ቫስ ፒንቶ ተሰናበቱ

ቅዱስ ጊዮርጊስ ፖርቹጋላዊ ዋና አሰልጣኙ ቫስ ፒንቶን ከኃላፊነት አንስቷል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ በ2010 የውድድር ዓመት መግቢያ ላይ በጤና እክል ምክንያት የተለዩትን ሆላንዳዊ አሰልጣኝ ማርቲን ኑይን ቦታ በአሰልጣኝ ቫስ ፒንቶ መተካቱ ይታወሳል። ክለቡ ከፖርቹጋላዊው አሰልጣኝ ጋር የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫን በማንሳት ቢጀምርም በተሳተፈባቸው ቀሪ ውድድሮች ግን የሚፈልገውን ውጤት ማሳካት አልቻለም። በሁለቱም የአፍሪካ ውድድሮች ያስመዘገበው ደካማ ውጤት ፕሪምየር ሊጉን ካለማሸነፉ ጋር ተደምሮ ዓመቱ ሲገባደድ ወደ 2011 የተዘዋወረው የኢትዮጵያ ዋንጫ ለአሰልጣኙ የመጨረሻ ዕድል እንደሚሆን ተገምቶ ነበር። ቡድኑ በኢትዮጵያ ዋንጫ እስከ ፍፃሜ ተጉዞ በመከላከያ መረታቱ ግን የአንድ ዓመት ውል ይቀራቸው የነበሩት የፖርቹጋላዊው አሰልጣኝ የፈረሰኞቹ ቤት ቆይታ መገባደጃ እንደደረሰ በእጅጉ ያመላከተ ነበር። ሆኖም የአሰልጣኝ ስንብቱ ሳይሰማ ቡድኑ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን መቀጠሉ የነገሩን መጨረሻ ተተባቂ አድርጎት ቆይቶ በመጨረሻ ዛሬ አሰልጣኝ ቫስ ፒንቶ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ መለያየታቸው ተረጋግጧል።

ከ1996 ጀምሮ ፊቱን ወደ ውጪ አሰልጣኞች ያዞረው ቅዱስ ጊዮርጊስ ዳግም ወደ ሀገር ውስጥ ይመለሳል ወይስ ሌላ የውጪ አሰልጣኝ ይቀጥራ የሚለው ጉዳይ በቀጣይ የሚጠበቅ ይሆናል። በ2010 የፕሪምየር ሊጉ የመጀመሪያ ዙር ሲጠናቀቅ ግማሽ የሚሆኑት ክለቦች አሰልጣኞቻቸውን ማሰናበታቸው ግርምትን የፈጠረ ሲሆን ዘንድሮ ደግሞ የስንብት ሂደቱ በሊጉ መክፈቻ ቀን መጀመሩ አስገራሚ ሆኗል።


ማስታወቂያ
የኢትዮ ኤሌክትሪክ ስፖርት ክለብ የዋናው እግርኳስ ቡድን የሚያደርጋቸውን ጨዋታዎች የቪድዮ ቀረጻ እና የጨዋታ ትንተና የሚያደርግ ባለሙያ ይፈልጋል፡፡ ስለሆነም በዚህ ሙያ ላይ የተሰማሩ አካላት በስራው ላይ ያላቸውን የታደሰ ህጋዊ ፍቃድ በመያዝ ሜክሲኮ በሚገኘው የክለቡ ጽህፈት ቤት በአካል በመቅረብ የፍላጎት ማሳወቂያ እና የመወዳደርያ ሰነድ መውሰድ የምትችሉ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

ለተጨማሪ መረጃ – 0115-534949 ; 0115-532051

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ስፖርት ክለብ