U-20 ምድብ ሀ | ቅዱስ ጊዮርጊስ በመሪነቱ ሲቀጥል ሀዋሳ፣ መከላከያ እና ጥሩነሽ አሸንፈዋል

የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ ምድብ ሀ 7ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ሲካሄዱ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ ከሜዳቸው ውጪ፤ ሀዋሳ ከተማ እና መከላከያ በሜዳቸው አሸንፈዋል።

ሀዋሳ ላይ ተጠባቂ በነበረው ጨዋታ ሀዋሳ ከተማ ሁለት ጊዜ ከመመራት ተነስቶ ኢትዮጵያ ቡናን 3-2 በሆነ ውጤት ረቷል፡፡ እጅጉን ማራኪ የሆነ የቡድን እንቅስቃሴ በታየበትን ጨዋታ በርከት ያሉ ተመልካቾች የተከታተሉት ሲሆን በግል ነጥረው የወጡ ተጫዋቾችን የተስተዋሉበት እና ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴን ያየንበት ነበር፡፡

የሀዋሳው ምንተስኖት እንድሪያስ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ሁለት ጊዜ ሙከራ አድርጎ የቡናማዎቹ ግብ ጠባቂ ዳዊት ባህሩ ሲያመክናቸው በሂደት የመሀል ሜዳ የሀዋሳን ድክመት የተመለከቱትን ኢትዮጵያ ቡናዎች ብልጫን በመውሰድ ጥሩ ዕድሎችን ሲፈጥሩ ታይቷል፡፡ በተለይ በየነ ባንጃ ወደ መስመር እየወጣ እና ወደ ውስጥ ከአማካዮቹ ጋር በጥልቀት በመግባት ለአጥቂዎች ወርቃማ ዕድሎችን ፈጥሯል፡፡ 10ኛ ደቂቃ ላይም በየነ በቀኝ በኩል በዚሁ ሂደት የፈጠረውን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ገዛኸኝ ደሳለኝ ወደግብነት ለውጦ ቡናማዎቹን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል፡፡

ከግቧ በኃላ በፍጥነት ወደ ማጥቃት የተሸጋገሩት ሀዋሳዎች በተደጋጋሚ በመስፍን ታፈሰ ያለቀላቸውን በርካታ ኳሶች በቀላሉ ከግቡ ጋር እየተገናኘ ሲያመክን ውሏል፡፡ ሆኖም በመጨረሻ 33ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር ታምራት ንጉሴ ያሻገረለትን ኳስ የቡና ተከላካይ እና ግብ ጠባቂን ስህተት ተመልክቶ በግንባር በመግጨት ግሩም ግብ አስቆጥሮ አቻ ማድረግ ችሏል፡፡

ከእረፍት መልስ 46ኛው ደቂቃ መስፍን ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ያመከናት የሁለተኛው አጋማሽ ቀዳሚዋ ሙከራ ነበረች፡፡ 59ኛው ደቂቃ ላይ መስፍን ታፈሰ በግብ ጠባቂው ግልፅ የማግባት ዕድል ሲያመክን በ64ኛው ደቂቃ ቡናዎች በቅብብሎሽ ወደ ሀዋሳ ግብ ክልል ደርሰው ኬቲካ ጅማ የግል ብቃቱን አክሎ ወደ ሳጥን ሲገባ የሀዋሳው ግብ ጠባቂ አላዛር ማርቆስ በሳጥን ውስጥ በመጥለፉ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ፉዓድ ነስሩ ወደ ግብነት በመለወጥ ዳግም ኢትዮጵያ ቡና ወደ 2-1 መሪነት አሸጋግሯል፡፡

78ኛው ደቂቃ ላይ በዛብህ ካቲቦ የቡና ተከላካዮችን ስህተት ተመልክቶ ወደ ፊት የላካትን ኳስ መስፍን ታፈሰ በግንባሩ በማስቆጠር ሀዋሳ 2-2 እንዲሆን አስችሏል፡፡ ኢትዮጵያ ቡናዎች በ81ኛው ኬቲካ ጅማ ያገኛትን ኳስ በቀጥታ መትቶ ብረት ከመለሰት ውጪ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በሀዋሳ ብልጫ ተወስዶባቸዋል፡፡ በተጨማሪው አምስት ደቂቃ 90+3ኛው ላይ ታምራት ንጉሴ በግራ በኩል በረጅሙ ወደ ግብ የላካትን ኳስ ተቀይሮ በመግባት በሜዳ ላይ አምስት ደቂቃ ብቻ የቆየው ሙሉቀን ታደሰ ወደ ግብነት ለውጦ ሀዋሳን አሸናፊ አድርጓል። ጨዋታውም በሀዋሳዎች 3-2 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

ሁለት ጎሎች በማስቆጠር ለሀዋሳ ድል ከፍተኛ ሚና የተወጣው መስፍን ታፈሰ

በሌሎች የምድቡ ጨዋታዎች ወደ ይርጋለም ያቀናው ቅዱስ ጊዮርጊስ ባለሜዳው ሲዳማ ቡናን 1-0 በማሸነፍ በመሪነቱ ሲቀጥል መከላከያ ረፋድ ላይ በሜዳው አካዳሚን ገጥሞ 4-0 አሸንፏል። ጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ ከሜዳው ውጪ ድሬዳዋ ከተማን 2-1 ሲያሸንፍ አምቦ ጎል ከ ወላይታ ድቻ 2-2 ተለያይተዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *