የአሰልጣኞች አስተያየት | ቅዱስ ጊዮርጊስ 2-0 ደደቢት

ከ11፡00 ጀምሮ በአዲስ አበባ ስታድየም በተደረገው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ደደቢት የ12ኛ ሳምንት ጨዋታ ጊዮርጊስ 2-0 ማሸነፍ ችሏል። ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላም የክለቦቹ አሰልጣኞች አስተያየቶቻቸውን ሰጥተዋል።

” ሃምሳ ሃምሳ የሆነ እንቅስቃሴ ቢታይም ሦስቱን ነጥቦች በማግኘታችን ደስ ተሰኝቻለው። ” ስትዋርት ሀል – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ስለጨዋታው

” አንዳንዴ ተጫዋቾችህ ሜዳ ላይ ካለው ተጋጣሚ ጋር ሳይሆን ከሊጉ ሰንጠረዥ ጋር ነው የሚጫወቱት ፤ ከታች ካለ በድን ጋር ሲጫወቱ ነገሮች ቀላል የሚሆኑ ይመስላቸዋል። ያ ሲሆን እንደሌላው ጊዜ ጠንክረው አይጫወቱም ፤ የጨዋታ ዕቅዱንም በትኩረት አይተገብሩም። በትክክል ስንጫወት በጣም ጥሩ እግር ኳስን እናሳያለን የግብ ዕድሎችንም በብዛት እንፈጥራለን። ሆኖም በብዛት በጥሩ ሁኔታ አልተጫወትንም። ሃምሳ ሃምሳ የሆነ እንቅስቃሴ ቢታይም ሦስቱን ነጥቦች በማግኘታችን ደስ ተሰኝቻለው። ”

ስለተሳቱ ኳሶች 

” ከማግባታችን በፊት ሦስት ጥሩ የግብ ዕድሎችን አምክነናል። ተጫዋቾች ሰዎች ናቸው ፤ ሮቦት አይደሉም።  ሆን ብለው አይስቱም። አንዳንዴ የተሳሳተ ውሳኔ ያሳልፋሉ በሌላ አጋጣሚ ደግሞ የቴክኒክ ስህተት ሊሰሩ ይችላሉ። ማድረግ ያለብን ግን ደጋግመን የግብ ዕድሎችን መፍጠር ነው። ሁሌም አንድ ስንስት ሌላ ዕድል እንደምናገኝ ማሰብ እና ለማስቆጠር መሞከር አለብን።  ደግሞ የሳትናቸው ኳሶች ቢኖሩም ሁለት ምርጥ ጎሎችን አግኝተናል። የሣላ ቅጣት ምትም ሆነ የአቤል ጎል ድንቅ ነበሩ። ”


” እንደቡድን ጥሩ ጨዋታ ነበር ያደረግነው” ኤልያስ ኢብራሂም – ደደቢት

ስለጨዋታው

” ቡድናችን ከጨዋታ ወደ ጨዋታ መሻሻሎችን እያሳየ ነው። ወደዚህ ስንመጣ በተወሰነ መልኩ ነጥብ ይዘን ለመሄድ አስበን ነው የመጣነው። ከዕረፍት በፊት እና በኋላ የነበረው እንቅስቃሴ ግን የተለያየ ነው የሆነብን። ከዕረፍት በፊት ኳስ ይዘን ብልጫ ወስደን ለመጫወት ሞክረናል ፤ የጎል አጋጣሚዎችንም መፍጠር ችለናል። ግን ዳኞች ላይ ተመሳሳይ ስህተቶች ሲፈጠሩ እያየን ነው። ሳምንትም ተመሳሳይ ስህተት ነበር ዛሬም ጎል የሚሆን ኳስ ተበላሽቶብን ጥፋት ተሰራው ተጫዋች በቀይ መውጣት ነበረበት። በአጠቃላይ ግን ከዕረፍት በፊት የተሻለ መንቀሳቀስ ችለን ነበር። ከዕረፍት በኋላ ግን ልጆች እንደመሆናቸውም መዘናጋት ነበር። ጎልም የተቆጠረብን በዛ መልኩ ነበር። በአጠቃላይ ስናየው ግን እንደቡድን ጥሩ ጨዋታ ነበር ያደረግነው። “

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *