ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ኢትዮጵያ ቡና ከ ሀዋሳ ከተማ

የዛሬ የመጨረሻው የቅድመ ዳሰሳችን ትኩረት የሚሆነው ኢትዮጵያ ቡና እና ሀዋሳ ከተማ የሚያደርጉት ተጠባቂ ጨዋታ ይሆናል።

በደረጃ ሰንጠረዡ አንደኛ እና ሁለተኛ ላይ የሚገኙት ኢትዮጵያ ቡና እና ሀዋሳ ከተማ ነገ 11፡00 ላይ እጅግ ተጠባቂ በሆነ ጨዋታ አዲስ አበባ ስታድየም ላይ ይገናኛሉ። በመቐለ ያልተጠበቀ ሽንፈት ያስተናገደው ሀዋሳ ከተማ የሊጉን መሪነት መረከብ የሚችልበት ዕድል አምልጦታል። የነገው ጨዋታ ግን ከበላዩ ካለው ቡድን ጋር የሚደረግ በመሆኑ ይህንን ዕድል በድጋሜ ያገኘዋል። ሽንፈት ከገጠመው ደግሞ ሦስት ደረጃዎችን ለመንሸራተት ሊገደድ ይችላል። ከሲዳማ ጋር ሦስት ነጥቦችን ለማግኘት ተቃርቦ በመጨረሻ ሰዓት አቻ ለመለያየት የተገደደው ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ መሪነቱን ለማስፋት ሀዋሳን ማሸነፍ ይጠበቅበታል። ከሲዳማው ጨዋታ አስቀድሞ ተከታታይ ድሎችን ወዳገኘበት ሜዳው መመለሱም እንደሚያግዘው ይገመታል። ጨዋታውም አምና በመጨረሻ ሰዓት በተቆጠሩ ግቦች 1-1 ተጠናቆ የስሜት መዘበራረቅን እንዳስመለከተን ጨዋታ ጠንካራ ፉክክር እንደሚያስተናግድ ይጠበቃል።          

ኢትዮጵያ ቡና በሲዳማው ጨዋታ ጉዳት የገጠማቸው አህመድ ረሺድ እና ሱለይማኑ ሎክዋን እንዲሁም የረጅም ጊዜ ጉዳት ላይ የቆዩት አማኑኤል ዮሀንስ እና አስራት ቱንጆ  አገግመው እንደተመለሱለት ተሰምቷል። በሀዋሳ በኩል ግን ብቸኛው በጉዳት ከዚህ ጨዋታ ውጪ የሚሆነው ደስታ ዮሀንስ ብቻ ነው። 

በነገው ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና በቅብብሎች ላይ የተመሰረተ እንዲሁም ፈጣን ሽግግርን በሚጠይቅ አጨዋወት ሀዋሳ ከተማ ደግሞ ከመስመር እና ከጥልቅ አማካይ ክፍል በሚነሱ ረጃጅም ኳሶች የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር በማሰብ እንደሚገቡ ይገመታል። ሆኖም ሁለቱም ሊቸገሩ የሙችሉባቸው ሁኔታዎች ይኖራሉ። ሀዋሳ ደስታ የሃንስን ማጣቱ እንደመቐለው ጨዋታ ሁሉ የግራ መስመር የመከላከል ክፍሉን ለጥቃት የማጋለጥ ዕድሉ ከመስፋቱ በተጨማሪ ከደስታ የሚያገኛቸው ለግብ የሚሆኑ ኳሶችንም ያጣል። በኢትዮጵያ ቡና በኩል ደግሞ የተከላካይ መስመሩ በጫናዎች ውስጥ ሲፈተን እና ይቅብብል ስህተቶችን ሲሰራ የሚታይ መሆኑ ለሀዋሳ ተደጋጋሚ ተሻጋሪ ኳሶች የሚሰጠውን ምላሽ ተጠባቂ አድርጎታል። ነገር ግን ኢትዮጵያ ቡና ጉዳት ላይ የነበሩት ተጫዋቾች መመለስ መሀል ላይ እያጣ ያለውን ጉልበት የሚመልስለት እንዲሁም እንደነካሉሻ አልሀሰን ያሉ አማካዮቹም ይበልጥ ለጎሉ ቀርበው እንዲጫወቱ የሚያስችለውም ነው።

ዳኛ

– ኢንተርናሽናል ዳኛ ኃይለየሱስ ባዘዘው ይህን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት የመምራት ኃላፊነት ተሰጥቷታል። አርቢትሩ በዳኘባቸው ሦስት ጨዋታዎች ሦስት የማስጠንቀቂያ ካርዶች እና አንድ የፍፁም ቅጣት ምት ሰጥቷል።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

–  ግቦች የማያጡት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ከ1996 ጀምሮ በተገናኙባቸው አጋጣሚዎች ሁሉ ቢያንስ አንድ ጎል ሲያስመለክተን ቆይቷል። የኢትዮጽያ ፕሪሚየር ሊግ በ1990 በአዲስ ፎርማት ከተጀመረ አንስቶ እስካሁን ድረስ እየተካፈሉ ከሚገኙ ብቸኛዎቹ ሁለቱ ክለቦች መሀከል የሆኑት ኢትዮጵያ ቡና እና ሀዋሳ ከተማ የእርስ በእርስ ውጤታቸውም በመሀላቸው ያለውን የፉክክር ሚዛናዊነት የሚያሳይ ነው።

– ሊጉ በአዲስ ፎርማት ከተጀመረበት 1990 ጅምሮ ሳይወርዱ የቆዩት ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን 40 ጊዜ ሲገናኙ በ15 አጋጣሚዎች ተለያይተዋል። ኢትዮጵያ ቡና 13 ሀዋሳ ደግሞ 12 ጊዜ ድል ቀንቷቸዋል። በነዚህ ጊዜያት ኢትዮጵያ ቡና 51 ጊዜ ኳስ እና መረብን ሲያገናኝ ሀዋሳ ከተማም ሶስት የፎርፌ ግቦችን ጨምሮ 43 ግቦችን ማስመዝገብ ችሏል።

– ኢትዮጵያ ቡና ከሰበሰባቸው 19 ነጥቦች 13ቱን አዲስ አበባ ስታድየም ላይ ያሳካቸው ሲሆን እስካሁንም በሜዳው ሽንፈት አልገጠመውም።

– ሀዋሳ ከተማ ሦስት ጊዜ ከሜዳው ሲወጣ ሁለት ነጥቦችን አሳክቷል። ግብ ማስቆጠር የቻለውም በፋሲል 3-1 በተሸነፈበት ጨዋታ ብቻ ነው። 

ግምታዊ አሰላለፍ

ኢትዮጵያ ቡና (3-4-2-1)

ዋቴንጋ ኢስማ

ተመስገን ካስትሮ – ክሪዝስቶም ንታምቢ – ቶማስ ስምረቱ

          
አህመድ ረሺድ – ካሉሻ አልሀሰን  – ሳምሶን ጥላሁን – እያሱ ታምሩ

                 
ሚኪያስ መኮንን  – አቡበከር ነስሩ

 ሱለይማን ሎክዋ

                                                                                         
ሀዋሳ ከተማ (3-4-1-2) 

ሶሆሆ ሜንሳህ 

 አዲስዓለም ተስፋዬ – ላውረንስ ላርቴ – መሣይ ጳውሎስ

ዳንኤል ደርቤ –ኄኖክ ድልቢ– ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን – ብሩክ በየነ

ታፈሰ ሰለሞን 

አዳነ ግርማ – እስራኤል እሸቱ

                                                      

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *