ኢትዮጵያውያን ዳኞች ወሳኝ የቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታ ይመራሉ

የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የምድብ ጨዋታዎች በቀጣዩ ሳምንት ሲጠናቀቁ በምድብ ሁለት ኢኤስ ሴቲፍ ከ ኤምሲ አልጀር የሚያደርጉትን ጨዋታ ኢትዮጵያውያን ዳኞች እንደሚመሩት ካፍ አሳውቋል። 

በምድብ ለ የዲ.ሪ. ኮንጎው ቲፒ ማዜምቤ ከ5 ጨዋታዎች 11 ነጥቦችን ሰብስቦ ወደ ሩብ ፍፃሜው መግባቱን ሲያረጋግጥ የአልጄሪያው ኢኤስ ሴቲፍ፣ የሞሮኮው ዲፋ ሀሰን ኤል ጀዳዲ እንዲሁም ሌላው የአልጄርያ ክለብ ኤምሲ አልጀር በተመሳሳይ 5 ነጥቦች ይከተላሉ። የምድቡ የመጨረሻ ጨዋታዎች ነሀሴ 22 ሲደረጉ በስታደ ጁልየ 1962 ሁለቱ የአልጄርያ ክለቦች ኢኤስ ሴቲፍ እና ኤምሲ አልጀር የሚያደርጉት ወሳኝ ጨዋታን ኢትዮጵያዊው ኢንተርናሽናል ዳኛ በዓምላክ ተሰማ በመሐል ዳኝነት የሚመራው ይሆናል። ረዳቶቹ ደግሞ ሌሎቹ ኢትዮጵያውያን ኢንተርናሽናል ዳኞች ተመስገን ሳሙኤል እና ክንዴ ሙሴ ናቸው።

ኢትዮጵያውያን ዳኞች በተለያዩ የአፍሪካ እና የዓለም አቀፍ ውድድሮች የመዳኘት እድል እያገኙ ሲሆን በዓለም ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ዋንጫ ሊዲያ ታፈሰ በመሐል ዳኝነት ስትመራ በሴካፋ ዞን የአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች ዋንጫ ደግሞ በላይ ታደሰ እና ትግል ግዛው ጨዋታዎችን እየመሩ የሚገኙ ዳኞች ናቸው።