የአሰልጣኞች አስተያየት | ሲዳማ ቡና 2-0 መከላከያ

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 12ኛ ሳምንት ሲዳማ ቡና መከላከያን በሜዳው ጋብዞ 2-0 በሆነ ውጤት ከረታ በኃላ የሁለቱ ክለብ አሰልጣኞች አስተያየታቸውን እንዲህ ሰጥተውናል፡፡

“የምንሰራቸውን ስህተቶች እያረምን አጨዋወታችንን በዚህ መልኩ እንቀጥላለን” ዘርዓይ ሙሉ – ሲዳማ ቡና

ስለ ጨዋታው

“ቡድናችን አሁን ላይ ጥሩ ለውጥ ነው የሚታይበት። አልፎ አልፎ የመከላከል ችግር ይታይብን ነበር። ዛሬ ሙሉ በሙሉ ያ ነገር ተቀርፏል፡፡ ከዛ ውጭ አሁንም ያገኘናቸውን ከመጠቀም አንፃር የሚቀረን ነገር አለ፡፡ ብዙ ጊዜ ጎል ጋር እንደርሳለን፤ አንድ ለአንድ ከግብ ጠባቂ ጋር እየተገናኘንም እናመክናለን። እዚህ ላይ ጠንክሮ መስራት ነው። የምንሰራቸውን ስህተቶች እያረምን አጨዋወታችንን በዚህ መልኩ እንቀጥላለን፡፡

ዮሴፍ፣ ግሩም እና መሣይ በዛሬው ጨዋታ ያለመሰለፋቸው ምክንያት

“ክፍተት ተፈጥሮ ነው። ያ ደግሞ በቀላሉ የሚስተካከል ነው። ከሜዳችን ውጭ ጠንካራ ጨዋታ ስላለን ተጫዋቾቹን ከማሳረፍ አንፃር ነው። ተጫዋቾቹ ከቡድኑ ጋር ነው ያሉት። የሚፈታ ችግር ነው፤ የተለየ ነገር አልነበረም፡፡

“የኛን ቡድን በአጠቃላይ ያወረደው የመጀመሪያው ጎል ነው” ሥዩም ከበደ – መከላከያ

ስለ ጨዋታው እና ቡድኑ እያጣ ስላለው ውጤት

“የኛ ብዙ ነገር እየተበላሸ እየተበላሸ የሄደው ከአዳማ ከነበረን ጨዋታ ጀምሮ ነው። በጨዋታው የነበረው እንቅስቃሴ ላይ ሁለት ተጫዋቾች በቀይ ወጥተውብን ነበር። ከጊዮርጊስም ከሸረም ጋር ስንጫወት ወደ አምስት ተጫዋቾች በቀይ ካርድ እና ህመም አላሰለፍንም ነበር፡፡ በዛሬው ጨዋታ ደግሞ ዳዊት እስጢፋኖስ እና ተመስገንን የመሳሰሉ ተጫዋቾች አልነበሩም። 

“በዛሬው ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ በተለይ ሲዳማ ቡናዎች ተጭኖ በመጫወት ወደ ጎል የሚያደርጉት ሙከራ መልካም ነበር፡፡ እኛ ደግሞ በተነጋገርነው መሠረት ይህን መቆጣጠር አልቻልንም፤ ይህ ነው ጥፋቱ። በሁለተኛው አጋማሽ የኛ ተጫዋቾች የተሻሉ ነበሩ። መሻላችን ግን በግብ አልታጀበም፤ አልተሳካልንም፡፡ ለቀጣዩ ከዚህ ተነስተን ማሻሻል ነው፡፡ ”

ከዳኛው ጋር ውዝግብ ስለፈጠሩበት የአዲስ ግደይ ጎል

“የኛን ቡድን በአጠቃላይ ያወረደው የመጀመሪያው ጎል ነው። መቶ ብቻ ሳይሆን ሁለት መቶ ፐርሰንት ከጨዋታ ውጪ ነው። እኔ በመሠረቱ ከዳኛ ጋር ክርክር ውስጥ አልገባም። የምቀበላቸው ብዙ ነገሮች ስላሉ፤ ይህ ግን በግልፅ ፊት ለፊት የሚታይ ከጨዋታ ውጭ አቋቋም ላይ ሆኖ ተቀብሎ ነው ያገባው። ዳኞች ይህን እያዩ የሚማሩበት ነገር ቢመቻች ጥሩ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *