ሪፖርት | አዳማ ከተማ ሦስተኛ ተከታታይ ድሉን አስመዝግቧል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አስረኛ ሳምንት በሜዳው ድሬዳዋ ከተማን ያስተናገደው አዳማ ከተማ 1-0 በማሸነፍ ሶስተኛ ተከታታይ ድሉን አስመዝግቧል።

አዳማ ከተማዎች መከላከያን በሰፊ ጎል ልዩነት 5-1 ከረታው ቡድናቸው ምንም የተጫዋች ለውጥ ሳያደርጉ ወደ ሜዳ የገቡ ሲሆን ድሬዳዋ ከተማዎች በአንፃሩ ባሳለፍነው ሳምንት ባህር ዳር ከተማን ካሸነፈው ስብስባቸው በአጥቂ ስፍራ ላይ የሚጫወተው ኢታሙና ኬይሙኔን በተላለፈበት ቅጣት ምክንያት በሲላ አብዱላሂ በመቀየር ቀርበዋል።

የመጀመሪያው አጋማሽ ቀዝቃዛ እንቅስቃሴ የታየበት ነበር። በ4-2-3-1 አሰላለፍ የገቡት አዳማዎች ከመጀመሪያው ደቂቃ አንስቶ ኳስ መስርተው ለመጫወት ጥረት ያደርጉ ቢሆንም ድሬዎች የተጋጣሚያቸውን የአማካይ ክፍል ጥንካሬ ቀድመው የተረዱ በሚመስል መልኩ ኳስ በተጋጣሚያቸው እግር ስር ስትገባ በቁጥር በመብዛትና በፍጥነት በማስጣል ወደ ሶስተኛው የሜዳ ክፍል መድረስ እንዳይችሉ አድርገዋል። በዚህም ከቅጣት ምቶች ከሚደረጉ ሙከራዎች ውጪ የጠራ የግብ እድል ለመፍጠር ረጅም ደቂቃዎች ለመጠበቅ ተገደዋል። 

በመልሶ ማጥቃት የግብ እድል ለመፍጠር ሙከራ ያደረጉት ድሬዳዋች በ23ኛው እና 39ኛው ደቂቃ ሲላ አብዱላሂ የግብ ሙከራዎች አድርገው በግብ ጠባቂው ኦዶንካረመ ሲከሽፍባቸው በሜዳው የቀኝ ክፍል አዘንብለው የተጫወቱት አዳማዎች በበረከት፣ ቡልቻ እና ዳዋ አማካይነት በፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ለመግባት የቻሉባቸው አጋጣሚዎች ቢኖሩም ወደ ግብ ዕድልነት ለመቀየር ግን ሲቸገሩ ተስተውለዋል። 

በሁለተኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የተጫዋች ቅያሪ ያደረገው አዳማ ከተማ በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ከነዓን ማርክነህ በጨጓራ ህመም ምክንያት በፉአድ ሲራጅ ተክቶ ሲጀምር በዚህ አጋማሽ የመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች እንግዳዎቹ ድሬዎች በአዳማ ላየ ጫና መፍጠር ችለው ነበር። በ48ኛው ደቂቃ ላይ ሐብታሙ በግንባሩ የገጨውን ኳስ ሮበርት ያወጣበት እንዲሁም በ49ኛው ደቂቃ ላይ በድጋሚ ሐብታሙ ወልዴ ፍፁም ቅጣት ምት ውስጥ አክርሮ የመታው ኳስ በግቡ ቋሚ በከል የወጣበት መሪ ለመሆን የተቃረቡባቸው አጋጣሚዎች ነበሩ። ድሬዳዋዎች በጨዋታው ወደ አደጋ ክልል ለመጨረሻ ጊዜ ለማለት በሚያስችል መልኩ የቀረቡት በ58ኛው ደቂቃ ሲሆን የአዳማው ተከላካይ ቴዎድሮስ በቀለ በረጅም የተሻገረ ኳስ በእግሮቹ ማሀል ማለፏን ተከትሎ በቅርብ ርቀት የነበገው ሲላ ወደፊት ይዞ ቢጠጋም በድጋሚ ቴውድሮስ ኳሱን ማስጣል ችሏል። የድሬዳዋ አመራሮች ቴዎድሮስ ኳሱን ያስቀረበት መንገድ ትክክል አይደለም፤ ፍፁም ቅጣት ምትም ይገባን ነበር በሚል ቅሬታ ሲያሰሙም ተሰትውሏል። 

ከ53ኛው ደቂቃ ጀምሮ ወደፊት ተጭነው ለመጫወት ሙከራ ያደረጉት አዳማዎች የጥረታቸውን ያህል ደቂመዎች በገፉ ቁጥር ይበልጥ ጠጣረ የሆነው የድሬዳዋን የተከላካይ መስመር ለማስከፈት ሲቸገሩ ተስተውሏል። በ71ኛው ደቂቃ ላይ ሱሌይማን ሰሚድን በማስገባት እና ሁለቱ ሱሌይማኖች በመጠቀም በሚሻገሩ ኳሶች የግብ እድል ለመፍጠር የሞከሩት በ80 ደቂቃ በዚሁ ሒደት ጎል ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። ሱሌይማን ሰሚድ ያሻማውን ኳስ ነፃ አቋቋም ላይ የነበረው ሳንጋሬ ወደ ግብነት ለወጠው ተብሎ ሲጠበቅ በግንባሩ ገጭቶ የግቡን አናት ታካ ወጥታበታለች። 

በ85ኛው ደቂቃ ላይ ሱሌይማን ሰሚድ ያሻማውን ኳስ በጨዋታው ግብ ለማስቆጠር ያለውን የግል ጥረት በሙሉ ሲጠቀም የዋለው ዳዋ ሆቴሳ በግንባሩ በመግጨት የአዳማን የአሸናፊነት ጎል አስቆጥሯል። የሊጉ 7ኛ ጎሉን ያስቆጠረው ዳዋ የጨዋታዋን ወሳኝ ጎል ካስቆጠረ በኋላ ደስታውን ማልያውን በማውለቅ ገልጿል።

ከግቡ መቆጠር በኋላ የአቻነት ግብ ፍለጋ ወደፊት መጓዝ የጀመሩት ድሬዳዋች ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል። በጨዋታ መጠናቀቂ ደቂቃ ላይ ወሰኑ ማዜ በረጅሙ የተሻገረትን ኳስ ለማግኘት ጥረት ቢያድርግበት ቅፅበት ሮበርት ኦዶንካራ  ቀድሞ በመያዝ ወደ መሬት ሲወድቅ ተከትሎት በመውደቅ ሮበርትን በመማታቱ ግርግር ተፈጥሮ የነበረ ቢሆንም ግርግሩ ሳይባባስ የዕለቱ ዳኛ ለሁለቱም ተጫዋቾች እና ሚኪያስ ግርማ የማስጠንቀቂያ ካርድ በማሳየት ሊያረጋጉ ችለዋል። ጨዋታውም ተጨማሪ ጎልል ሳይሰተናግድበት በአዳማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ ከመጥፎ አጀማመሩ ያገገመው አዳማ ከተማ ሶስተኛ ተከታታይ ድሉን በማስመዝገብ ደረጃውን ወደ ስድስተኛ ከፍ ማድረግ ችሏል። ድሬዳዋ ደግሞ በ9 ነጥቦች 10ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *