የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን እሁድ እለት በሬሞ ክለብ ሽንፈትን ካስተናገደ በኋላ ሰኞ እለት ወደ መዲናዋ ብራዚልያ ተመልሶ ዝግጅቱን ቀጥሏል፡፡
በግራናዳ ኤቨንት አማካኝነት ወደ ብራዚል የተጓዙት ዋልያዎቹ ትላንት በሲቲ ፋየር ዴፓርትመንት ልምምዳቸውን የሰሩ ሲሆን ቅዳሜ በቤዜራኦ ስታድየም ከጋማ እግርኳስ ክለብ ጋር ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፡፡
በብራዚል ሁለተኛ ዲቪዝዮን የሚገኘው ጋማ እግርኳስ ክለብ በርካታ ደጋፊዎች ያሉት ክለብ ሲሆን በአውሮፓ ክለቦች ለሪያል ማድሪድ ፣ ዴፖርቲቪ እና ዶርትሙንድ እንዲሁም ለብራዚል ብሄራዊ ቡድን ለበርካታ አመታት የተጫወተው ፍላቪዮ ኮንሴሳኦ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን በተቃራኒ ይገጥማል፡፡
የኢትዮጵያ የብራዚል ዝግጅት አዘጋጅ የሆነው ማርሲዮ ግራናዳ የዋልያዎቹ የብራዚል ቆይታ ስኬታማ መሆኑን ተናግሯል፡፡ ‹‹ ዋልያዎቹ ከሬሞ ጋር ያደረጉት ጨዋታ ስኬታማ ነበር፡፡ በጨዋታው በተገኘው የተመልካች ቁጥር እና የሜዳ ላይ ፉክክር ደስተኛ ነን፡፡ ቅዳሜ ኢትዮጵያ ከ ጋማ ክለብ ጋር የምታደርገው ጨዋታን ለመከታተል የሚፈልጉ ተመልካቾች ቁጥርም ከፍተኛ ነው፡፡ ›› ብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በብራዚልያ እስከ ኦክቶበር 23 ድረስ በመቆየት ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ዝግጅት ማድረጉን ይቀጥላል፡፡ ከጋማ ጋር የሚያደርገውን ጨዋታ ተከትሎም ከብራዚልዬንሴ እና ሉዚንያ ክለቦች ጋር ይጫወታል፡፡