ሶከር መፅሀፍት | ኢንቨርቲንግ ዘ ፒራሚድ (ምዕራፍ አራት-ክፍል ሦስት)

በእንግሊዛዊው የእግርኳስ ጸኃፊ ጆናታን ዊልሰን ደራሲነት በ2008 ለንባብ የበቃው Inverting the Pyramid: The History of Football Tactics ን በሶከር ኢትዮጵያ በተከታታይ ክፍሎች እያቀረብንላችሁ እንገኛለን፡፡ በዛሬው መሠናዶም የአራት ሁለተኛ ክፍል እንዲህ ይቀርባል፡፡

|| ያለፈውን ሳምንት ለማንበብ ይህን ይጫኑ LINK

ከ1930ዎቹ አጋማሽ በኋላ የ<ዉንደርቲም> እግርኳሳዊ ልዕለ-ኃያልነት ወደ ማክተሙ ተቃረበ፡፡ ኦስትሪያውያኑ በአውሮፓ የተቆናጠጡትን የጨዋታ የበላይነት ለጣልያኖቹ አስረከቡ፡፡ አዲሶቹ ባለተራዎች በጥልቀት ሳያውቁትም ቢሆን በፎርሜሽን አጠቃቀም ረገድ በእንግሊዛውያኑ 2-3-2-3 (W-M) እና በዳኑቢያኑ 2-3-5 መካከል የሚዋልለውን የተጫዋቾች የሜዳ ላይ አደራደር መተግበር ቀጠሉ፡፡ ይሁን እንጂ ጣልያኖች የቡድን ስነ-ስርዓትን የማስጠበቅ ጠንካራ ባህል ላይ ባላቸው ጽኑ እምነት ከሌሎቹ ይለዩ ነበር፡፡ ብሪያን ግላንቪል የወቅቱን የልዕልና ሽግግር በተመለከተ ” ጣልያናውያን ቴክኒካዊ በሆኑ ጉዳዮች ከሌሎቹ የአውሮፓ ሃገራት ተቀናቃኞቻቸው አንጻር ደከም ያሉ ናቸው፡፡ ነገር ግን ይህን ጉድለት በተጫዋቾቻቸው ምርጥ የአካል ብቃት እና የአልበገር-ባይነት ስነ ልቦናዊ ብልጫ ያቻችሉታል፡፡” ሲል ጽፏል፡፡

በፋሺስታዊው አገዛዝ ስር ለተክለ ሰውነት ግንባታ እና ቅልጥፍና ቅድሚያ የመስጠት ዝንባሌ ተለመደ፡፡ በሁለቱ የዓለም ጦርነቶች መካከል በነበረው ዘመን ሃገሪቱ ዓለማቀፋዊ የእግርኳስ ደረጃዋን ከፍ ወዳለ እርከን አሻገረችው፡፡ ዘወትር እጅብ ብሎ እንደነገሩ በሚያዘው ጸጉሩ የሚታወቀው ባለራዕዩ ቪቶሪዮ ፖዞ ደግሞ ለታሪካዊው የውጤታማነት ዓመታት የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል፡፡ ጣልያን በዚያን ወቅት የተቀዳጀቻቸው እግርኳሳዊ ስኬቶች ያለ አስተዋዩና ትልመኛው አሰልጣኝ የሚታሰቡ አልነበሩም፡፡ አጠቃላይ የሃገሪቱ ዘመናዊ እግርኳስ እድገትም በእርሱ አማካኝነት መጠንሰሱ ሁሉን የሚያስማማ ነው፡፡

በ1886 ቱሪን አቅራቢያ በምትገኝ ትንሽ  መንደር ውስጥ ተወልዶ ያደገው ፖዞ በልጅነቱ ጥሩ ሯጭ የመሆን እምቅ አቅም አሳይቶ ነበር፡፡ እንዲያውም በ<ፒድሞንት የተማሪዎች ጨዋታዎች> ውድድር ላይ የ400 ሜትር ሩጫ አሸንፎ ያውቃል፡፡ ከፍ ሲል በመሃል ተከላካይ- አማካይነት (Centre-Half) ሚና ለጁቬንቱስ የመጫወት እድል ያገኘው ጂዮቫኒ ጎሲዮኔ የተባለው የልጅነት ጓደኛው ” ጎበዝ ከሆንክ ዝም ብለህ እንደ ሞተር ከምትከንፍ ፥ እስቲ ኳሷን እግርህ ስር ይዘህ ፊት ለፊትህ ሩጥ፡፡” ብሎ አፌዘበት፡፡ ፖዞ ወዲያውኑ ሐሳቡን ቀየረና እግርኳስን መጫወት ጀመረ፡፡ ትልቅ ተጫዋች ከመሆኑ በፊት ግን በዓለም ዓቀፉ የዙሪክ ንግድ ትምህርት ቤት ጥናቱ ላይ አተኩሮ በትምህርቱ ዓለም ገፋበት፡፡

