ሪፖርት | ጅማ አባ ጅፋር መከላከያን በመርታት ደረጃውን አሻሽሏል

ዛሬ በተደረገ የሁለተኛው ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታ ጅማ አባ ጅፋር መከላከያን አስተናግዶ በአስቻለው ግርማ ብቸኛ ግብ 1-0 አሸንፏል፡፡

ባለሜዳዎቹ ጅማ አባ ጅፋሮች ባሳለፍነው ሳምንት በተስተካካይ ጨዋታ ደደቢትን ካሸነፈው ስብስብ ውስጥ ጉዳት ላይ የሚገኘው ኤልያስ አታሮን በተስፋዬ መላኩ በመተካት በ4-3-3 አሰላለፍ ወደሜዳ ሲገቡ በመከላከያ በኩል ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ነጥብ ከተጋራው ቡድን ዳዊት እስጢፋኖስ በሳሙኤል ታዬ እንዲሁም ፍቃዱ ዓለሙ በተመስገን ገብረኪዳን ተቀይረው ቡድኑ በተለመደው የ4-4-2 ዳይመድ አሰላለፍ ጨዋታውን ጀምሯል።

ጅማ አባ ጅፋር ከከፍተኛ ሊግ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ እንዲያድግ ብሎም ፕሪሚየር ሊጉን በተቀላቀለበት ዓመት ዋንጫ እዲያነሳ ከፍተኛውን ድርሻ ከተወጡ ተጫዋቾች መካከል የሚጠቀሰው ተመስገን ገብረኪዳን በጅማ ደጋፊዎች ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል፡፡

በባለሜዳዎቹ አማካይነት የተጀመረው የመጀመሪያው አጋማሽ አሰልቺ እና ሳቢ ያልሆነ ጨዋታ የተመለከትንበት ነበር። አብዛኛዎቹን ደቂቃዎች መሀል ሜዳ ላይ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ለመውሰድ በሚደረጉ ሽኩቻዎች የተገደቡ እቅስቃሴዎች የበረከቱበትም ሆኗል።

በተወሰነ መልኩ የኳስ ቁጥጥር ሚዛኑ ወደ መከላከያዎች ቢያጋድልም ወደ ግብ በመድረስ እና ሙከራ በማድረግ ጅማዎች የተሻሉ ነበሩ። ከመሀል ሜዳ ኳስን መስርተው ወደ ግብ ለመድረስ የሚደርጉት ጥረት እምብዛም ውጤታማ ያልሆነላቸው ጅማዎች ወደ መከላከያ ሳጥን ለመግባት በግራ እና ቀኝ በኩል ለመስመር አጥቂዎቻቸው ለአስቻለው ግርማ እና ዲዲዬ ለብሪ የሚጥሏቸው ተሻጋሪ ኳሶችን መጠቀም መርጠዋል። በ6ኛው ደቂቃ በመልስ ምት ከግብ ጠባቂው ዳንኤል አጄዬ ቀጥታ የተሻገረውን ኳስ አስቻለው ግርማ ፍጥነቱን በመጠቀም የመከላከያን ተከላካዮች በማለፍ ጅማዎችን ቀዳሚ ያደረገች ግብ አስቆጥሯል።

ግቡ ገና በመጀመርያዎች ደቂቃዎች እንደመቆጠሩ በሁለቱም ቡድኖች ላይ መነቃትንን እና ጥሩ የፉክክር መንፈስ እንደሚፈጥር ቢጠበቅም እንቅስቃሴው በመሀል ሜዳ ተገድቦ ቆይቷል። አልፎ አልፎ ጅማዎች ተሻጋሪ ኳሶችን በግንባር ለመግጨት የሚደርጉት ጥረት እንዲሁም በመከላከያ በኩል ከርቀት በምንይሉ ወንድሙ ከተሞከሩ ኢላማቸውን ያልጠበቁ ሙከራዎች ውጪ በ37ኛው ደቂቃ ፍሬው ሰለሞን ከተመስገን ጋር በጥሩ ቅብብል ወደ ሳጥን ውስጥ ገብተው ተመስገን ሞክሮ ዳንኤል ያዳነበት ሙከራ ብቻ በመከላከያ በኩል ሊጠቀስ የሚችል ነበር።

ከእረፍት መልስ ዳዊት ማሞን በፍቃዱ ዓለሙ ቀይረው በማስገባት በሦስት አጥቂዎች ለመጫወት የሞከሩት መከላከያዎች ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ የተደራጀ ጨዋታን በመጫወት ጫና መፍጠር ችለው ነበር። 59ኛው ደቂቃ ላይም ከቀኝ ሳጥን ጠርዝ ላይ የተገኘውን ቅጣት ምት ሳሙኤል ታዬ ከምንይሉ ጋር በፍጥነት አስጀምረውት ምንይሉ ሞክሮ የግቡን ቋሚ ታካ የወጣችበት አጋጣሚ እንዲሁም 62ኛው ደቂቃ ላይ ሳሙኤል ከርቀት ሞክሮት ዳንኤል አጄዬ ያዳነበት ሙከራዎች ተጠቃሾች ናቸው። አባ ጅፍሮች በሁለተኛው አጋማሽ በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት የሞከሩ ቢሆንም በ64ኛው ደቂቃ ማማዱ ሲዲቤ ከመስዑድ የተሻገረለትን ኳስ ሲሞክር በይድነቃቸው ኪዳኔ ከተመለሰበት አጋጣሚ ውጭ ወደ መከላከያ ግብ ክልል አልፈው የግብ ዕድሎችን መፍጠር አልቻሉም።

75ኛው ደቂቃ ላይ አስቻለው ግርማን ተክቶ ወደ ሜዳ የገባው ቢስማክ አፒያን ጨምሮ ጨዋታውን የጀመሩት ዳንኤል አጄዬ ፣ አዳማ ሲሶኮ ፣ ዲዲየ ለብሪ እና ማማዱ ሲድቤ ጋር ጅማ አባ ጅፍር ያሰለፋቸው የውጭ ተጫዋቾች ቁጥር ወደ አምስት ከፍ በማለቱ መከላከያዎች ለዕለቱ ኮሚሽነር እና ዳኛ በኩል የክስ ቻርጅ አስመዝግበዋል፡፡ ከክሱ መመዝገብ በኃላ የተደናገጡት ጅማዎች ዲዲየ ሌብሬን በኤርሚያስ ኃይሉ በመቀየር አስወጥተዋል።

በጨዋታው መገባደጃ ከርቀት የተሻገረን ኳስ ለመመለስ ከሳጥን ውጭ ኳስን በእጅ የነካው የጦሩ ግብ ጠባቂ ይድነቃቸው ኪዳኔ በቀይ ካርድ ከሜዳ ሲወጣ የተሰጠውን ቅጣት ምት ማማዱ ሲዲቤ ከመምታቱ በፊት ከዳኛው ጋር በገባው እሰጣ ገባ ቅጣት ምቱን ሳይመታ የቢጫ ካርድ ሰለባ ሆኖ ጨዋታው ፍፃሜውን አግኝቷል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *