ሀዋሳ ከተማ በውሰት የሰጣቸውን ተጫዋቾች መልሷል

ሀዋሳ ከተማ ለከፍተኛ ሊግ ክለቦች በውሰት ሰጥቷቸው የነበሩ ሁለት ተጫዋቾቹን ወደ ክለቡ መልሷቸዋል። 

በ2009 የውድድር ዓመት የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ ማጠናቀቅ የቻለው ገብረ መስቀል ዱባለ ወደ ስልጤ ወራቤ በውሰት ካመራ በኋላ 14 ጎሎችን በማስቆጠር የሊጉ ሁለተኛ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ አጠናቋል። አሁን ደግሞ ወደ ሀዋሳ ከተማ የተመለሰ ሲሆን ከእስራኤል እሸቱ እና አዲሱ ፈራሚ ክዎሜ ፉቪ ጋር ለመጀመርያ ተሰላፊነት ይፎካከራል።

ሌላው ከውሰት የተመለሰው አክሊሉ ተፈራ በወልቂጤ ከተማ መልካም የውድድር ዓመት ያሳለፈ የመስመር አጥቂ ነው። አምስት ግቦችን ከመስመር እየተነሳ ማስቆጠር የቻለው አክሊሉ በወልቂጤ አብረውት ከሰሩት አሰልጣኝ አዲሱ ካሳ ጋር በሀዋሳ በድጋሚ የሚገናኝ ይሆናል።

በየዓመቱ ከወጣት ቡድኑ ተጫዋቾችን በማሳደግ የሚታወቀው ሀዋሳ ከተማ በዚህ ክረምትም 5 ተጫዋቾችን ያሳድጋል ተብሏል። በ17 ዓመት በታች ብሐራዊ ቡድን ያንፀባረቀው ምንተስኖት እንድርያስም ከሚያድጉት ተጨዋቾች መካከል እንደሆነም ተገልጿል።

በተያያዘ ዜና ሀዋሳ ከተማ የቦርድ አባላቱን መበተኑ የተነገረ ሲሆን አዳዲስ አባላት በቅርቡ ይመረጣሉ ተብሏል።