ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ሲዳማ ቡና ከ ፋሲል ከነማ

ሲዳማ ቡና ፋሲል ከነማን የሚያስተናግድበት የዓመቱ የመጀመሪያ የሊግ ጨዋታ በቅድመ ዳሰሳችን ተመልክተነዋል። 

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የዘንድሮው የውድድር ዓመት ሀዋሳ ላይ በ09፡00 በሚደረገው የሲዳማ ቡና እና ፋሲል ከነማ ጨዋታ ይከፈታል። ሲዳማ ቡናም ከይርጋለሙ ስታድየም ወደ ሀዋሳ ሰው ሰራሽ ሜዳ በመምጣት የሚያደርገው የመጀመሪያ ጨዋታ ይሆናል። በሌላ በኩል ደግሞ አዲሱ የፋሲል ከነማ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ላለፉት ሦስት ዓመታት ሀዋሳን ይዞ በተጫወተበት ስታድየም የመጀመሪያ የሜዳ ውጪ ጨዋታውን እንደሚያደርግ ይጠበቃል።

ሁለቱ ክለቦች በክረምቱ ጊዜ ብዙ ለውጦችን አድርገዋል። ሲዳማ አስር ፋሲል ከነማ ደግሞ አስራ ሁለት ዝውውሮችን ፈፅመዋል። በአሰልጣኝ ቅጥር በኩል ሲዳማ ቡና ከአሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ጋር ሲቀጥል ፋሲል ከነማ ከአሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ጋር የነበረውን ውል ጨርሶ ከውበቱ አባተ ጋር ውድድሩን ይጀምራል። ክለቦቹ በቅድመ ውድድር ጊዜ የተሳተፉባቸውን ውድድር ስንመለከት ሲዳማዎች የደቡብ ካስትል ዋንጫን ማንሳት ሲችሉ በአዲስ አበባ ዋንጫ ላይ የተሳተፉት ፋሲሎች ከምድብ ማለፍ ሳይችሉ ቀርተዋል። 

በነገው ጨዋታ አጠቃላይ እንቅስቃሴ ሲዳማ ቡና በዋናነት በአዲስ ግደይ በሚመራው የመስመር ጥቃቱ ሊያመዝን እንደሚችል ሲገመት አዲስ ከፍፁም ከበደ ጋር የሚገናኝበት የሜዳ ክፍል ትልቁን ፍልሚያ እንደሚያስተናግድ ይጠበቃል። በፋሲል በኩል ሱራፌል ዳኛቸው ወደ ኋላ እየተሳበ የሚያግዘው የአማካይ ክፍል የኳስ ቁጥጥር የበላይነቱን ለማግኘት የሚያደርገው ጥረት ከሲዳማ የሚገጥመውን ፍልሚያ የሚያስመለክተን ይሆናል።

ሙጃይድ መሀመድ እና ወንድሜነህ ዓይናለም በልምምድ ሜዳ ላይ ባጋጠማቸው ጉዳት በሲዳማ የጉዳት ዝርዝር ውስጥ የገቡ ተጫዋቾች ሲሆኑ በፋሲል ከነማ በኩል ምንም የጉዳት ዜና አልተሰማም።

የእርስ በእርስ ግንኙነት   

– ፋሲል ከነማ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ካደገበት 2009 ጀመሮ አራት ጊዜ ተገናኝተዋል። በእስካሁኖቹ ውጤቶችም ሲዳማ ቡና ሦስት ጊዜ በማሸነፍ የበላይ ነቱን ሲይዝ የመጨረሻው ግንኙነታቸው በፋሲል 2-1 አሸናፊነት የተጠናቀቀ ነበር። በአራቱ ጨዋታዎች ሲዳማ ቡና ስምንት ፋሲል ደግሞ ሦስት ግቦችን አስቆጥረዋል።

– በ2009 የውድድር ዓመት እንደዘንድሮው ሁሉ በሊጉ መክፈቻ የተገናኙበት የይርጋለሙ ጨዋታ በሲዳማ የ1-0 አሸናፊነት ሲጠናቀቅ ግቧን ያስቆጠረው ትርታዬ ደመቀ ነበር።

ዳኛ

– ኢንተርናሽናል ዳኛ ብሩክ የማነብርሀን ጨዋታውን በመሀል ዳኝነት ይመራዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ሲዳማ ቡና (4-3-3)

መሣይ አያኖ

ግሩም አሰፋ – ሰንዳይ ሙቱኩ – ግርማ በቀለ – ፈቱዲን ጀማል

ዳዊት ተፈራ – ዮሴፍ ዮሀንስ – አበባየው ዮሀንስ

አዲስ ግደይ – ፀጋዬ ባልቻ – ሀብታሙ ገዛሀኝ

ፋሲል ከነማ (4-3-3)

ሚኬል ሳማኬ

ሰዒድ ሁሴን – ከድር ኩሊባሊ – ያሬድ ባየህ – ፍፁም ከበደ

ያስር ሙገርዋ – መጣባቸው ሙሉ – ኤፍሬም ዓለሙ

አብዱርሀማን ሙባረክ – ኢዙ አዙካ – ሱራፌል ዳኛቸው


ማስታወቂያ
የኢትዮ ኤሌክትሪክ ስፖርት ክለብ የዋናው እግርኳስ ቡድን የሚያደርጋቸውን ጨዋታዎች የቪድዮ ቀረጻ እና የጨዋታ ትንተና የሚያደርግ ባለሙያ ይፈልጋል፡፡ ስለሆነም በዚህ ሙያ ላይ የተሰማሩ አካላት በስራው ላይ ያላቸውን የታደሰ ህጋዊ ፍቃድ በመያዝ ሜክሲኮ በሚገኘው የክለቡ ጽህፈት ቤት በአካል በመቅረብ የፍላጎት ማሳወቂያ እና የመወዳደርያ ሰነድ መውሰድ የምትችሉ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

ለተጨማሪ መረጃ – 0115-534949 ; 0115-532051

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ስፖርት ክለብ