ሪፖርት | ቅዱስ ጊዮርጊስ ጅማን እግር በእግር መከተሉን ቀጥሏል

ተጠባቂ የነበረው የአመሻሹ የአዲስ አበባ ስታድየም ጨዋታ በጭቃማው ሜዳ ላይ ተደርጎ ቅዱስ ጊዮርጊስ በደደቢት ላይ የ 3-0 ድል ያሳካበት ሆኖ ተጠናቋል።

የቡድኖቹን የተጨዋቾች ምርጫ ከ26ኛው ሳምንት ጨዋታዎች አንፃር ስንመለከተው ቅዱስ ጊዮርጊስ ሙሉ በሙሉ ወልዲያን በረታበት የመጀመሪያ አሰላለፍ ወደ ሜዳ ሲገባ ደደቢት ደግሞ የሶስት ተጨዋቾች ቅያሪ አድርጓል። በዚህም መሰረት ዓዲግራት ላይ  ከተሸነፈበት ቡድን ውስጥ ክሌመንት አዞንቶን በታሪክ ጌትነት ፣ ኤፍሬም አሻሞን በአቤል እንዳለ ሲቀይር በጨዋታው በሁለት ቢጫ ካርዶች ከሜዳ የወጣው አስራት መገርሳን በብርሀኑ ቦጋለ ተክቷል። ከጨዋታው ጅማሮ በፊትም ከሁለት ሳምንታት በፊት ከዚህ አለም በሞት ለተለዩት የደደቢት አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ የህሊና ፀሎት የተደረገ ሲሆን የደደቢት ተጨዋቾች እና ደጋፊዎች የአሰልጣኙ ምስል የታተመበት ቲሸርት በመልበስ እንዲሁም ባነር ይዘው በመግባት ሀዘናቸውን ገልፀዋል።


ከጨዋታው መጀመር አስቀድሞ የጣለው ከባድ ዝናብ የአዲስ አበባ ስታድየም የመጨዋቻ ሜዳን ከወትሮውም በባሰ ሁኔታ አጨቅይቶት ነበር። በዚህም ሁለቱም ቡድኖች የመረጡትን አጨዋወት ለመተግበር ከመቸገራቸው በተጨማሪ ጨዋታው ፍትጊያ የበዛበት እንዲሆን ያስገደደም ነበር። ሆኖም የመጀመሪያውን ግብ የተመለከትነው የፌደራል ዳኛ ኃይለየሱስ ባዘዘው የጨዋታ ማስጀመሪያ ፊሽካ ከተሰማ በኃላ ብዙም ስይቆይ ነበር። በሁለተኛው ደቂቃ የመጀመሪያ ጥቃታቸውን የሰነዘሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በዛው ቅፅበት የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተዋል። አብዱልከሪም ኒኪማ ከሰነጠቀለት በኋላ አሜ መሀመድ ወደ ውስጥ ለማሳለፍ የሞከራት ኳስ በደስታ ደሙ በእጅ በመነካቷ ነበር ፍፁም ቅጣት ምቱ የተገኘው። ግዙፉ የመሀል ተከላካይ ሳላሀዲን ባርጌቾም አጋጣሚውን ወደ ግብ ቀይሮ ፈረሰኞቹን መሪ ማድረግ ችሏል።  

ግብ ካስተናገዱ በኃላ ደደቢቶች ቀድሞም በሚታወቁበት አጨዋወት በአጫጭር ቅብብሎች በቅዱስ ጊዮርጊስ ሜዳ ላይ ለረጅም ደቂቃዎች መቆየት ችለው ነበር። ሆኖም በጥልቀት ወደ ኃላ እየተሳበ ከአማካዮቹ ኳስ ለመቀበል ጥረት ሲያደርግ የነበረው ጌታነህ ከበደ ተሳትፎም የተጨመረበት የደደቢት የጨዋታ ምርጫ ከሜዳው ሁኔታ ጋር የተጣጣመ አይመስልም። ቡድኑ ኳስ ይዞ በቆየባቸው በነዚህ ጊዜያትም በቅዱስ ጊዮርጊስ የመከላከል ወረዳ የተገኘባቸው ጊዜያት ጥቂት ነበሩ። በ35ኛው ደቂቃ ከጌታነህ እና አቤል እንዳለ ቅብብል ከሳጥን ውጪ ከተሞከረው ኳስ ሌላ ቡድኑ የሮበርትን ጥረት የፈለገ የግብ አጋጣሚ መፍጠር ያልቻለበን የመጀመሪያ አጋማሽ አሳልፏል።
በፍጥነት መሪ መሆን የቻሉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በጀመሩበት ፍጥነት እና ጫና ባይቀጥሉም የተጋጣሚያቸውን አጨዋወት መግታት ግን አልከበዳቸውም ነበር። በማጥቃቱ ረገድ ቡድኑ ያገኛቸውን የቅጣት ምቶችን በረጅሙ ወደ ውስጥ በመጣል በጨዋታም በተመሳሳይ ከመስመር አማካዮቹ በሚነሱ ኳሶች ከተጋጣሚው በተሻለ ወደ ግብ ሲደርስ ቆይቷል። በዚህ ረገድ 8ኛው ደቂቃ ላይ ኦዝቫልዶ ታቫሬዝ ከቀኝ መስመር ወደ ውስጥ የጣለው እና መሀሪ መና 24ኛው ደቂቃ ላይ ከረጅም ርቀት ቅጣት ምት ያደረገው ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ተጠቃሽ ነበሩ። ከዚህ በተጨማሪ ከደደቢት ተጨዋቾች የሚቀሙ ኳሶችን ወደ ፊት በማሳለፍ የመልሶ ማጥቃት ዕድሎችን ሲጠብቁ የቆዩት ጊዮርጊሶች ከእረፍት በፊት ሁለተኛውን ግብ ያገኙት ግን 41ኛው ደቂቃ ላይ በሀይሉ አሰፋ ካሻማው የማዕዘን ምት ነበር። ግቧን በግንባር በመግጨት ያስቆጠረው ደግሞ አማካዩ ሙሉዓለም መስፍን ነው።


ሁለተኛው አጋማሽ በጀመረባቸው ደቂቃዎች በተሻለ ሁኔታ ረዘም ያሉ ኳሶችን ወደ ፊት መጣል የጀመሩት ደደቢቶች የኃላ ኃላ ወደ መጀመሪያው አጨዋወታቸው መመለሳቸው አልቀረም። አሁንም በተመሳሳይ ቅብብሎቻቸው ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ የግብ ክልል ለመድረስ የሚያደርጉት ጥረትም ከሜዳው አለመመቸት ጋር ተያይዞ ለአደገኛ የአንድ ለአንድ ፍልሚያዎች የሚያጋልጣቸው እንጂ ያለቀለት የግብ ዕድል የሚፈጥርላቸው አልሆነም። በአመዛኙ ከጌታነህ ከበደ ይነሱ የነበሩት ሙከራዎችም እምብዛም አደገኛ አልነበሩም። የፊት አጥቂው በ62 እና 74ኛው ደቂቃ ላይ ያደረጋቸው የርቀት ሙከራዎች በተሻለ መልኩ ኢላማቸውን የጠበቁ ቢሆኑም ሮበርት በቀላሉ ሊያድናቸው ችሏል።
በመከላከሉ በኩል ምንም ክፍተት ባለመፍጠር የቀጠሉበት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በሁለተኛው አጋማሽ በርከት ያሉ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችን ፈጥረዋል። ከግራ የቡድኑ ወገን የሚነሱ ተሻጋሪ ኳሶችም በተደጋጋሚ የደደቢትን የኃላ ክፍል ሲረብሹ ይታዩ ነበር። በተመሳሳይ መልኩ በ63ኛው ደቂቃ ላይ ኦዝቫልዶ ታቫራዝ ከግራ አቅጣጫ በረጅሙ የጣለውን ኳስ ናትናኤል ዘለቀን ቀይሮ የገባው ምንተስኖት አዳነ ታሪክ ጌትነትን በመቅደም ጨርፎ የቅዱስ ጊዬርጊስን መሪነት ወደ ሶስት ከፍ አድርጎታል። 67ኛው ደቂቃ ላይ አሜ መሀመድ ከሳጥን ውጪ የመታው እንዲሁም ከሁለት ደቂቃዎች በኃላ ታሪክ ጌትነት በሚገባ ካላራቀው ኳስ የተገኘው ዕድል የጊዮርጊስን መሪነት ከዚህም በላይ የማስፋት ዕድል ነበራቸው።


ደደቢቶች በመስመር በኩል የሚሰነዝሩትን ጥቃት የተሳካ ለማድረግ አኩዌር ቻሞ እና ኤፍሬም አሻሞን ቀይረው በማስገባት ከጌታነህ ግራ እና ቀኝ ያለውን ቦታ እንዲጠቀሙ ያሰቡ ቢመስልም ይህ ነው የሚባል ሙከራን መግኘት አልቻሉም። በተመሳሳይ መልኩ አቡበከር ሳኒ እና ጋዲሳ መብራቴን ወደ ሜዳ ያስገቡት ጊዮርጊሶች ግን ያለቀላቸው ዕድሎችን መፍጠር ችለዋል። በተለይ በ83ኛው ደቂቃ አሜ መሀመድ እንዲሁም በ89ኛው ደቂቃ አቡበከር  በመልሶ ማጥቃት ብዙ ርቀት ሸፍነው በደደቢት ሳጥን ውስጥ በመገኘት ያደረጓቸው ሙከራዎች ተጠቃሽ ነበሩ። ሆኖም የመጀመሪያውን ደስታ ደሙ ተንሸራቶ በመደረብ ሲያወጣው ሁለተኛው ሙከራ ደግሞ በታሪክ ጌትነት ድኗል። ቅዱስ ጊዮርጊስም ተጨማሪ ግብ ሳያክል ጨዋታውን በ3-0 ውጤት እንዲያሸነፍ ሆኗል።
ውጤቱ ቅዱስ ጊዮርጊስን ወደ 48 ነጥብ ከፍ እንዲል አድርጎት ጅማ አባ ጅፋርን በግብ ልዩነት ብቻ መከተሉን ሲቀጥል ደደቢት 24ኛው ሳምንት ላይ ከቆመበት 34 ነጥብ ሳይንቀሳቀስ ቀርቷል።

የአሰልጣኞች አስተያየት

ም/አሰልጣኝ ጌቱ ተሾመ – ደደቢት

ሜዳው ለጨዋታ ካለመመቸቱ አንፃር በዛሬው ጨዋታ ተዳክመን ነበር ብዬ አላስብም። በዚህ ሜዳ ላይ ይህን ያህል መንቀሳቀሳችን በራሱ ጥሩ እንደሆነ ነው የማስበው። ጎሎች ተቆጠሩብን እንጂ የተሻለ ኳስ ተቆጣጥረንም ነበር። ሜዳው ግን ምንም የሚያጫውት አልነበረም። 

አሰልጣኝ ቫስ ፒንቶ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

3-0 በማሸነፋችን እና ድንቅ እንቅስቃሴ በማድረጋችን ደስ ብሎኛል። ጨዋታውን ተቆጣጥረን ተጫውተናል። ተጨዋቾቻችን በተለይ በአዕምሮ ረገድ ጠንካራ ነበሩ። ከዚህም በላይ በርካታ ግቦችን ማስቆጠር እንችል ነበር። ደደቢት በአንፃሩ ከሁለት ጊዜ በላይ የመጨረሻ አጋጣሚዎችን መፍጠር አልቻለም።