ሪፖርት | መቐለ ከተማ መሪዎቹን መከተሉን ገፍቶበታል

በ27ኛው ሳምንት የሊጉ የዛሬ መርሀ ግብር መከላከያን ያስተናገደው መቐለ ከተማ 1-0 በማሸነፍ ጅማ አባ ጅፋር እና ቅዱስ ጊዮርጊስን በሁለት ነጥቦች ርቀት መከተሉን ቀጥሏል።

መቐለ ከተማ በ26ኛው ሳምንት በድሬዳዋ ከተሸነፈው ስብስብ መካከል በያሬድ ብርሀኑ ምትክ ያሬድ ከበደን በመጀመርያው አሰላለፍ ሲጠቀም በጅማ ከተሸነፈው ስብስብ በርካታ ለውጦችን ባደረገው መከላከያ በኩል ይድነቃቸው ኪዳኔ፣ ማራኪ ወርቁ፣ በኃይሉ ግርማ፣ ምንይሉ ወንድሙ አርፈው አቤል ማሞ፣ አማኑኤል ተሾመ፣ አቤል ከበደ እና ሳሙኤል ሳሊሶ በመጀመርያ አሰላለፍ ተካተዋል።

በጥሩ ፍጥነት የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያው አጋማሽ ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ እና መልካም ፋክክር የታየበት ነበር። አሞስ አሻምቶት ፋሴይኒ ኑሁ አግኝቶ ከመምታቱ በፊት የጦሩ ተከላካዮች ተረባርበው ባወጡት ሙከራ ተነቃቅተው የጀመሩት ባለሜዳዎቹ በሙከራ ረገድ ከመከላከያ የተሻሉ ነበሩ። መቐለ ከተማዎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሜዳቸው በሚያረጉት ጨዋታ የሚተገብሩትን ተጋጣሚ ቡድንን በራሱ ሜዳ ላይ በማፈን የቅብብል አማራጭ እንዲያጣ የመጫን አጨዋወትን ዛሬም ቢጠቀሙበትም መከላከያዎች ጫናውን በብልሃት በመቋቋም ጥሩ ተንቀሳቅስዋል። በተለይም አማኑኤል ተሾመ እና ቴድሮስ ተፈሰ ቡድኑ ኳስ ሲያጣ ለተከላካይ ክፍሉ ሙሉ ሽፋን እየሰጡ ከኳስ ጋር ደግሞ በማጥቃት ሽግግሩ ላይ እየተሳተፋ በ3ኛው የሜዳ ክፍል የቁጥር ብልጫ እንዳይወሰድባቸው አድርገዋል። ሆኖም ይህ አጨዋወታቸው ከ25ኛው ደቂቃ በኃላ በብዛት አልታየም። ዕድሎችን በመፍጠሩም በኩልም በ19ኛው ደቂቃ ፍፁም ገ/ማርያም በግል ጥረቱ ይዞ ገብቶ አክርሮ በመታው እና የግቡን ቋሚ የታችኛው ክፍል ገጭቶ በወጣበት ኳስ አስደንጋጭ ሙከራ ቢያረጉም ከዚያ በኃላ በነበረው እንቅስቃሴ ጥንቃቄ በመምረጥ ይህ ነው የሚባል የጎል ሙከራ ማድረግ አልቻሉም።

በአንፃሩ መቐለ ከተማዎች በሚታወቁበት ሁለት ቦታቸውን የማይለቁ እና ለተከላካይ መስመሩ ሙሉ ሽፋን የሚሰጡ አማካዮች አጨዋወት ይልቅ ቡድኑ ኳስ ሲያገኝ ሚካኤል ደስታ ለጋቶች ፓኖም ቀርቦ እንዲጫወት በማድረግ ወደ 4-1-2-3  የሚጠጋ ቅርፅ መያዝን በመምረጣቸው ቡድኑ በተጋጣሚ ሜዳ ላይ ተጭነው የሚጫወቱ 5 የሚደርሱ ተጫዋቾችን ከማግኘቱ ባለፈ የመከላከያ አማካዮች የፊት ለፊት እንቅስቃሴን በመቀነስ በብቸኛ አጥቂነት የተሰለፈው ፍፁም ገ/ማርያም ከቡድኑ እንዲነጠል አድርገውታል። የመስመር ሽግግርን ማሳካት የሚችሉት ሁለቱ አማካዮች ያሬድ ከበደ እና ፉሰይኒ ኑሁን መሰረት አድርጎ የቀጠለው የባለሜዳዎቹ የማጥቃት አጨዋወት ያለቀላቸው ዕድሎችም የተፈጠሩበት ነበር። በዚህ ረገድ ታታሪው ፋሴይኒ ነሁ አሻምቶት ያሬድ ከበደ በግንባሩ ገጭቶ ወደ ውጭ የወጣው እና ራሱ ኑሁ ፋሴይኒ ካሻማው ሌላ ኳስ ሚካኤል ደስታ ያመከነው ተጠቃሽ ነበሩ።

መቐለ ከተማዎች አጥቅተው መጫወታቸውን ቢቀጥሉም በሽመልስ ተገኝ የሚመራውን የመከላከያ ጠንቃቃ የኃላ ክፍል ሰብረው መግባት ከብዷቸው ታይተዋል። በመጀመሪያው አጋማሽ የመጨረሻ ደቂቃዎች አጥቅተው የተጫወቱት መከላከያዎች በተራቸው የግብ ዕድልን ሲፈጥሩ ታይተዋል። ሳሙኤል ሳሊሶ ያሻማውን ኳስ አቤል ከበደ በግንባሩ ገጭቶ ተከላካዮች ያወጡበት እና ፍፁም ገ/ማርያም አክርሮ መቶ ኢቮኖ ያዳነበት ሙከራዎች በዚህ ውስጥ የሚካተቱ ነበሩ። ከዚህ ውጪ በመጀመርያዎቹ 15 ደቂቃዎች ጉዳት ገጥሞት የነበረው ጋቶች ፓኖም እስከ 43 ደቂቃ ቆይቶ በሃብታሙ ተከስተ ተቀይሮ መውጣቱ ከእረፍት በፊት  የሚጠቀስ ክስተት ነበር።

ጥቂት የግብ አጋጣሚዎች በታዩበት 2ኛው አጋማሽ ሙከራ በማድረግ ቀዳሚ የነበሩት ባለ ሜዳዎቹ ሲሆኑ ሚካኤል ደስታ በግንባር በመግጨት ያመቻቸለትን ኳስ አመለ ቢመታም አቤል በቀላሉ አድኖበታል። ደቂቃዎች እየገፉ በሄዱ ቁጥር እጅግ በተቀዛቀዘው ጨዋታ ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው የገቡት መከላከያዎች ሁለት አስቆጪ አጋጣሚዎች ፈጥረው ነበር። ሳሙኤል ሳሊሶ በግሩም ሁኔታ አክርሮ የመታውን ኳስ ፊሊፕ ኦቮኖ ጨርፎ ሲያወጣው ሳሙኤል ሳሊሶ ያሻማውን መኣዝን ምት ከተከላካዮች ጀርባ ነፃ አቋቋም ላይ የነበረው ሳሙኤል ታየ ቢያገኘውም በሚያስቆጭ ሁኔታ አባክኖታል።

አሰልቺ በነበረው የሁለቱ ቡድኖች እንቅስቃሴ ላይ የመከላከያ ተጫዋቾች ተደጋጋሚ ጊዜ ማባከን ተደምሮበት ጨዋታውን እጅግ የተቀዛቀዘ አድርጎታል። በ71ኛው ደቂቃ ላይ በግርግር መሃል የተሰነጠቀለትን ኳስ ተጠቅሞ አጥቂው አማኑኤል ገብረሚካኤል አስቆጥሮ መቐለ ከተማን መሪ አድርጓል። ሆኖም አጥቂው ጎሉን ከማስቆጠሩ በፊት በሳጥን ውስጥ በተከላካይ ላይ ጥፋት ሰርቷል በሚል ተቃውሞ አቅርበዋል። ከ8 ደቂቃዎች ክርክር በኋላ በቀጠለው ጨዋታ ኳስ አቀባዮች በትክክል ኳስ ከማቀበል ይልቅ ጨዋታውን ለማዘግየት ዘለግ ያለ አላስፈላጊ ጊዜ ሲፈጁ የእለቱ ዳኛ የቡድን መሪው ተክለ እያሱ በመጥራት እንዲስተካከል ቢሞክሩም ባለመስተካከሉ የመከላከያ ቡድን አባላት ቅሬታቸው አሰምተዋል።

ደቂቃዎች እየገፉ በሄዱ ቁጥር መቐለዎች አፈግፍገው ሲጫወቱ መከላከያዎች የአጥቂ ቁጥር በመጨመር ያላቸውን አቅም አሟጠው ቢያጠቁም ተቀይረው የገቡት ምንይሉ ወንድሙ  እና ማራኪ ወርቁ ካደረጓቸው ያልተሳኩ ሙከራዎች ውጭ ይህ ነው የሚባል ለግብ የቀረበ ሙከራ ሳያደርጉ ጨዋታው በመቐለ ከተማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎም መቐለ ከተማ ከመሪዎቹ በ2 ነጥቦች አንሶ በ3ኝነት መከተሉን ሲቀጥል መከላከያ ደግሞ የደረጃ ለውጥ ባያሳይም ከወራጅ ቀጠናው በ3 ነጥቦች ብቻ ርቆ 9ኛ ላይ ተቀምጧል።

አሰልጣኝ ዮሀንስ ሳህሌ – መቐለ ከተማ

ማሸነፍ ይገባናል፤ ከሚገባን በላይ አጥቅተናል። እነሱም ጥሩ ተከላክለዋል። ዘጠና ደቂቃው ሙሉ ስናየው ማሸነፍ ይገባናል። ሌላው ጅማ እና ጊዮርጊስን መከታተል ስላለብን ይሄን ጨዋታ ማሸነፍ ግድ ነበር። አምስት ተጫዋቾች ወደ ፊት ልከን ከፍተን ነው የተጫወትነው። ይሄ ሁሉ ደጋፊ ለማሸነፍ ነው የመጣው ማሸነፍ ይገባናል።

* የአሰልጣኝ ስዩም ከበደን አስተያየት ማግኘት አልቻልንም።