የአሰልጣኞች አስተያየት | ድሬዳዋ ከተማ 1-3 ሲዳማ ቡና


ድሬዳዋ ላይ ከተደረገው ጨዋታ በኋላ አሰልጣኞች የሰጡትን አስተያየት እነሆ!

” የመጣነው ማሸነፍ ፈልገን ነው፤ ማሸነፋችንም ይገባናል ” ዘርዓይ ሙሉ – ሲዳማ ቡና

ስለ ጨዋታው

እንዳያችሁት ሙሉ ዘጠና ደቂቃ ኳሱን ይዘን ተጫውተናል። የመጣነው ማሸነፍ ፈልገን ነው፤ ማሸነፋችንም ይገባናል። መጀመርያ ሜዳውን ስናይ የማያጫውተን መስሎን ፈርተን ነበር። እንዳሰብነው ግን አልከበደንም። ዛሬ ይዘነው የገባነው የጨዋታ አቀራረብ የማጥቃት ባህሪ ያላቸውን ተጫዋቾችን ያማከለ ነው። ማሸነፍን ዕቅዳችን አድርገን ስለመጣንም ተሳክቶልናል። እነርሱም ያገኙትን አጋጣሚ አልተጠቀሙም እንጂ እንቅስቃሴያቸው አያስከፋም።

በጨዋታ የመብለጣቸው ምክንያት

ቅድም ተናግሬያለው። በተለይ መሐል ሜዳ ላይ ኳስ ይዘው የሚጫወቱ ተጫዋቾች ማስገባታችን መሐል ሜዳውን እንድንቆጣጠር አድርጎንል። ይህም መሆኑ በቀላሉ ሳንቸገር ወደ ፊት እንድንሄድ አድርጎናል። በዛ ላይ ጨዋታው በድሬዳዋ በኩል አላማ አልነበረውም። በዛ ነው ብልጫውን እንድንወስድ የሆነው። ወደ ጨዋታው መጠናቀቂያ ግን ውጤቱን ማስጠበቅ ስለሚገባን የመከላከል አቅም ያላቸውን ተጫዋቾች ቀይረን አስገብተናል።

ቡድኑ ከጨዋታ ጨዋታ እየተሻሻለ መሆኑ እና በወጣቶች የተገነባ መሆኑ የሰጠው ጠቀሜታ

የውድድር ዓመቱ ገና ሳይጀምር አቅደን የተነሳነው በወጣቶች የተገነባ፣ ኳስ ይዞ የሚጫወት ቡድን መስራት እንዳለብን ነው። ለዚህም የሚረዱ እና እኛ ለምንፈልገው አጨዋወት የሚሆኑ ተጫዋቾችን ነው የያዝነው። እንግዲህ እስካሁን ውድድሩ ከተጀመረ ጀምሮ ኳስ ይዞ የሚጫወት ወጥ የሆነ አቋም ያለው እንዲሁም ለወደፊቱ ተስፋ ያለው ቡድን ገንብተናል። በዚህ አጋጣሚ በወጣት ተጫዋቾች እንመን፤ ብዙ ስራ መስራት ይችላሉ የሚል መልክት ማስተላለፍ እፈልጋለው።

ስለ ቀጣይ

ይህን ጥንካሬ ይዘን እንቀጥላለን። በተወሰኑ ቦታዎች ላይ አዲስ ተጫዋች አስፈርመናል። ጉዟችን ወደ ዋንጫ ነው። የውድድሩም አሸናፊ ሆኖ ለማጠናቀቅ ከፍተኛ ዕድል አለን።

” ዛሬ ነገሮች ሁሉ ከብደውናል” ስምዖን ዓባይ – ድሬዳዋ ከተማ

ስለ ጨዋታው

ከወትሮ ለየት ያለ መልክ ነበረው። መሐል ሜዳ ላይ ብልጫ ተወስዶብን ነበር። መሐል ላይ ብልጫ ከተወሰደብክ ደግሞ ቡድንህ ምንም አይነት ነገር መቆጣጠር አይችልም። ትልቁ ነገር ያየሁት አንደኛ በተጫዋች ጥራት በኩል ልዩነታችን የሰፋ ነው። ሁለተኛ እንደ ምክንያት ባልወስደውም ተጫዋቾቹ ላይ ድካም ይታይ ነበር። ሦስተኛ ሲዳማ ቡና በጣም ጠንካራ ቡድን ነው። ስለዚህ በብዙ መልኩ ዛሬ ጥሩ አልነበርንም። የጎል አጋጣሚዎችን ከመፍጠራችን ውጪ በእንቅስቃሴ ረገድ እነርሱ የተሻሉ ስለነበሩ ዛሬ ነገሮች ሁሉ ከብደውናል።

ክፍት የተከላካይ መስመር አጋጥሞት አለመጠቀሙ

ትክክል ነው። ስለ እግርኳስ ስናወራ የተደበቀ ነገር የለም፤ የሚታይ ነው። ሜዳ ላይ የጎል አጋጣሚዎችን ፈጥረናል። አንድ፣ ሁለት፣ ሦስት ኳሶችን ልትስት ትችላለህ። አራተኛ እና አምስተኛውን ግን ማግባት አለብህ። ይህ የማይሆን ከሆነ በስነ-ልቦናው የፈጠረባቸው ነገር አለ ማለት ነው። መቋቋም ያልቻሉትም ነገር ያለ ይመስለኛል። በተለይ ፊት ላይ ያሉት ተጫዋቾች ብዙ ኳስ አምክነዋል። እነዚህ ነገሮች በራስ መተማመን አሳጥተውናል፤ ተጫዋቾቹ ወርደውብናል። ይሄን ወደ ፊት የምናየውም ቢሆንም መሐል ሜዳ ላይ መበለጣችን እና ያገኘነውን አጋጣሚ አለመጠቀማችን ዋጋ አስከፍሎናል።

ወደ አንደኛው ዙር መጠናቀቂያ ላይ ቡድኑ በርካታ ጎሎች የማስተናገዱ ምክንያት

አራቱም ተከላካዮች ብዙ ጨዋታ ተጫውተዋል። ድካም እየታየባቸው ነው። የማሸነፍ ፍላጎታቸውም ቀንሷል፤ ይትኩረት ማጣት ይታይባቸው ነበር። ተደጋጋሚ ጨዋታ በምታደርግበት ሰዓት ብዙ ነገሮችን ታጣለህ። እነዚህን ሰዎች መቀየር ካልቻልክ እንደ ዛሬው ዋጋ እየከፈልክ ትሄዳለህ። አማካዮቹም ክፍተት ነበረባቸው። የእነርሱ ክፍተት ደግሞ ተከላካይ ላይ ጫና እየፈጠረ ሄዶል።

ስለ ሁለተኛው ዙር

አስራ ስምንት ነጥብ ይዞ ለመጨረስ ነበር እቅዳችን አልተሳካም። ይህ መጥፎ አይደለም። የቡድናችን የተጫዋች ጥልቀት እንደምታዩት ነው። በአራት እና በሦስት ቀን ልዩነት ስትጫወት እንዴት እንደምትጋለጥ እየታየ ነው። የሚሰሩ ስራዎች ይኖራሉ፤ የተወሰኑ ተጫዋቾች ይመጣሉ ። በድክመታችን ላይ ተጫዋቾች መቀያየር ከቻልን ጥሩ ነገር ይመጣል ብዬ አስባለው።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *