ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | አዳማ ከተማ  ከ ወልዋሎ ዓ/ዩ

ከነገ ሦስት መርሐ ግብሮች መካከል አዳማ ከተማ እና ወልዋሎ ዓ/ዩ በሚገናኙበት ጨዋታ ዙሪያ ተከታዮቹን ነጥቦች አንስተናል።

ሰባተኛ እና ስምንተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ወልዋሎ ዓ/ዩ እና አዳማ ከተማ ነገ 09፡00 ላይ በአዳማው አበበ ቢቂላ ስታድየም የ12ኛ ሳምንት ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። እንዳለፉት ዓመታት ሁሉ ኮስታራ ተፎካካሪ መሆን የተሳነው የሚመስለው አዳማ ከተማ ሦስት ጨዋታዎችን በተከታታይ አሸንፎ ደካማ አጀማመሩን መቀልበስ ቢችልም ደደቢትን ከገጠመበት ጨዋታ ሙሉ ሦስት ነጥብ አለማሳካቱ ከሰንጠረዡ ወገብ ከፍ እንዳይል አድርጎታል። በርግጥ ክለቡ ከነገው ውጪ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ ያለው መሆኑ ይበልጥ ለመሻሻል የሚያስችለው ነው ፤ ወልዋሎን መርታት ከቻለ ደግሞ መሪዎቹን በቅርብ ርቀት የሚከተል ይሆናል። ሁሉንም ጨዋታዎቻቸውን ያደረጉት ወልዋሎዎች ከተከታታይ የአቻ ውጤቶች በኋላ ባህር ዳርን ማሸነፍ መቻላቸው ወደ ሰባተኝነት አምጥቷቸዋል። ደቡብ ፖሊስ እና መከላከያን ካሸነፉባቸው ሳምንታት በኋላ መድገም ያልቻሉትን ተከታታይ ድል ነገ ማሳካት ከቻሉም ራሳቸውን ወደ ላይኛው ፉክክር ከቀረቡ ክለቦች መካከል ያገኙታል። 

ባለሜዳዎቹ አዳማ ከተማዎች ከነዓን ማርክነህ ፣ ኤፍሬም ዘካሪያስ ፣ ሰራፌል ጌታቸው እና አንዳርጋቸው ይላቅን በጉዳት ምክንያት በነገው ጨዋታ አይጠቀሙም። በተለይም የከነዓን አሁንም ወደ ሜዳ አለመመለስ የቡድኑን የፈጠራ እና የማጥቃት አማራጮች የሚያሳንስ በመሆኑ የቁመተ ረጅሙ አማካይ ቦታ በአግባቡ መሸፈኑን ማረጋገጥ የአዳማዎች ዋነኛ የቤት ስራ ይሆናል። በወልዋሎ  ዓዲግራት በኩልም ከባህርዳር ጋር በነበረው ጨዋታ በጉዳት ተቀይሮ የወጣው የፊት አጥቂው  ሬችሞንድ አዶንጎ እንዲሁም የረጅም ጊዜ ጉዳት ላይ የሚገኙት ዋለልኝ ገብሬ እና ኤፍሬም ኃይለማርያም ነገም በጉዳት አይሰለፉም። ሆኖም ለአሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም እፎይታ የሚሰጠው እና የተጫዋቾች ምርጫቸውን የሚያሰፋላቸው ዜና የዳንኤል አድሓኖም እና አስራት መገርሳ ከጉዳት እና ቅጣት መልስ ለጨዋታው ዝግጁ መሆናቸው ነው። 

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ሁለቱ በድኖች የተገናኙባቸው ሁለት የሊጉ ጨዋታዎች በመሸናነፍ የተጠናቀቁ ነበሩ። በመጀመሪያው ዙር አዳማ ሜዳው ላይ 3-0 ሲያሸንፍ በሁለተኛው ወልዋሎ የ 1-0 ድል ቀንቶታል። 

– አዳማ ከተማ በሜዳው ካደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች የመጨረሻዎቹን ሦስቱን በድል ሲወጣ አንዴ ተሸንፎ አንዴ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል።

– ስድስት ጊዜ ከሜዳቸው የወጡት ወልዋሎዎች ሁለት አቻ ፣ ሁለት ድል እና ሁለት ሽንፈት ገጥሞቸዋል።

ዳኛ

– ከአስራ አንዱ የሊጉ ሳምንታት በአራቱ የመዳኘት ዕድሉን ያገኘው ተፈሪ አለባቸው በዚህ ጨዋታ ላይ በመሀል ዳኝነት ተመድቧል።

ግምታዊ አሰላለፍ

አዳማ ከተማ (4-2-3-1)

ሮበርት ኦዶንካራ

ሱለይማን ሰሚድ – ምኞት ደበበ – ተስፋዬ በቀለ – ቴዎድሮስ በቀለ

ዐመለ ሚልኪያስ – ኢስማኤል ሳንጋሪ 

ቡልቻ ሹራ – አዲስ ህንፃ – በረከት ደስታ

ዳዋ ሁቴሳ

              
ወልዋሎ ዓ/ዩ (4-3-3)

አብዱልዓዚዝ ኬይታ

እንየው ካሳሁን –  ደስታ ደሙ – ቢኒያም ሲራጅ – ብርሀኑ ቦጋለ

ብርሀኑ አሻሞ – አስራት መገርሳ – አፈወርቅ ኃይሉ

 አብዱሀማን ፉሰይኒ – ፕሪንስ ሰቨሪንሆ – ኤፍሬም አሻሞ

                                                                        

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *