ሪፖርት | መቐለ ከተማ ሀዋሳን በማሸነፍ ሊጉን መምራት ጀምሯል

በ24ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በሜዳው ትግራይ ስታድየም ሀዋሳ ከተማን ያስተናገደው መቐለ ከተማ በፉሴይኒ ኑሁ ብቸኛ ጎል 1-0 በማሸነፍ የሊጉን የመሪነት መንበር ከጅማ አባጅፋር ተረክቧል።

መቐለ ከተማ ባሳለፍነው ዓርብ በቀሪ 45 ደቂቃ ጨዋታ ከተቀመው ቡድን መካከል ቶክ ጀምስ እና ካርሎስ ዳምጠው እንዲሁም በቅጣት ያጡት አመለ ሚልኪያስ ምትክ ሐብታሙ ተከስተ፣ ጋቶች ፓኖም እና አሌክስ ተሰማ ሲካተቱ በሀዋራ ከተማ በኩል በ23ኛ ሳምንት ፋሲል ከተማን ካሸነፈው ስብስብ መካከል በእስራኤል እሸቱ ምትክ ያቡን ዊልያምን በማስገባት ጨዋተመውን ጀምሯል። (ያቡን በጨዋታው የቆየው ለ6 ደቂቃዎች ብቻ ሲሆን በዳዊት ፍቃዱ ተተክቷል)

እንደተጠበቀው ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ድረስ ተመጣጣኝ ፉክክር በታየበት እና ሳቢ የኳስ ፍሰት በተስተዋለበት ጨዋታ በመጀመርያው አጋማሽ ባለሜዳዎቹ መቐለ ከተማዎች የተሻለ ብልጫ ነበራቸው። በመቐለ ከተማ በፈጣን ሁኔታ የማስጨነቅ እንቅስቃሴ ምክንያት ሀዋሳ ከተማዎች ከዚህ በፊት በሚታወቁበት ከግብ ጠባቂው ኳስን መስርተው መጫወት ካለመቻላቸው በተጨማሪ የሃዋሳ ከተማ ተከላካዮች እና አማካዮች በራሳቸው የሜዳ ክልል በተረጋጋ ሁኔታ እንዳይቀባበሉ ጊዜ እና ቦታ ሲያጡ ተሰተውሏል። በዚህ የተነሳ ተደጋጋሚ ቅብብሎቻቸው ሲበላሹ ተስተውሏል። በዚህም ምክንያት ከመቐለ ጫና ለማምለጥ በረጃጅሙ የሚህኳቸው ኳሶች በቀላሉ ሲጨናገፉ ታይቷል።

ወደ ተጋጣሚ ክልል በመድረስ የተሻሉ የነበሩት ባለሜዳዎቹ መቐለ ከተማዎች በያሬድ እና አማኑኤል ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ኣድርገው ነበር። በተለይም ያሬድ ከበደ ከሳጥኑ ጠርዝ አክርሮ የመታውና ሶሆሆ የመለሰበት ለግብ የቀረበች ሙከራ ነበረች። ከመጀመርያው ሙከራ ብዙም ሳይቆዬ አማኑኤል ገብረሚካኤል በተከላካዮች ትኩረት ማጣት ያገኛትን ኳስ ተጠቅሞ የመታትን ኳስ አምበሉ ደስታ ዮሃንስ እንደምንም አውጥቶታል። ባለፈው ሳምንት በቀይ ካርድ በወጣው አመለ ሚልክያስ ምትክ ወደ ተከላካይ አማካይ ተመልሶ የተጫወተው ጋቶች ጥሩ ሲንቀሳቀስ በፈጣን የመልሶ ማጥቃት የሜዳው ስፋት ተጠቅሞ ለሚያጠቃው መቐለ ከተማ ከዚ በፊት አጠረቶት የነበረው ከሳጥን ሳጥን አካሎ የመጫወት ብቃት በመመለስ ጥሩ የማጥቃት አማራጭ ሲፈጥር ተስተውሏል።

ጠንካራውን የመቐለ ተከላካይ መስመር አልፈው የጎል እድሎች ሀመፍጠር የተቸገሩት ሀዋሳ ከተማዎች ለጎል የቀረበ ሙከራ ለማረግ 19 ደቂቃዎች የፈጀባቸው ሲሆን ከቀኝ መስመር የተሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ ፍቅረየሱስ ቢመታም ኢላማው ሳይጠብቅ ወደ ውጪ ወጥቷል። መቐለ ከተማዎች በሁለቱም መስመር የሚሰነዝሯቸው ጥቃቶችን ለመከላከል በሚመስል መልኩ ሃዋሳዎች አማካይ መስመራቸው ወደ ቀኝ እና ግራ በመለጠጥ የመቐለን የመስመር ጥቃት ቢከላከሉም በአማካይ መስመራቸው መሃል ክፍተቶች ሲተው ተስተውልዋል። በዚህም የመቐለ አማካዬች ክፍተቱን ተጠቅመው ከሃዋሳ ሳጥን በቅርበት ቢጫወቱም ጥቃቱን በአግባቡ ሳይከውኑ፤ የመጨረሻ እድሎችንም ሳይፈጥሩ ቀርተዋል።

እንደወትሮው መሃል ሜዳ ላይ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ማሳካት ያልቻሉት ሀዋሳ ከተማዎች የጋቶች ፖኖም እና በጨዋታው ጥሩ የተንቀሳቀሰው ሐብታሙ ተከስተ ጥምረት አልፈው ሳጥን ውስጥ መገኘት የቻሉባቸው አጋጣሚዎች ጥቂት ነበሩ። በዚህ መሐል አቼምፖንግ አሞስ አሻምቶ ሚካኤል ደስታ በግንባሩ ገጭቶ ላውረንስ ላርቴ ያወጣበት ፤ አሌክስ ተሰማ በረጅሙ ያሸማውን ኑሁ ፉሴይኒ ሳያገኘው ቀርቶ ሶሆሆ የመለሰው ፤ ከቅጣት ምት ፉሴይኒ መትቶ ሶሆሆ በግሩም ሁኔታ የመልስበት እና ብዙም ሳይቆይ ተከላካዩ መሳይ የተሳሳተውን ኳስ ያሬድ ከበደ ቢመታም በድጋሚ በሶሆሆ የከሸፈው ሙከራ በመቐለ በኩል ፤ በሃዋሳ በኩል ደግሞ አዲስዓለም በግሩም ሁኔታ የመታው ኳስ ሶፈንያስ ሰይፈ ሲተፋው ተከላካዮች ተደርበው ያወጡት ኳሰ የሚጠቀስ ነው።

በመጀመርያ አጋማሽ የመጨረሻ ደቂቃዎች መቐለ ከተማዎች መጠነኛ መቀዛቀዝ ሲያሳዩ ሀዋሳ ከተማዎች በመሃል ሜዳ ያመዘነ በርካታ ንክኪዎች ቢያደርጉም በመጨረሻ ደቂቃ ላይ ፍሬው ሰለሞን ያሻማውን ደስታ የውሃንስ ሞክሮ ለጥቂት ወደ ላይ ከወጣችው ኳስ ውጪ ተጨማሪ የግብ እድሎች ሳይፈጠሩ የመጀመርያው አጋማሽ ተገባዷል።

በእረፍት ሰአት ላይ ኢትዮጵያ አሸናፊ በነበረችበት 3ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ አባል የነበሩት የቀድሞ የታይድል እግር ኳስ ክለብ ተጫዋች እና አሰልጣኝ አስመላሽ አለማዬ በመቐለ ከተማ ክለብ የ20 ሺ ብር እና የ እውቅና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ሙሉ ክፍለ ጊዜ በሚባል መልኩ በእንግዶቹ ሀዋሳ ከተማዎች የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ሲቀጥል በሁለቱም ቡድኖች በኩል ከመጀመርያው አጋማሽ ያነስ ሙከራ ተስተውሏል። በ47ኛው ደቂቃ ላይ በቀኝ መስመር በኩል ያሬድ ከበደ ያሻማውን ኳስ ፉሴይኒ ኑሁ ወደ ግብነት በመቀየር መቐለ ከተማን መሪ ማድረግ ችሏል።

ከግቧ መቆጠር በኋላ ሃዋሳ ከተማዎች በሙሉ ሃይላቸው ሲያጠቁ የታዩ ሲሆን ብዙም ሳይቆዩ አቻ የሚሆኑበትን እድል አግኝተውም ነበር። አዲስዓለም በግሩም ሁኔታ የመታው ቅጣት ምት ቀሚውን ገጭታ የመለሰችው ኳስ ለእንግዶቹ እጅግ አስቆጪ ነበር። ሀዋሳ ከተማዎች በአምበሉ ደስታ ዮሀንስ በኩል የማጥቃት እንቅስቃሴ ያደረጉ ሲሆን መቐለዎችም በግራ መስመር በኩል የተፈጠረባቸውን ጫና ለመቋቋም ሲቸገሩ ተስተውሏል። ያሬድ ከበደን አስወጥተው መድሃኔ ታደሰ በማስገባት ወደ 4-4-2 አደራደር ቢቀይሩም ከኳስ ውጪ በአግባቡ ያልተደራጀ በመሆኑ የሃዋሳ አማካዮች እንደ ልብ መንቀሳቀስ ችለዋል።  በተለይም ታፈሰ ሰለሞን በመስመሮች መካከል በመቆም ችግሮችን ሲፈጥር እና ለጎል እድሎች መነሻ ሲሆን ነበር። በዚህ ሒደት የተገኘውን ኳስ ጋብሬል አህመድ ከታፈሰ የተሻገረለትን ኳስ ያመከናት ተጠቃሽ ናት። ከዚ ውጭም ጋብሬል አክርሮ ወደ ግብ መትቶ ፍቃዱ ተደርቦ ያወጣበት እንዲሁም ከሙሉዓለም ተሻግሮለት ዳዊት ሳይጠቀምበት የቀረው አጋጣሚ በሀዋሳ በኩል አስቆጪ የነበሩ ሙከራዎች ነበሩ።

ጨዋታው በመቐለ ከተማ 1-0 አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ መቐለ የሊጉን መሪነት በ42 ነጥቦች ከጅማ አባ ጅፋር ሲረከብ ሀዋሳ ከተማ በ33 ነጥቦች በነበረበት 7ኛ ደረጃ ላይ ረግቷል።