ሪፖርት | ሽረ እንዳስላሴ ለመጀመርያ ጊዜ ወደ ፕሪምየር ሊግ አድጓል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ወሳኙ የመለያ ጨዋታ ዛሬ ሀዋሳ ላይ በሽረ እንዳሥላሴ እና ጅማ አባ ቡና መካከል ተከናውኖ ሽረ 2-1 አሸንፎ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ያደገ ሶስተኛው ክለብ ሆኗል። 

የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል አቶ ዘሪሁን ቀቀቦ እና ሌሎች የክብር እንግዶች ተጫዋቾችን ከተዋወቁ በኋላ በኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙር ታጅቦ የተከናከነው ጨዋታ የመጀመርያው አጋማሽ የአባ ቡና የበላይነት ጎልቶ የታየበት፣ በሁለተኛው አጋማሽ ደግሞ ሽረ ውጤት የቀለበሰበትን የበላይነት ያሳየበት ነበር። 

ሽረ እንዳስላሴ በአባ ቡና ተጫዋች ተገቢነት ላይ ክስ ካስመዘገቡ በኋላ በአባ ቡናዎች ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ የተጀመረው ጨዋታ ጎል ለማስተናገድ ብዙ ደቂቃ መጓዝ አላስፈለገውም። በ4ኛው ደቂቃ ከግራ መስመር ከረጅም ርቀት የተሻገለትን ኳስ በቀኝ የሳጥኑ ክፍል ጥሩ አቋቋም ይዞ የነበረው ብዙዓየው እንደሻው በቀጥታ በመምታት ወደ ግብነት ቀይሮ አባ ቡናን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል። ከጎሉ በኋላም አመዛኙን የመጀመርያ አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ አባ ቡናዎች የተሻሉ የነበሩ ሲሆን በኳስ ቁጥጥርም ሆነ ወደ ጎል በመቅረብ ረገድ ብልጫን አሳይተዋል። 

በ12ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት ዳዊት ተፈራ ያሻማውን ኳስ በኃይሉ በለጠ በግምባሩ ገጭቶ ወደ ውጪ የወጣበት አንዲሁም በ20ኛው ደቂቃ ሱራፌል ጌታቸው ከመስመር ያሻገረውን ኳስ ሀይደር ሸረፋ ተንሸራቶ ሳይደርስበት የቀረው ሙከራ በአባ ቡና በኩል የሚጠቀሱ የግብ አጋጣሚዎች ነበሩ። በአንፃሩ ሽረዎች በመጀመርያው አጋማሽ ከራሳቸው የሜዳ ክልል ለመውጣት ሲቸገሩ የተስተዋሉ ሲሆን ሊጠቀስ የሚችል የግብ ሙከራ ማድረግ ሳይችሉ የመጀመርያው አጋማሽ በጅማ አባ ቡና መሪነት ተጠናቋል። 

ከእረፍት መልስ ፍፁም የተሻሻለ ሽረ እንዳሥላሴን በተቃራኒው ደግሞ የተዳከመ እና ለሚደረጉበት ጥቃቶች ምላሽ የማይሰጥ አባ ቡናን ተመልክተናል። ሽረ በተለይ በግራ መስመር በኩል ባደላ እንቅስቃሴ ከሸዊት ዮሀንስ በሚነሱ ኳሶች ተደጋጋሚ አደጋዎችን የመፍጠር ሙከራዎች አድርገዋል። በ59ኛው ደቂቃ ሸዊት ከሳጥኑ ጠርዝ ወደ ግብ የመታው ኳስ ቋሚውን ገጭቶ ሲወጣበት ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ በግበ ጠባቂ ከተመለሰ ኳስ ያገኘውን መልካም እድል ኳሷን ወደ ላይ በመስደድ አምክኗታል። 

የሽረዎች የግብ ፍለጋ ጫና በርትቶ በ73ኛው ደቂቃ የጨዋታው ልዩነት ፈጣሪ ሸዊት ዮሀንስ ከግራ መስመር አክርሮ በቀጥታ ወደ ግብ የላካት ኳስ በማራኪ ሁኔታ ከመረብ አርፋ አቻ መሆን ችለዋል። የአቻነት ጎሉ መቆጠሩን ተከትሎ ተዳክመው የታዩት አባ ቡናዎች ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ያደርጋሉ ተብሎ ቢጠበቅም ሽረዎች ይህን የሚያደርጉበት እድል አልሰጧቸውም። የአቻነት ጎሉ እንደተቆጠረ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ሰዒድ ሁሴን በ76ኛው ደቂቃ ግብ ጠባቂው ሙላት ዓለማየሁ የተፋውን ኳስ በፍጥነት ደርሶ ወደ ግብነት በመቀየር ሽረን ወደ መሪነት አሸጋግሯል። 

በመጨረሻዎቹ 15 ደቂቃዎች አባ ቡናዎች ግብ አስቆጥረው ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ቢያደርጉም የሽረን የተከላካይ መስመር የሚፈትን የተደራጀ የማጥቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ሳይችሉ ቀርተዋል። በ90+1ኛው ደቂቃ ላይ ሐፍቶም ቢሰጠኝ በቀይ ካርድ የወጣበት ክስተትም የጨዋታው የመጨረሻ ደቂመዎች አካል ነበር። 

ጨዋታው በሽረ እንዳሥላሴ 2-1 አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ የሰሜን ኢትዮጵያው ክለብ ከፍተኛ ሊጉን በሶስተኛ ደረጃ በማጠናቀቁ ከእለቱ የክብር እንግዶች የነሀስ ሜዳልያ ሲበረከትለት ለመጀመርያ ጊዜ ወደ ፕሪምየር ሊግ ማደጉንም አረጋግጧል። ጅማ አባ ቡና በአንፃሩ በወረደበት ዓመት ወደ ፕሪምየር ሊግ ለመመለስ ከጫፍ ደርሶ ሳይሳካለት ቀርቷል።

በ2005 የተመሰረተው ሽረ እንዳሥላሴ በተመሰረተ በቀጣዩ ዓመት ወደ ብሔራዊ ሊግ መሸጋገር የቻለ ሲሆን በ2009 ከፍተኛ ሊጉን በተቀላቀለበት ዓመት ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለማደግ ከወልዋሎ እና መቐለ ጋር ተፎካክሮ ሶሥተኛ ደረጃን ይዞ ነበር ያጠናቀቀው። ዘንድሮ ደግሞ ከምድቡ ሁለተኛ ደረጃ ይዞ በማጠናቀቅ በመለያ ጨዋታ ጅማ አባ ቡናን አሸንፎ በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ ፕሪምየር ሊጉን ተቀላቅሏል። በዳንኤል ጸሀዬ የሚመራው ክለብ በቀጣዩ ዓመት በፕሪምየር ሊጉ ከሚሳተፉ ክለቦች በእድሜ ትንሹ የሚሆንበት ታሪክም አስመዝግቧል።