጋጣሚ ወደ ጎል በመድረስ ጫና ለመፍጠር የሚያደርጉት ጥረት ተሳክቶላቸው 65ኛው ደቂቃ ላይ ሳምሶን ጥላሁን ያሻገረለትን ኳስ ሳሙኤል ሳኑሚ ጉልበቱን ተጠቅሞ ከሁለት ተከላካዮች ጋር ታግሎ ኳሱን በማመቻቸት ጎል አስቆጥሮ ኢትዮዽያ ቡናን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።

ከዚህ ጎል መቆጠር በኋላ ኢትዮዽያ ቡናዎች ተነቃቅተው በመልሶ ማጥቃት የድሬደዋ ተከላካዮቹን ይረብሹ እንጂ ጠንካራ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም ነበር። ጎል የተቆጠረባቸው ድሬዎች ባልተደራጀ መንገድ ከተከላካዮች ወደ አጥቂዎች የሚጣሉ ኳሶች ለቡና ተከላካዮች ሲሳይ እየሆነ ተመልሶ በራሳቸው ላይ ጫና ቢፈጥርባቸውም ታይቷል። 85ኛው ደቂቀ ላይ ግን በአንድ ደቂቃ ልዩነት ሁለት የጎል አጋጣሚዎች አግኝተው ኩዋሜ አትራም ከ30ሜትር ርቀት የተገኘውን ቅጣት ምት መቶት ሀሪሰን በሚገርም ሁኔታ ወደ ውጭ ሲያወጣው ይሄው ኳስ የመአዘን ምት ተመቶ በረከት ሳሙኤል በግንባሩ ገጭቶ ለጥቂት በቋሚው በኩል የወጣው ድሬዎችን አቻ ማድረግ የሚችሉ የግብ ሙከራዎች ነበሩ።

መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ 90+2ኛው ደቂቃ ላይ ከ25ሜትር ርቀት አማኑኤል ዮሐንስ አንተነህ ተስፋዬን በእግራ እግሩ ኳሱን አሳልፎ በቀኝ እግሩ በቮሊ ያስቆጠረው አስደናቂ ጎል የኢትዮዽያ ቡናን አሸናፊነት ሲያረጋግጥ በአንፃሩ የድሬዎችን ተጫዋቾችና ደጋፊዎችን ቅስም ሰብራለች። ጨዋታውም በዚሁ ውጤት በኢትዮዽያ ቡና 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ኢትዮዽያ ቡና በማሸነፉ ከአአ ረጅም ርቀት አቋርጠው የመጡት ደጋፊዎች በውጤቱ እጅግ ተደስተው ደስታቸውን የገለፁበት መንገድ አስገራሚ ነበር። ቡድናቸው በሚያስመዘግበው ውጤት ደስተኛ ያልሆኑን የድሬደዋ ከተማ ደጋፊዎች በክለቡ አጠቃላይ አመራር ላይ ጠንካራ ተቃውሞ ሲያሰሙ በሌላ መልኩ ደግሞ ደጋፊዎች የቀደመሰዋ የቡድኑ አሰልጣኝ መሰረት ማኒን ስም እያነሱ ሲያወድሱ ተመልክተናል።

ውጤቱን ተከትሎ ኢትዮዽያ ቡና ደረጃውን በማሻሻል ወደ ሰባተኛ ሲመጣ በተከታታይ ጨዋታዎች ነጥብ እየጣለ የሚገኘው ድሬደዋ ከተማ የቁልቁለት መንገዱን በመያዝ 15 ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

አሰልጣኞች አስተያየት

ድሬደዋ ከተማ – ስምዖን አባይ

እንዳያችሁት ጨዋታውን በእኛ ቡድን በኩል ከመቶው አስር ፐርሰንቱን እንኳ ሲጫወቱ አልተመለከትኩም። ከዚህ ቀደም ከነበረው አጨዋወት በጣም የወረደ አቋም ነው ያሳየነው። ኢትዮዽያ ቡና ያሸነፈው ከእኛ ተሽሎ አይደለም። እኛ ያደረግነው ምንም አይነት እንቅስቃሴ የለም ፤ ቡና ያሸነፈን ባላቸው ልምድ እና ብስለት ነው። ዛሬ ቡድናችን በጣም በጣም የወረደ አቋም ነበረው ። ለደጋፊ የሚገባው እንኳ ውጤት እንቅስቃሴ አይደለም። ለዛሬው ውጤትም ራሴን ተጠያቂ አደርጋለው በዚህም ይቅርታ እጠይቃለው ።

ኢትዮዽያ ቡና – ዲዲዬ ጎሜስ

ሲገቡ የነገርኳቸው ተጫዋቾቼን በወኔ እና በፍላጎት እንዲጫወቱ ነበር። ምክንያቱም ደጋፊው ባሳለፍናቸው ጨዋታዎች ውጤታችን ጥሩ ባለመሆኑ አዝኖ ነበር ። በዚህም በሚፈለገው መንገድ ቲኪ-ታካ ባንጫወትም ፣ በዛ ያሉ የጎል አጋጣሚዎች መፍጠር ባንችልም ያገኘነውን አጋጣሚ ተጠቅመን አሸነፈን መውጣታችን አስደስቶኛል። ከውጤቱ በላይ ያስደሰተኝ ረጅም ርቀት ተጉዘው የመጡ ደጋፊዎቻችን እንዲህ ሲደሰቱ ማየቴ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *