ቅዱስ ጊዮርጊስ ከካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ ውጪ ሆኗል

ዛሬ በስታር ታይምስ ስታድየም በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ የአንደኛ ዙር የመልስ ጨዋታውን ከዩጋንዳው ኬሲሲኤ ጋር ያደረገው ቅዱስ ጊዮርጊስ 1 – 0 በሆነ ውጤት መሸነፉን ተከትሎ ለሁለተኛ ተከታታይ አመት ወደ አፍሪካ ትልቁ ውድድር የምድብ ድልድል ውስጥ ለመካተት የነበረውን ዕድል አምክኗል።

ባሳለፍነው ረቡዕ በአዲስ አበባ ስታድየም ከተደረገው ጨዋታ በሁለቱም በኩል ለውጦች ታይተዋል። ኬሲሲዎች በመጀመሪያው ጨዋታ በተጠባባቂነት የተጠቀሙባቸውን መሀመድ ሻባንን እና ኦኮት ዴኒስን በጁሊየስ ፖሎቶ እና ኦቤንቻን በመተካት በመስመር ተከላካይ እና አማካይ ክፍላቸው ላይ ለውጥ አድርገዋል። በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ደግሞ የተደረገው ብቸኛ ቅያሪ በመስመር አጥቂ ቦታ ላይ ሲሆን ለውጡም ጋዲሳ መብራቴን በበኃይሉ አሰፋ የተካ ነበር።

ከሜዳቸው ውጪ በተደረገው ጨዋታ ግብ ሳይቆጠርባቸው የተመለሱት ኬሲሲዎች እንደተጠበቀው ሁሉ አጥቅተው ለመጫወት የሞከሩበትን የመጀመሪያ አጋማሽ አሳልፈዋል። የመጀመሪያውን ዕድልም መሀመድ ሻባን ከሙኩሩዚ የተሻገረለትን ኳስ ለመጠቀም ሞክሮ ከሮበርት ኦዱንካራ ጋር ሲጋጭ የታየ ነበር። 30ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ዴሪክ ኒስንባቢ እና አለን ኦኬሎ ከከፈቱት ጥቃት ሙዛሚሩ ሙታያባ ከሳጥን ጠርዝ ላይ ያደረገውን ጥሩ ሙከራ ኦዱንካራ ሲያድንበት ከደቂቃዎች በኃላ አለን ኦኬሎ የሙስጠፋ ኪዛንን ተሻጋሪ ኳስ ተጠቅሞ የሞከረው የግንባር ኳስ ግን ጠንካራ ባለመሆኑ ኦዱንካራን ማለፍ ሳይችል ቀርቷል። ቅዱስ ጊዮርጊሶችም አማራ ማሌ የመሀል ተከላካዩ ቲሞቲ አዎኒን አልፎ ከጠባብ አንግል ሞክሮት ወደ ውጪ በወጣበት ኳስ ምላሽ ሰጥተዋል። ከሁሉም በላይ ግን ፈረሰኞቹ የግብ ክልላቸው አካባቢ የተሰጠውን ቅጣት ምት አለን ኦኬሎ ሲመታ ተደርበው በፈጣን መልሶ ማጥቃት ተጋጣሚያቸው የጎል ክልል ድረስ ሄደው ሳይጠቀሙበት የቀሩበት ሁኔታ የሚያስቆጭ ነበር።

ከዕረፍት መልስ ኬሲሲዎች በሁለት ደቂቃ ልዩነት ወደ ቻምፒዮንስ ሊጉ የምድብ ድልድል እንዲያመሩ ምክንያት የሆነችውን ብቸኛ ግብ ከሻባን መሀመድ አግኝተዋል። በዚሁ ደቂቃ የማዕዘን ምት ያገኙት ባለሜዳዎቹ የማዕዘን ምቱን በአጭሩ ከጀመሩት በኃላ ሙስጠፋ ኪዛ በጥሩ ሁኔታ ወደ ጊዮርጊስ ሳጥን ሲጥልለት ነበር ሻባን በግንባሩ በመግጨት ከመረብ ያዋሀደው። ግቡ ሲቆጠር የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጨዋቾች የነበራቸው ቦታ አያያዝ የቆመ ኳስን የሚከላከሉበትን መንገድ በእጅጉ ጥያቄ ውስጥ የከተተ ነበር። በተቀሩት ደቂቃዎች ቅዱስ ጊዮርጊሶች ጨዋታውን ተቆጣጥረው ለመጫወት በመሞከር የተንቀሳቀሱ ሲሆን ጋዲሳ መብራቴን እና አዳነ ግርማን ቀይረው በማስገባትም ጫና ለመፍጠር ሲጥሩ ታይተዋል። ሆኖም አበባው ቡታቆ ካደረገው ሙከራ ሌላ የኬሲሲኤን ጠንካራ የተከላካይ ክፍል አልፎ የግብ ዕድል መፍጠርም ሆነ አቻ መሆን አልቻሉም። ጨዋታውም በመሀመድ ሻባን ብቸኛ ግብ ልዩነት ፈጣሪነት ሲጠናቀቅ ኬሲሲኤ በታላቁ የአፍሪካ የክለቦች ውድድር መድረክ የምድብ ድልድል ውስጥ በመካተት የመጀመሪያው ዩጋንዳዊ ክለብ መሆን ችሏል። ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ በሳምንቱ አጋማሽ በካይሮ በሚደረገው የዕጣ ማውጣት ስነስርዐት ተጋጣሚውን አውቆ በኮንፌዴሬሽኑ የምድብ ድልድል ውስጥ ለመካተት የሚፋለም ይሆናል።

የአሰልጣኞች አስተያየት

ማይክ ሙቴዬቢ – ኬሲሲኤ

ወደ ምድብ ድልድሉ መግባት ለኬሲሲኤ ትልቅ ስኬት ነው። ከትልልቆቹ የአፍሪካ ቡድኖች ጋር ትከሻ ለትከሻ ለመፎካከር ዕድል ማግኘታችን በራሱ ትልቅ ነገር ሲሆን ይህን ያደረግነው ደግሞ በወጣት ተጨዋቾች መሆኑ የውጤቱን ዋጋ ከፍ ያደርገዋል።

ቫስ ፒንቶ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

እኛ ከኬሲሲኤ የተሻልን ነበርን። የተሻሉ የሚባሉ የግብ ዕድሎችንም ፈጥረናል። ሆኖም እኛ ዕድሎቻችንን መጠቀም አልቻልንም ኬሲሲዎች ግን ያን አድርገዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *