​የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 6ኛ ሳምንት የቅዳሜ ጨዋታዎች ቅድመ ዳሰሳ

ከተጀመረ አንድ ወር ያሳለፈው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 6ኛው ሳምንት አዲስ አበባ ላይ በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ይጀምራል። በሁለቱ ጨዋታዎች ላይ የተወሰኑ ነጥቦችን እናስነብባችሁ።

መከላከያ ከ ሀዋሳ ከተማ

በፌ/ዳ ይርጋለም ወ/ጊዮርጊስ የመሀል ዳኝነት ከቀኑ 09፡00 ሰዐት ላይ በሚጀምረው ጨዋታ እስካሁን ሁለት ነጥቦችን ብቻ በማሳካት በሊጉ ግርጌ የተቀመጠው መከላከያ  በ6 ነጥቦች 9ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘውን ሀዋሳ ከተማን ያስተናግዳል። የመጀመሪያዎቹን አራት ሳምንታት ጨዋታዎቹን በአዲስ አበባ ስታድየም ሲያደርግ የቆየው እና ሁለት ነጥቦችን ብቻ ያሳካው መከላከያ ሳምንት ከሜዳው ውጪ በአርባምንጭ ተሸንፏል። ክለቡም ከመቼውም ጊዜ በተለየ ከፍተኛ የውጤት ማጣት ገጥሞት ነው ሀዋሳን የሚያስተናግደው። ምን አልባት ተጋጣሚው ከሜዳው ውጪ ምንም ጨዋታ ያሸነፈ አለመሆኑ ለመከላከያ ተስፋ ሰጪ ይመስላል። ያገኟቸውን ስድስት ነጥቦች በሙሉ ሀዋሳ ላይ መሰብሰብ የቻሉት ሀዋሳ ከተማዎች ይህ ጨዋታ ከሜዳቸው ውጪ ነጥብ ይዞ ለመመለስ አራተኛ ዕድል የሚሰጣቸው ይሆናል። አምና 20ኛው ሳምንት ላይ መከላከያ ቅዱስ ጊዮርጊስን አሸንፎ እንዲሁም ሀዋሳ ከተማ በደደቢት 3-1 ተረቶ 20ኛው ሳምንት ላይ ሲገናኙ በሙሉ የጨዋታ ብልጫ 3-0 ማሸነፍ የቻሉት ሀዋሳ ከተማዎች ነበሩ።

ቴውድሮስ በቀለን ለብሔራዊ ቡድን ያስመረጠው መከላከያ በዚህ ሳምንትም ማራኪ ወርቁን እና አዲሱ ተስፋዬን በጉዳት የሚያጣ ይሆናል። በሀዋሳ በኩል ዳንኤል ደርቤ ከጉዳት ያላገገመ ሲሆን በአዳማ ከተማ በነበረው ጨዋታ ግጭት የገጠመው  ጋናዊው ላውረንስ ላርቴ ሌላው በጉዳት ከጨዋታ ውጪ የሆነው ተጨዋች ነው። ሆኖም የዳዊት ፍቃዱ እና ደስታ ዮሀንስ  ወደ ሜዳ መመለስ ለአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ቡድን መልካም ዜና ሆኗል።

ጨዋታው በዋነኝነት የሊጉን እጅግ ደካማ የአማካይ ክፍል በተቃራኒው በጥንካሬው ከሚታወቅ የአማካይ መስመር ጋር የሚያገናኝ ነው። ከሚካኤል ደስታ መልቀቅ በኃላ ሚዛኑን እያጣ የመጣው የመከላከያዎች የመሀል ክፍል አሁንም ችግሩ አልተቀረፈም። በተመሳሳይ የቡድን ቅርፅ እና የተጨዋቾች ምርጫ ጨዋታዎችን እያደረገ የሚገኘው ይሄው የቡድኑ ደካማ ክፍል ኳስ መስርቶ ለመጫወት ሲሞክር ቢታይም አሁንም የመጨረሻ የግብ ዕድሎችን በብዛት ለመፍጠር ሲቸገር ይታያል። ወደ መሀለኛው የሜዳ ክፍል የጠበበው የአማካይ መስመሩ እንቅስቃሴ ለተጋጣሚ የተከላካይ መስመር ለመከላከል ቀላል የሆነ አይነት ነው። ቡድኑ የሜዳውን ስፋት ለመጠቀም የሚረዳውም የፊት አጥቂዎቹ አልፎ አልፎ ወደመስመር እየወጡ የሚታዩበት የጨዋታ ሂደት ብቻ ሆኗል። ምናልባት በግላቸው የተሻለ ሲንቀሳቀሱ ለሚታዩት የጦሩ አጥቂዎች መልካም ዜና የሚሆነው ደካማው የሀዋሳ ከተማ የተከላካይ መስመር ክፍተት ነው። ላውረንስ ላርቴን አግኝቶ የተወሰነ መስተካከል የታየበት የሀይቆቹ የኃላ ክፍል በአዳማው ጨዋታ ከተጨዋቹ መውጣት በኃላ የቀደመ ያለመናበብ ችግሮቹ ታይተውበታል።  እናም የመሳይ ጳውሎስ እና ሲላ መሀመድ ጥምረት እንደ አምናው ሁለተኛ ዙር ጨዋታዎች የማይሆን ከሆነ ለሀዋሳ ከተማ ትልቅ ክፍተት ይሆናል። ከዚህ ውጪ ግን በታፈሰ ሰለሞን የሚመራው የቡድኑ የአማካይ ክፍል በተለይ በዚህ ጨዋታ የኳስ ቁጥጥር የበላይነቱን ለማግኘት እና ዕድሎችን ለመፍጠር የሚቸገር አይመስልም። የዳዊት ፍቃዱ መመለስም የቡድኑን የፊት መስመር አስፈሪነት እና የሜዳውን የጎን ስፋት በአግባቡ የመጠቀም ጥንካሬውን ከፍ የሚያደርገው ይሆናል። 

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ ጅማ አባ ጅፋር

በእኩል አራት ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው 14ኛ እና 15ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት አባ ጅፋር እና ኢትዮ ኤሌክትሪክን የሚያገናኘው ጨዋታ 11፡30 ላይ በፌ/ዳ ማናዬ ወ/ፃድቅ እየተመራ የሚጀምር ይሆናል። ሁለቱም ቡድኖች በተመሳሳይ መልኩ በመልካም ሁኔታ ሊጉን ቢጀምሩም አሁን ላይ ግን በወራጅ ቀጠናው ለመቀመጥ ተገደዋል። ባለሜዳዎቹ ኤሌክትሪኮች አርባምንጭን ሜዳው ላይ ረተው ከተመለሱ በኃላ አዲስ አበባ ላይ ሁለት ጨዋታዎችን በተከታታይ ሲሸነፉ ስድስት ግቦችን በማስተናገድ ጭምር ነበር። አባ ጅፋሮችም ከሶስት የ1-0 ተበታታይ ሽንፈቶች በኃላ ሳምንት ከሲዳማ ቡና ጋር አቻ በመለያየት በጥቂቱ እፎይታን ቢያገኙም ከመጀመሪያው ሳምንት በኃላ እስከአሁን ኳስና መረብን ማገናኘት አልቻሉም። አምና በሉጉ መገባደጃ ላይ በሌላው የጅማ ክለብ ጅማ አባ ቡና እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ መሀል ተነስቶ የነበረው ቅራኔ ይህን ጨዋታ የተወሰነ ውጥረት የሚያላብሰው ቢሆንም የአባጅፋር ደጋፊዎች በስፖርታዊ ጨዋነት ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ባነሮችን ወደሜዳ ይዘው ለመግባት እና በጨዋታውም ቡድናቸውን ብቻ ለማበረታታት የጀመሩት እንቅስቃሴ በመልካም ጎኑ የሚገለፅ እንዲሁም የጨዋታውንም መንፈስ እግር ኳሳዊ እንዲሄን የሚያግዝ ነው።

ግርማ በቀለ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ኄኖክ አዱኛ ከጅማ አባ ጅፋር በቤሔራዊ ቡድኑ ጥሪ በጨዋታው ላይ አይኖሩም። አዲስ ነጋሽ በቅጣት እንዲሁም ሱሊማን አቡ በጉዳት በጨዋታው ላይ የማይኖሩ ሌሎች የኤሌክትሪክ ተጨዋቼች ሲሆኑ በጅማ አባ ጅፋር በኩል ኤልያስ አታሮ ፣ አዳማ ሲሶኮ እና ኦኪኪ አፎላቢ ዝናቡ ባፋአን እና ጌቱ ረፌራን በጉዳት ዝርዝር ውስጥ ተቀላቅለዋል። 

ከአዲስ አበባ ዋንጫ ውድድር ጀምሮ በመሀል ተከላካይ መስመር ላይ የሚያጣምራቸውን አዳማ  ሲሶኮን እና ኤልያስ አታሮን በአንድ ጊዜ የጣው አባጅፋር ትልቅ ፈተና እንደሚገጥመው ይታሰባል። ለኢትዮ ኤሌክትሪክ የስካሁኖቹ ግቦች ዋነኛ ተጠቃሽ የሆነው አልሀሰን ካሉሻ እና ዲዲዬ ለብሪ ካላቸው ጠንካራ ጥምረት አንፃር የአባ ጅፋር የተከላካይ መስመር መሳሳት ለአሰልጣኝ ገ/መድህን ኃይሌ ትልቅ ራስ ምታት ይመስላል። ይህን ተከትሎም በጨዋታውም ከሚጠበቁ ዋነኛ ፍልሚያዎች አንዱ የሁለቱ የኤሌክትሪክ አጥቂዎች ከጅማ አባጅፋር አዲስ የተከላካይ መስመር ጥምረት ጋር የሚገናኙበት ይሄናል። ምናልባት የጅማዎች የተከላካይ አማካዮች አሜኑ ነስሩ እና ይሁን እንዳሻው ይህን ክፍተት በመሙላት እና የተጋጣሚያቸው የማጥቃት እንቅስቃሴ ወደ ግብ ክልላቸው ሳይደርስ ለማቋረጥ ከፍተኛ ሀላፊነት ይጠብቃቸዋል። የአባጅፋርን የዘንድሮ ብቸኛ ግቦች ያስቆጠረው አፎላቢም አለመኖር ለክለቡ ትልቅ እጦት ነው። በዚህ ረገድ ቡድኑ በቀኝ መስመር አማካዩ እንዳለ ደባልቄ የማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ እንደሚንተራስ የሚታሰብ ሲሆን እዚህ ቦታ ላይ ተጨዋቹ ከኢትዮ ኤሌክትሪኩ የግራ መስመር ተከላካይ ዘካሪያስ ቱጂ ጋር የሚገናኝበት ሂደት ተጠባቂ ነው። የኢትዮ ኤሌክትሪኩ የተከላካይ አማካይ ኄኖክ ካንሳሁን ከጅማ አባጅፋሩ ዋነኛ የፈጠራ ምንጭ ዮናስ ገረመው የሚገናኙባቸው አጋጣሚዎችም ጨዋታው ላይ ከሚጠበቁ  ፍልሚያዎች መሀከል የሚጠቀስ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *