ፕሪምየር ሊግ | የ27ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ቅድመ ዳሰሳ – ክፍል 3

ዛሬ አራት ጨዋታዎች የተስተናገዱበት የሊጉ 27ኛ ሳምንት ነገ በሁለት ጨዋታዎች ቀጥሎ ይውላል። መቐለ እና አዳማ ላይ የሚደረጉት እነዚህን ጨዋታዎችም በክፍል ሦስት ቅድመ ዳሰሳችን ተመልክተናቸዋል።

መቐለ ከተማ ከ መከላከያ

በ26ኛው ሳምንት ሙሉ ነጥብ ካላገኙ የዋንጫ ተፎካካሪዎች መካከል አንዱ የሆነው መቐለ ከተማ ወደ ሜዳው ተመልሶ መከላከያን ይገጥማል። መቐለ ላይ ሀዋሳን ካስተናገደ በኃላ በቀጣዮቹ ሁለት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ ያሳካው መቐለ ከተማ በዚህ ጨዋታ ወደ አሸናፊነቱ ካልተመለሰ በፉክክሩ ውስጥ ለመዝለቅ መቸገሩ አይቀርም። የጅማ አባ ጅፋር እና የቅዱስ ጊዮርጊስ የዛሬ አሸናፊነት የፈጠረውን የአምስት ነጥብ ልዩነትን ለማጥበብ ማሸነፍ ለመቐለ ብቸኛው አማራጩ ነው። 32 ነጥቦች ላይ የሚገኘው መከላከያ በበኩሉ በመጠኑ ከአደጋ የራቀ ቢመስልም ስጋት እያንዣበበት ይገኛል። በሰንጠረዡ ወገብ ላይ በደንብ ለመደላደልም ተጨማሪ ነጥቦች ያስፈልጉታል። ይህ በመሆኑም በሳምንቱ መጀመሪያ አዲስ አበባ ስታድየም ላይ ጨዋታዎቻቸውን ላደረጉት ሁለቱ ክለቦች በተለያየ መንገድ አስፈላጊያቸው የሆነው ይህ ጨዋታ ከወዲሁ ተጠባቂ ሆኗል።

የመቐለ ከተማው የፊት አጥቂ ቢስማርክ ኦፖንግ አሁንም ጉዳት ላይ የሚገኝ ሲሆን ቀሪው የቡድኑ ስብስብ ግን ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ነው። በመከላከያ በኩል ደግሞ አዲሱ ተስፋዬ እና ዳዊት እስጢፋኖስ ቅጣታቸውን ባለመጨረሳቸው ቴዎድሮስ በቀለ እና ዐወል አብደላ ደግሞ ከጉዳት ባለማገገማቸው ወደ መቐለ አልተጓዙም።

በዚህ ጨዋታ ላይ ጥሩ የማጥቃት ፍላጎት የሚታይበት ክፍት እንቅስቃሴ እንደሚኖር ይጠበቃል። የቢስማርክ ኦፖንግ አለመኖር ክፍተት እየፈጠረበት የሚገኘው መቐለ ከተማ በቦታው ዐመለ ሚልኪያስን ያሰለፈበት የፋሲል ጨዋታ በቂ ውጤት አላስገኘም። ከዚህ በተጨማሪ ኑሁ ፉሰይኒም በአጥቂ አማካይነት ያበረከተው አስተዋፅኦ እምብዛም ነበር። እነዚህ ነጥቦች ቡድኑ በነገው ጨዋታ ላይም ተጨማሪ ሽግሽጎች እና ቅያሪዎች ሊያደርግ እንደሚችል ያመለክታሉ። ሆኖም ተጋጣሚው ለመስመር ተከላካዮቹ የማጥቃት ነፃነትን የሚሰጥ እንደመሆኑ መጠን በአማኑኤል ገ/ሚካኤል የሚመራው የመቐለ የመስመር ጥቃት የተሻለ ዕድልን የሚፈጥርለት ይሆናል። ቡድኑ በጠንካራው የተከላካይ አማካይ ጥምረቱ የሚያቋርጣቸው የተጋጣሚው ቅብብሎችም በፈጣን የማጥቃት ሽግግሮች ከታገዙ የግብ ዕድል ለመፍጠር ጠቃሚ እንደሚሆኑ ይታመናል።

ለኳስ ቁጥጥር የበላይነት ቦታ የሚሰጠው የአሰልጣኝ ስዩም ከበደ ቡድን ሁለት አጥቂዎችን ቢጠቀምም አንደኛው ለአማካይ ክፍሉ ቀርቦ የመጫወት ኃላፊነት ሲሰጠው ይታያል። መከላከያ ነገም የመቐለን የሁለትዮሽ የተከላካይ አማካይ ጥምረት ለማለፍ ለፈጣሪው አማካይ የቅብብል አማራጬችን ለመፍጠር ተመሳሳይ አካሄድ እንደሚኖረው ይታሰባል። ከዚህ በተጨማሪ ቡድኑ የመስመር ተከላካዮቹንም በመጠቀም መሀል ሜዳው ላይ የቁጥር ብልጫን በማግኘት እና ወደ መሀል አጥብበው ከሚጫወቱ የመስመር አማካዮቹ ጥረት ጋር በመጨመር ከባዱን የመቐለ የተከላካይ መስመር አልፎ ወደ ፍፁም ገ/ማርያም የመጨረሻ ኳሶችን ለማድረስ የሚሞክርበት ዕድል ይኖራል። በዚህ ሂደት ውስጥ ከመቐለ የተከላካይ መስመር ፊት የሚኖረውን ክፍተት ለቅብብሎች መጠቀም የመከላከያዎች ዋነኛ የቤት ስራ እንደሚሆን ይታሰባል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– የቡድኖቹ የመጀመሪያ የሆነው የዘንድሮው የ12ኛ ሳምንት ግንኙነት በመከላከያ 1-0 አሸናፊነት ሲጠናቀቅ ምንይሉ ወንድሙ ግብ አስቆጣሪ ነበር።

– መቐለ ከተማ በሁለተኛው ዙር ሜዳው ላይ ካደረጋቸው አራት ጨዋታዎች ሶስቱን አሸንፎ በአንዱ ነጥብ ተጋርቷል። በእነኒህ ጊዜያት 8 ግቦችን ሲያስቆጥር መረቡ የተደፈረው አንዴ ብቻ ነበር።

– መከላከያ ሁለተኛው ዙር ከገባ አምስት ጊዜ ከአዲስ አበባ የወጣ ሲሆን ሁለት ድል ሁለት ሽንፈት ገጥሞት በአንድ አጋጣሚ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል።

ዳኛ

–  ይህን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት የሚመራው ፌደራል ዳኛ አዳነ ወርቁ ነው።               

አዳማ ከተማ ከ አርባምንጭ ከተማ

በደረጃ ሰንጠረዡ አናት እና ግርጌ ባሉት ፉክክሮች ውስጥ የሚገኙት አዳማ እና አርባምንጭ ነገ የየራሳቸውን ጉዞ በሚወስነው ጨዋታ ይገናኛሉ። ለሶስት ቀናት ሊጉን የመምራት ዕድል አግኝቶ የነበረው አዳማ በኢትዮጵያ ቡና በመሸነፉ ወደ አምስተኛነት ተንሸራቷል። አሁንም ሙሉ ለሙሉ ተስፋው ያልመከነው አዳማ ነገ ሙሉ ነጥብ ማግኘት ከቻለ እስከ ሶስተኝነት ከፍ የማለት ዕድል ይኖረዋል። 15ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው አርባምንጭ ከበላዩ ያሉት ድሬዳዋ እና ኤሌክትሪክ ነጥብ በመጋራታቸው ከአዳማ ሶስት ነጥብ ማግኘት በግብ ክፍያም ቢሆን ከወራጅ ቀጠናው ያስወጣዋል። አንድ ተስተካካይ ጨዋታ ላለው አርባምንጭ እንደ ጅማው ጨዋታ ሁሉ ከአዳማም ነጥብ ከተጋራ ከታች ላለው ሩጫ የሚረዳው በመሆኑ በሜዳቸው ለመጨረሻ ጊዜ ባደረጉት ጨዋታ ስድስት ግቦች ላስቆጠሩት አዳማዎች ከባድ ተፎካካሪ እንደሚሆን ይጠበቃል።

በኢትዮጵያ ቡናው ጨዋታ በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ የወጡት ጃኮ ፔንዜ እና በረከት ደስታ ከአዳማ በቅጣት ከነገው ጨዋታ ውጪ ሲሆኑ በዛው ጨዋታ ጉዳት ገጥሞት የነበረው ሱራፌል ዳኛቸው ግን እንደሚመለስ ተሰምቷል። አርባምንጭ በበኩሉ ያለ ጉዳት እና ቅጣት መሉ ቡድኑን ይዞ ወደ አዳማ አቅንቷል።

በሜዳው ሙሉ ለሙሉ በማጥቃት ላይ የተመሰረት እንቅስቃሴ የሚያደርገው አዳማ ከተማ በተመሳሳይ አኳኋን ለነገው ጨዋታ እንደሚዘጋጅ ይታሰባል። በንፅፅር በራሳቸው ሜዳ ላይ ቆይተው የሚከላከሉ ቡድኖች ሲገጥሙት የሚቸገርው አዳማ ነገም ተመሳሳይ ፈተና ሊገጥመው የሚችል በመሆኑ ዋነኛ የማጥቃት አማራጮቹን እንደሚጠቀም ይታሰባል። በዚህም በከንዓን ማርክነህ ከሚመራው እና ከመስመር ተከላካዮቹ እገዛን በሚያገኘው የአማካይ ክፍሉ የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን በማግኘት ወደ ቀኝ ባደላ ጥቃት ክፍተቶችን ለማግኘት እንደሚሞክር ይታሰባል። ዳዋ ሁቴሳ ፊት ላይ ሆኖ ከተጋጣሚው የኃላ መስመር ጋር የሚያደርገው ፍልሚያ እና የሱራፌል ዳኛቸው የረጅም ርቀት ኳሶችም ቡድኑን ለውጤት ለማብቃት ወሳኝ ይሆናሉ። 

አርባምንጭ ከተማ በጨዋታው ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ እንደሚቀርብ ይታሰባል። የአማካይ ክፍሉን ለተከላካይ መስመሩ በማቅረብ እንዲሁም በምንተስኖት አዳነ እና አማኑኤል ጎበና ጥምረት የከንዓንን የአማካይ መስመር እንቅስቃሴ በመግታት አዳማ በማጥቃት ዞን ውስጥ ደጋግሞ እንዳይገባ ማድረግ ከአዞዎቹ ይጠበቃል። ከዚህ በተጨማሪ የመስመር ተከላካዮቻቸውን የመከላከል ኃላፊነት በማብዛት የአዳማን የመስመር አማካዮች ማቆም ሌላው ወሳኝ ተግባራቸው ሊሆን ይችላል። አርባምንጮች በራሳቸው ሜዳ ላይ የሚያቋርጧቸውን ኳሶች በመጠቀም ለፊት አጥቂዎቻቸው በተለይም ለተመስገን ካስትሮ ምቹ ቀጥተኛ ኳሶችን ማድረስ ደግሞ ግብ ለማስቆጠር የሚጠቀሙበት አካሄድ የመሄን ዕድል አለው። ለዚህ ሂደት ውስጥ የመስመር አማካዮቻቸው ኃላፉነት የጎላ ሲሆን ተመስገን እና ብርሀኑ አዳሙም ከአዳማዎቹ ሙጁብ ቃሲም እና ምኞት ደበበ ጋር ብርቱ ፍልሚያ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– 11 ጊዜ ተገናኝተው አዳማ 4 ጊዜ ሲያሸንፍ 2 ጊዜ አቻ ተለያይተው አርባምንጭ ከተማ 5 ጊዜ ማሸነፍ ችሏል። አዳማ 8 ሲያስቆጥር አርባምንጭ 9 አስቆጥሯል።

– አዳማ አበበ ቢቂላ ስታድየም ላይ 5 ጊዜ ተገናኝተው አዳማ 3 ጊዜ ሲያሸንፍ አርባምንጭ ቀሪዎቹን ሁለት ጨዋታዎች አሸንፏል።

– አዳማ ከተማ በሁለተኛው ዙር ከሰበሰባቸው 19 ነጥቦች መካከል 15ቱን ያሳካው በሜዳው ነው። ከስድስት ጨዋታዎችም አንዴ ሽንፈት ሲገጥመው ሌሎቹን በድል ተወጥቷል።

– አርባምንጭ ከተማ ለመጨረሻ ጊዜ ከሜዳው ከወጣባቸው አምስት ጨዋታዎች ያሳካው አንድ ነጥብ ብቻ ሲሆን 9 ግቦች ተቆጥረውበት አንድም ጊዜ ኳስ እና መረብን አላገናኘም።

ዳኛ

– ፌደራል ዳኛ ተካልኝ ለማ ይህን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት የሚመራው ይሆናል።