ሪፖርት | መቐለ 70 እንደርታ ቡናን በማሸነፍ ሶስተኛ ተከታታይ ድሉን አስመዘገበ

በ12ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ትግራይ ስታድየም ላይ ኢትዮጵያ ቡናን ያስተናገደው መቐለ 70 እንደርታ 1-0 በማሸነፍ ሦስተኛ ተከታታይ ድሉን አስመዝግቧል።

ባለሜዳዎቹ “ምዓም አናብስት” በአስረኛው ሳምንት ሀዋሳን ከሜዳ ውጪ ካሸነፈው ስብስባቸው ቢያድግልኝ ኤልያስን በዮናስ ገረመው ብቻ በመተካት ሲገቡ እንግዳዎቹ ኢትዮጵያ ቡናዎች በበኩሉላቸው 11ኛው ሳምንት በተመሳሳይ ሀዋሳን ካሸነፉበት ስብስብ ቶማስ ስምረቱ፣ ሱሌይማን ሉክዋ እና የኋላሸት ፍቃዱን በማሳረፍ በወንድይፍራው ጌታሁን፣ አቡበከር ናስር እና አማኑኤል ዮሃንስ ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል።

የስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ርስቱ ይርዳው፣ የእግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ ጅራ እና የኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት አሸብር ወልደጊዮርጊስ በክብር እንግድነት ተገኝተው ባስጀመሩት ጨዋታ በመጀመርያዎቹ አምስት ደቂቃዎች ኢትዮጵያ ቡናዎች ጫና ፈጥረው ሲጫወቱ ሶስት እጅግ ለጎል የቀረቡ ዕድሎችንም አምክነዋል። በተለይም አቡበከር ወደ መቐለ ሳጥን ውስጥ በጥሩ ሁኔታ ይዞ የገባውን ኳስ መትቶ አሌክስ ተሰማ ተደርቦ ሲያወጣው ከግቡ ቅርብ ርቀት ነፃ አቋቋም የነበረው ካሉሻ አልሃሰን በማይታመን መልኩ ያመከነው ዕድል እና። አቡበበር ከሳጥኑ ግራ ጠርዝ በጥሩ ሁኔታ አሻግሮ አልሃሰን ካሉሻ ከመምታቱ በፊት አንተነህ ገ/ክርስቶስ ያወጣው ኳስ ይጠቀሳሉ።


በሶስት ተከላካዮች የተጫወቱት ኢትዮጵያ ቡናዎች በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ብልጫ ወስደው ተጫውተው ያለቀላቸው የግብ ዕድሎች ቢፈጥሩም በቀረው የጨዋታው ክፍለ ጊዜ ግን እንደቡድን የተደራጀ እንቅስቃሴ ማድረግ ያልቻሉበት ነበር። በተለይም በመሃል ሜዳ የተሰለፉት አማኑኤል ዮሐንስ፣ አልሃሰን ካሉሻ እና ሳምሶን ጥላሁን በቡድኑ መዋቅር ውስጥ የነበራቸው ሚና የተዘበራረቀ እና ያልተናበበ ነበር።

ወደ ጨዋታው ቅኝት ዘግይተው የገቡት እና እጅግ በርካታ ዕድሎች የፈጠሩት መቐለዎችም በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ኳስ ሲያጣ ወደ አምስት ተከላካዮች የሚቀየረውን የቡና የመከላከል አደረጃጀት ሰብረው ለመግባት ቢቸገሩም ቀሰ በቀስ በቀኝ መስመር ባደላ የማጥቃት እንቅስቃሴ በርካታ የግብ ዕድሎች ፈጥሯል። አማኑኤል ገ/ሚካኤል እና ያሬድ ከበደ በጥሩ ቅብብል ሄደው ያሬድ የቡና ሳጥን ውስጥ ብቻውን ተነጥሎ ለነበረው ሓይደር ሸረፋ አቀብሎት አማካዩ በማይታመን መልኩ ያመከነው ሙከራ እና አንተነህ ገ/ክርስቶስ ከቅጣት ምት መቶት ዋቴንጋ ኢስማ ያዳነው ይጠቀሳሉ። በጨዋታው የመጀመርያ ተሰላፊነት ዕድል ሳያገኝ የቆየው ዮናስ ገረመው በግሉ ያደረገው እንቅስቃሴ ድንቅ ነበር። በተለይም በመስመሮች መካከል የነበረው እንቅስቃሴ እና ከቡድን ጓደኞቹ የፈጠረው ተግባቦት በጥሩ ጎኑ የሚነሳ ነው።


በጨዋታው በመስመር በሚደረገው ፈጣን የማጥቃት ሽግግር እና በመልሶ ማጥቃት ግብ ለማግኘት ተጭነው ሲጫወቱ የታዩት መቐለዎች በመጀመርያው አጋማሽ መጨረሻ ደቂቃዎች በሁለት አጋጣሚዎች ዮናስ ገረመው እና ያሬድ ከበደ  ሙከራዎች ቢያደርጉም ሁለቱም ሙከራዎች በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ተመስገን ካስትሮ ግብ ከመሆን ተርፈዋል። በ36ኛው ደቂቃ ላይ ግን በቡና የግብ ክልል ኳስ በእጅ በመነካቱ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት አማኑኤል ገብረሚካኤል አስጥቆሮ ቡድኑ እንዲመራ አስችሏል። ከግቡ በኃላ ያሬድ ከበደ በጥሩ ሁኔታ መቶ  ዋቴንጋ ኢስማ በድንቅ  ብቃት ያዳነው የግብ ዕድልም በመቐለዎች በኩል የሚጠቀስ ሙከራ ነው።

በአንፃራዊነት ከመጀመርያው አጋማሽ በተሻለ የተቀራረበ ፉክክር የታየበት ሁለተኛው አጋማሽ በባለሜዳዎቹ መቐለዎች የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ቢቀጥልም ኢትዮጵያ ቡናዎች ከመጀመርያው አጋማሽ የተሻለ የግብ ዕድሎች የፈጠሩበት ነበር። አጋማሹ ከተጀመረ በኃላ ብዙም ሳይቆዩ የተጫዋቾች ከውጥ ያደረጉት ቡናዎች ተቀይሮ በገባው ቃልኪዳን ዘላለም ሁለት የግብ አጋጣሚ ሲያገኙ በተለይም ተጫዋቹ ከመስመር የተሻገረችለትን ኳስ መትቶ አሌክስ ተሰማ ተደርቦ ያወጣት ኢትዮጽያ ቡናዎችን አቻ ለማድረግ የተቃረበች ሙከራ ነበረች።


በጨዋታው የኳስ ቁጥጥር ብልጫ የወሰዱት መቐለዎች እንደ መጀመርያው አጋማሽ ቶሎ ቶሎ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ባይደርሱም የጎል ብልጫቸው ወደ ሁለት ከፍ የሚያደርጉባቸው ዕድሎች መፍጠር ችለው ነበር። አንተነህ ገ/ክርስቶስ ከሚካኤል ደስታ በግሩም ሁኔታ የተላከችለት ኳስ ተጠቅሞ ያደረጋት ሙከራ እና አማኑኤል ገ/ሚካኤል ከዋቴንጋ ኢስማ ጋር ተገናኝቶ ግብ ጠባቂው በጥሩ ብቃት ያወጣት ኳስ የሚጠቀሱ ናቸው።

በመጨረሻዎቹ አራት ተጨማሪ ደቂቃዎች ተጭነው የተጫወቱት ቡናማዎቹ በመጨረሻ ደቂቃ አቻ ለመሆን ተቃርበው ነበር። ቃልኪዳን በጥሩ ሁኔታ ወደ ውስጥ ገብቶ አክርሮ የመታውን ፍሊፕ ኦቮኖ ሲመልሰው ከግቡ ፊት ለፊት የነበረው አማኑኤል ዮሐንስ በድጋሚ ወደ ግብ ቢልከውም ግብ ጠባቂው አድኖታል። ጨዋታውም በመቐለ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

የዛሬውን ውጤት ተከትሎ ባለሜዳው መቐለ 70 እንደርታ ተከታታይ ሶስተኛ ድል አስመዝግቦ ወደ መሪዎቹ ሲጠጋ የሊጉ መሪ ኢትዮጽያ ቡና ከተከታዮቹ የነበረውን ልዩነት ማስጠበቅ ሳይችል ቀርቷል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *