የአሰልጣኞች አስተያየት | ቅዱስ ጊዮርጊስ 5-1 መከላከያ

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ቅዱስ ጊዮርጊስ መከላከያን ገጥሞ 5-1 ካሸነፈበት ጨዋታ በኋላ የሁለቱ ቡድን አሰልጣኞች በሚከተለው መልኩ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

“ይዘነው የገባነው የአዕምሮ ጥንካሬ፣ ታጋይነት እና አልሸነፍ ባይነት የሚደንቅ ነበር” ስቴዋርት ሀል – ቅዱስ ጊዮርጊስ 

” እግርኳስ አንዳንዴ የማይገመት ስፖርት ነው። ማክሰኞ 10 እድሎችን ፈጥረን ተሸነፍን። ዛሬ 8 ወይም 7 የሚሆኑ እድሎችን ፈጥረን 5 አስቆጠርን። እግርኳስ ሳቅ የሚያጭር ጨዋታ ነው። ትላንት ቁጭ ብለን ባለፈው ያመከንናቸውን እድሎች በተንቀሳቃሽ ምስል ስናይ ነበር። ተጨዋቾቼ ራሳቸው ያመከኗቸው እድሎች ሲያዩ ማመን አልቻሉም ነበር። ዛሬ ነገሮችን ለመለወጥ የነበራቸው መነሳሳት ጥሩ የሚባል ነው። ይዘነው የገባነው የአዕምሮ ጥንካሬ፣ ታጋይነት እና አልሸነፍ ባይነት የሚደንቅ ነበር። ተጨዋቼ ትንሽ ያልተገቡ ትችቶችን በዚህ ሳምንት ሲያስተናግዱ ነበር። የስራው አንድ አካል ቢሆንም ትንሽ ሚዛናዊ ያልሆነ ነው። ልጆቻችን ትንሽ ተበሳጭተው ስለነበር ዛሬ ምላሻቸውን ሰጥተዋል። ”


” የዛሬው ውሏችን ጥሩ አልነበረም” ሥዩም ከበደ – መከላከያ 

” በጨዋታው ዛሬ ቡድናችን ጥሩ አልነበረም፤ ጊዮርጊስ በልጦናል። እንደ አመጣጣችን እና እቅዳችን ፈታኝ ነገር እንደሚጠብቀን አውቀናል። እንዲያም ሆኖ ወደ ጨዋታው ልንደርስ ስንል እንደ ምንይሉ ወንድሙ አይነት አጥቂ መታመሙ ጉዳት አለው። ቢሆንም ዛሬ እንደ ቡድን ጥሩ አልነበርንም። በመከላከሉ ላይ የመከላከል ጥረት ቢያደርጉም አጥቂዎች እና አማካዮቹ  የተጋጣሚ ቡድንን ለማሸነፍ ያደረጉት ጥረት ደካማ ነበር። ለመጀመርያዎቹ ሁለቱ ጎሎች መቆጠር እንደ ግለሰብ የምንወቅሰው ባይኖርም የጎሎቹ መብዛት እያንዳንዱ በቦታው ኃላፊነቱን በአግባቡ ያለመወጣት ድክመት ነው። ግን እንዲህ ያለ የጎል ብዛት ይቆጠርብናል ባልልም እንደ ጨዋታቸው ጊዮርጊሶች ማሸነፋቸው ይገባቸዋል። ”

የፍፁም ገብረማርያም ቅያሪ 

” አንዳንዴ እያየህ ዝም የምትለው ነገር አለ። ፍፁም ጥሩ ተጫዋች ነው አምንበታለሁም። ነገር ግን የመጀመርያው አጋማሽ ላይ ያደረገው ነገሮች ሁሉ ጥሩ አልነበሩም። ከኳስም ያለ ኳስም የነበረው እንቅስቃሴ ቡድናችን ውስጥ የነበረው ሚና አናሳ የነበረ በመሆኑ ለመቀየር ተገደናል። ተቀይሮ የገባው ተጫዋች ጥሩ አቅም ያለው ከተስፋ ቡድን ያደገ ነው። ምንም እንኳን የዛሬው እንቅስቃሴው ባይሳካለትም። እንደ አሰልጣኝ በወቅቱ ያየህውን የመቀየር ግዴታ ይኖርብሀል። ካለቀ በኋላ እንዲህ የምናደርገው ቢሆን ልንል እንችላለን። የመጀመርያ ውሳኔያችን ግን ትክክል ነበር።”


በሁለት የሊግ ጨዋታዎች አስር ጎል ስለማስተናገዳቸው

” የመጀመርያው የአዳማ ጨዋታ ብዙም አልተከፋሁበትም፤ ምክንያቱም ሁለት ተጫዋቾች በቀይ ካርድ ወጥተውብን ነበር። የዛሬው ግን እኔም ብቻ ሳይሆን ተጫዋቹም የሚጠብቁት አይደለም የ። ከምንም በላይ ግን የመጀመርያዎቹ  ሁለቱ የተቆጠሩ ጎሎች የእኛ ድክመት አለበት። ከዛ ስሜት ተነስተው ነው የጊዮርጊስ ደጋፊዎቹም ተጫዋቾቹም በስነ ልቦና የተሻለ በመሆን የቻሉት። በአጠቃላይ የዛሬው ውላችን ጥሩ አልነበረም።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *