ሪፖርት | የሐብታሙ ብቸኛ ጎል ድሬዳዋን ወሳኝ ሦስት ነጥብ አስጨብጣለች

23ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ በአዲስ አበባ እና በክልል ሜዳዎች ሲካሄድ ድሬዳዋ ላይ መከላከያን ያስተናገደው ድሬዳዋ ከተማ 1-0 በማሸነፍ ከወራጅ ቀጠናው ከሚገኙ ቡድኖች ነጥቡን ከፍ ያደረገበትን ውጤት አስመዝግቧል፡፡

ድሬዳዋ ከተማ በሜዳው በተስተካካይ ጨዋታ ወላይታ ድቻን ካሸነፈበት ስብስቡ በጉዳት ምክንያት ዘነበ ከበደ እና ያሬድ ታደሰን በማጣቱ በምትካቸው አህመድ ረሺድ እና ዘላለም ኢሳያስን ይዞ ወደ ሜዳ ገብቷል፡፡  መከላከያ በበኩሉ በ22ኛው ሳምንት በአዲስ አበባ ስታድየም ከወልዋሎ ከተደረገው ጨዋታ ስብስቡ ምንተስኖት ከበደ እና በኃይሉ ግርማን አሳርፎ ሙሉቀን ደሳለኝ እና አማኑኤል ተሾመን የመጀመሪያ ተሰላፊነት ቅድሚያን ሰጥቷል፡፡

ኢ/ዳኛ ዳዊት አሳምነው በመሩት የሁለቱ ቡድኖች ፍልሚያ በመጀመርያው የጨዋታ 10 ደቂቃዎች እንግዶቹ መከላከያዎች በመሀል ሜዳ ላይ ኳሱን በሚገባ ተቆጣጥረው በመጫወት ከባለሜዳዎቹ ድሬዎች የተሻሉ እንደነበሩ አመላካች እንቅስቃሴ በማድረግ ጎል ማስቆጠር የሚችሉበትን አጋጣሚ በ6ኛው ደቂቃ ላይ መፍጠር ችለውም ነበር ። በቀኝ መስመር የሳጥኑ ጠርዝ ላይ  በአንድ ሁለት ቅብብል የገባው ሙሉቀን ደሳለኝ በጥሩ አቋቋም ላይ ለሚገኘው ዳዊት እስጢፋኖስ የላከለትን የተመጠነ ኳስ በፍ/ቅ/ምት መምቻው ላይ የነበረው የመከላከያው የአጥቂ አማካይ ኳሱን ተቆጣጥሮ ወደ ጎል ቢልከውም አጠንክሮ ያልመታው በመሆኑ የድሬው ግብ ጠባቂ ሳምሶን አሰፋ በጥሩ ሁኔታ ሊያወጣበት ችሏል፡፡ ቀይ እና አረንጓዴ ለባሾቹ ይህን የጎል ሙከራ ካደረጉ በኋላ በሁሉም ተጫዋቾች ዘንድ የታየው ግላዊም ሆነ የቡድን እንቅስቃሴ በሒደት የመውረድ አዝማሚያን አሳይቷል፡፡ በአንፃሩ ባለሜዳዎቹ ድሬዎች ወደ ጨዋታው ሪትም በመግባት የበላይነት ለማሳየትና ኳስ ለመቆጣጠር የሚያስችላቸውን እንቅስቃሴ ማድረግ ከመቻላቸውም በላይ በ11ኛው ደቂቃ ላይ ሱራፌል ዳንኤል ከቀኝ መስመር በጥሩ ሁኔታ ያሻገረለትን ዮሴፍ ዳሙዬ ኳሱ አየር ላይ እያለ በግራ እግሩ አክርሮ ቢመታውም የግቡን አግዳሚ ታኮ ሊወጣ ችሏል።

በከፍተኛ ደረጃ እየተነቃቁ የሄዱት ድሬዎች ኢላማውን የጠበቀ ባይሆንም እንኳ 12ኛው ደቂቃ ላይም ተጨማሪ ለጎል የቀረበ ሙከራ በኩዋሜ አትራም አማካኝነት ሊያደርጉ ችለዋል፡፡ ተጫዋቹ በጥሩ ሁኔታ ኳሷን  መቷት በግቡ አናት ላይ ወጥታበታለች ። የመከላከያ ቡድን አራቱም ተከላካዮች ባልተደራጀ ሁኔታ ከመከላከላቸውም በላይ በተደጋጋሚ በሚሰሩት ስህተት የግብ ክልላቸውን በቀላሉ ተጋላጭ  በማድረግ ተጋጣሚያቸው የበለጠ ክፍተት እንዲያገኝ አድርገዋል፡፡ በ13ኛው ደቂቃም ሱራፌል ዳንኤል ከቀኝ መስመር ላይ በመከላከያ የጎል ክልል ይገኝ ለነበረው ክዋሜ አትራም ጥሩ ኳስ አቀብሎ አጥቂው የሞከረውን ጠንከር ያለ ምት በመከላከያ ተከላካዮች ተደርቦ የተመለሰውን ኳስ ሀብታሙ ወልዴ አግኝቶ መሬት ለመሬት በመምታት ለድሬደዋ ከተማ ወሳኟን ጎል አስቆጥሯል።

በዚህችጎል መቆጠር የተበረታቱት ድሬዎች እስከ 20 ኛው ደቂቃ ድረስ ሌላ አደገኛ የጎል አጋጣሚ ባይፈጥሩም ኳስን በመቆጣጠር እና ስነ ልቦናዊ የበላይነት በማሳየት ረገድ የተሻሉ ሆነው ለመታየት ችለዋል፡፡ ይህም የጨዋታው ክፍለ ጊዜ እየገፋ በሄደ ቁጥር እየተዳከሙ የነበሩትን መከላከያዎች መብለጥ አስችሏቸዋል። በ20ኛው ደቂቃ አካባቢ በሳጥኑ አቅራቢያ ከቀኙ ክፍል አትራም ኩዋሜ ለሀብታሙ ወልዴ ጥሩ ቅብብል አድርጎለት አጥቂው ጎል ቢያስቆጥርም  በካታንጋ በኩል በሚገኘው መስመር ጨዋታውን የመሩት ፌ/ዳኛ ቦጋለ አበራ ጎሉ ከመቆጠሩ በፊት ሀብታሙ ወልዴ ከጨዋታ ውጭ አቋቋም ላይ ነበር በሚል ምልክት በማሳየታቸው ጎሉ ሳይፀድቅ ቀርቷል። የእንግዳው ቡድን የመከላከል ድክመት እንዳለ ሆኖ የድሬ አጥቂዎች ተረጋግተውና እራሳቸውን ከጨዋታ ውጭ አቋቋም ነፃ አድርገው በረጅሙ የሚላክላቸውን ኳስ ለመጠቀም አለመቻላቸው ሌሎች ጎሎችን እንዳያስቆጥሩ አድርጓቸዋል። በአመዛኙ በመሀል ሜዳ ላይ በተገደበ እንቅስቃሴ የቀጠለው የመጀመሪያው አጋማሽ ከላይ ከተጠቀሱት የጎል ሙከራዎች ውጪ ሌሎች የተሻሉ አጋጣሚዎች ሳይታይበት  በድሬዳዋ 1 – 0 መሪነት ቡድኖቹ ወደ እረፍት አምርተዋል።

ከእረፍት መልስ ድሬዎች በጉዳት ምክንያት እያነከሰ ይጫወት የነበረው አጥቂው አትራም ኩዋሜን በበረከት ይስሐቅ ቀይረው ወደ ሜዳ ሲመለሱ ጨዋታው እንደተጀመረ ባልተጠበቀ ሁኔታ የመከላከያ ተከላካዮችን ትኩረት ማጣት ተከትሎ ሐብታሙ ወልዴ ከጎሉ ፊት ለፊት ነፃ ኳስ አግኝቶ አገባው ሲባል የግቡን ቋሚ ታኮ የወጣው እና በ52ኛው ደቂቃ ላይ የመከላከያው ግብ ጠባቂ ይድነቃቸው ኪዳኔ ኳሱን መስርቶ ለማስጀመር በማሰብ ለተከላካዩ አወል አብደላ አቀብሎት አወል ኳሱን የሚቀበለው ሲያጣ ለራሱ ለይድነቃቸው ሲመልስ ኳሱ በማጠሩ ምክንያት ሐብታሙ ወልዴ በፍጥነት ኳሱን ተቆጣጥሮ ግብ ጠባቂውን ለማለፈረ ሲሞክር ይድነቃቸው እንደምንም ተስቦ የያዘበት በአራት ደቂቃዎች ውስጥ ባለሜዳዎቹ ድሬዎች የጎል መጠናቸውን ከፍ ማድረግ የሚችሉበት የሚያስቆጩ አጋጣሚዎች ነበሩ። አወል አብደላም ከስህተቱ በኋላ ወድያውኑ በምንተስኖት ከበደ ተቀይሮ  አስወጥተውታል።

መከላከያዎች ሙሉቀን ደሳለኝን በማራኪ ወርቁ ፣ ዳዊት እስጢፋኖስን በአቤል ከበደ በመቀየር ወደ ጨዋታው ለመመለስ ከድሬዎች በተሻለ ቢንቀሳቀሱም በአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ጎል በመድረስ ከሚያደርጉት የማጥቃት መንገድ ይልቅ  በረጃጅም ኳሶች ለፍፁም ገ/ማርያም እና ለምንይሉ ወንድሙ ይጣሉ የነበሩ ኳሶች በድሬዳዋ ተከላካዮች እየተመለሰ በራሳቸው ላይ አደጋ ሲፈጥሩ ተስተውሏል። በተለይ በረከት ይስሀቅ ፣ ሐብታሙ ወልዴ  እና ዮሴፍ ዳሞዬ ወደ መስመሩ አስፍተው ራሳቸውን ከተከላካዮች ነፃ በማድረግ የሚቀበሉትን ኳስ ወደ ፊት በመሄድ ሲያሻግሩ በአግባቡ በመቀበል ጎል የሚያስቆጥር ተጫዋች አለመኖሩ ተጨማሪ ጎሎችን እንዳያስቆጥሩ አድርጓቸዋል።

ጨዋታው ወደ መጠናቀቂያው ላይ ሲቃረብ ውጤት ለማስጠበቅ መከላከልን ምርጫቸው ያደረጉት ድሬዎች ጫና ውስጥ ገብተው የነበረ ቢሆንም የመከላከያ የማጥቃት እንቅስቃሴ ደካማ በመሆኑ ብዙም የረባ ሙከራ ሳይደረግባቸው ወጥተዋል። ሆኖም 90 ደቂቃው ተጠናቆ 4 ደቂቃ ጭማሪ በታየበት አጋጣሚ ከቀኝ መስመር ቴዎድሮስ ታፈሰ ወደ ሳጥን ያሻገረውን ኳስ ፍፁም ገ/ማርያም ተንሸራቶ ጎል ቢያስቆጥርም ረዳት ዳኛው ቦጋለ አበራ ከጨዋታ ውጭ ነው ብለው ሳይፀድቅ ቀርቷል። የመከላከያ ተጨዋቾችም በውሳኔው ላይ በተገቢ መልኩ ቅሬታ ሲያሰሙ ተስተውሏል። ጨዋታውም በድሬዳዋ አሸናፊነት ተጠናቋል።

* በጨዋታው ዳዊት እስጢፋኖስ ከተመልካች ያልተገቡ ዘለፋዎች ሲያስተናግድ የታየ ሲሆን ተጫዋቹ ወደ መልበሻ ክፍል በሚያመራበት ወቅትም በጣቱ ያልተገባ ምልክት በማሳየት አፀፋዊ ምላሽ ሲሰጥ ታይቷል። ከተመልካች የሚሰነዘረው ስድብ በሁለተኛው አጋማሽም የቀጠለ ሲሆን ተጫዋቹ ወደ አላስፈላጊ ነገር እንዳይገባ በማሰብም የጨዋታው ዋና ዳኛ ዳዊት አሳምነው እየጠሩ ሲመክሩት ተሰተውሏል። ተመልካቹ ከስፖርታዊ መርህ በወጣ መልኩ ስሙን እየጠሩ ሲሳደቡ እና ተጫዋቹም አፀፋ ለመስጠት ሲሞክር መታየታቸው ሊታረም የሚገባው ድርጊት ነው።
ውጤቱን ተከትሎ ድሬዳዋ ከተማ የደረጃ ለውጥ ባያስመዘግብም ነጥቡን 25 አድርሶ 12ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ መከላከያም በተመሳሳይ የደረጃ ለውጥ ሳያስመዘግብ በ28 ነጥብ 9ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

የአሰልጣኞች አስተያየት

ስምዖን ዓባይ – ድሬዳዋ ከተማ

በመጀመርያ ከጨዋታው ፈልገን የገባነው ትልቅ ነገር ሦስት ነጥብ ለማግኘት ነበር። የመጀመርያው አርባ አምስት ጫና በመፍጠር ኳሱን ተቆጣጥረን የጎል ሙከራ አድርገን ጎልም አስቆጥረን ወጥተናል። በሁለተኛው አጋማሽ ቡድናችን ላይ አንዳንድ ስሜታዊ ነገሮች ይታዩ ነበር ፤ በዚህም ተበልጠን ነበር። በአጋጣሚ የምናገኛቸው የግብ አጋጣሚዎችን አለመጠቀማችን መጨረሻ ላይ ዋጋ ሊያስከፍለን የሚችል ነበር። ቢሆንም ግን አቅደን ይዘን የገባነው ለሦስት ነጥብ ስለነበር ይህን እናሳካ እንጂ አጨዋወታችን ላይ መስተካከል ያለበት ነገር አለ።

ስዩም ከበደ – መከላከያ

በአጠቃላይ ጨዋታው ጥሩ ነበር። ለሁለታችንም ወሳኝ ጨዋታ ነበር። የመጀመረወያውን 15 ደቂቃ ብልጫ ወስደን ጨዋታውን ተቆጣጥረን ስለነበረ የተሻለ ነገር እናደርጋለን ብዬ ተስፋ ነበረኝ ። ራሳችን በሰራነው ስህተት ተጠቅመው ጎል ካስቆጠሩብን በኋላ የጨዋታው መልክ ተቀይሯል። እንደነዚህ ያሉ አጋጣሚዎች በተጨዋቾች ላይ የሚያሳድረው ስነልቦና ጫና ቀላል አይደለም ። ከእረፍት መልስ አንዳንድ ነገር ለማስተካከል ሞክረናል። የበለጠ ጫና ለመፍጠር አጥቂዎች በመጨመር የታክቲክ ለውጥ አድርገናል። ድሬዳዋ ጥሩ ነጥብ አሳክቷል ብዬ አስባለው ።