በዚህ ተቋም ውስጥ እንግሊዘኛ፣ ፈረንሳይኛና ጀርመንኛ ቋንቋዎችን ተማረና ወደ ለንደን አመራ፡፡ በርዕሰ መዲናዋ ለረጅም ጊዜ ስደተኛ ሆኖ መቆየቱ ሲታክተው ወደ ሰሜናዊ የሃገሪቱ ሌላኛዋ ከተማ ብራድፎርድ አቀና፡፡ በዚያም በአባቱ ገፋፊነት የሙሉ ልብስ ጥሬ እቃ የሆነውን የሱፍ ጨርቅ አመራረት አጠና፡፡ በሒደት እንግሊዝና እግርኳሷ ሃሳቡን ወጥረው ያዙት፡፡ ስለዚህም አዲስ ቤቱን ለመላመድ እጅግ ታታሪ ሆኖ ተገኘ፡፡ የካቶሊክ እምነት ተከታይ ቢሆንም በእንግሊዝ ቤተክርስቲያናት የሚሰጡ መንፈሳዊ ትምህርቶች ላይ መታደምም ጀመረ፡፡ ሙሉ ሳምንቱን እንግሊዛዊነት እየሰረጸበት ይሄድ ገባ፡፡ እሁድ-እሁድ ቤተክርስቲያን ይሄዳል፤ ለአምስት ቀናት ይሰራል፡፡ ቅዳሜ-ቅዳሜን ደግሞ ለእግርኳስ የተመደበ ቀን አደረገው፡፡ ቤተሰቦቹ በወንድሙ የኢንጅነሪንግ ኩባንያ ውስጥ እየሰራ እንዲያግዘው ቢወተውቱ ፖዞ “አሻፈረኝ!” አላቸው፡፡ በውሳኔው የተናደዱት አባት ለልጃቸው በተቆራጭ መልክ የሚልኩትን ድጎማ አቋረጡ፡፡ በዚህ ምክንያት ቋንቋ እያስተማረ መተዳደሪያሪያውን ለማሟለት ጣረ፡፡

በዲክ ደክወርዝ፣ ቻርሊ ሮበርትስ እና አሌክ ቤል ጥምረት የተገነባውን ድንቅ የተከላካይ መስመር የያዘው ማንችስተር ዩናይትድ በአጨዋወት ዘይቤው ሳቢያ የፖዞ ተመራጭ ክለብ ሆኖ ነበር፡፡ ከጨዋታዎች በኋላ ተጫዋቾች በሚወጡበት የኦልድ ትራፎርድ በር ላይ እያንዣበበ ከተጫዋቾች ጋር ቅርበት ለመፍጠር ሞከረ፡፡ በአንደኛው ሳምንት ብርታት ተሰማውና ደፍሮ ሮበርትስን ቀረብ አለው፡፡ እጅጉን እንደሚያደንቀው አወጋው፤ ከእርሱ ጋር ስለጨዋታዎች የመወያየት እድል ቢያገኝም እንደሚደሰት ነገረው፡፡ ይህም የሁለቱን ረጅም ዘመን የዘለቀ ጓደኝነት ጅማሮ አበሰረ፡፡ ወዳጅነቱ አድጎ እርሱ የሚያሰለጥነው የጣልያን ቡድን ከሃያ ዓመታት በኋላ የተጠቀመበትን የጨዋታ ዘይቤ ወለደ፡፡ ሶስተኛ ተከላካይን (Third Back) ለሚያካትተው የጨዋታ ስልት ከፍተኛ ጥላቻን ያሳድር ስለነበር የእርሱ የመሃል ተከላካይ-አማካይ (Centre Half) ልክ ሮበርትስ በማንችስተር ዩናይትድ ሲያደርግ እንደነበረው ረጃጅም ቅብብሎችን ወደ መስመሮች የማሻገር ብቃት የያዘ እንዲሆንለት ፈለገ፡፡ አሰልጣኙ በመሰረታዊነት የያዘው እምነት የተለያዩ ውሳኔዎች ሲያሳልፍ በደንብ አግዞታል፡፡ በ1924 <ኮሚሳሪዮ ቴክኒኮ> በመባል የሚታወቀውን የቡድኑ ቴክኒክ ኮሚቴ ሲሾም ወዲያውኑ በሮማውያኑ ዘንድ የጣዖት ያህል የሚታየውን ፉልቪዮ ቤርናዲኒ  ከቡድኑ ቀነሰው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ተጫዋቹ ኳስን እግሩ ስር የሚያቆይ እንጂ ወደ ተለያዩ የሜዳው ክፍሎች የሚያሰራጭ አልነበረም፡፡

ፖዞ በእህቱ የሰርግ ስነ ስርዓት ላይ ለመገኘት ወደ ጣልያን ባቀናበት ወቅት ቤተሶቦቹ ዳግም ወደ እንግሊዝ እንዳይመለሰ ከለከሉት፡፡ ወዲያውኑም በጣልያን እግርኳስ ማህበር ውስጥ የጸሃፊነት ስራ አገኘ፡፡ ለ1912ተ ኦሊምፒክ ብሄራዊ ቡድኑን ይዞ ወደ ሲውዲን እንዲሄድ ታዘዘ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜም የቴክኒክ ኮሚቴ ሆኖ ሰራ፡፡ በውድድሩ ጅማሬ ጣልያን በፊንላንድ በጠባብ ውጤት ከተረታች በኋላ ሲውዲንን በማሸነፍ ጉዞዋን ለማስተካከል ብትሞክርም በኦስትሪያ አስከፊ በሆነ ሁኔታ 5-1  ተረመረመች፡፡ አስደንጋጩ ሽንፈት ያልተጠበቀና እጅግ የሚያበሳጭ ቢሆንም በፖዞና በሜይዝል መካከል የመጀመሪያ ግንኙነት እንዲፈጠር ከማድረግ አኳያ ትልቅ ፋይዳ ነበረው፡፡ ከዚያን ጊዜ አንስቶ ሁለቱ የእግርኳስ ባለሙያዎች ቀሪ ዘመናቸውን ተቀናቃኝ ግን ደግሞ ጥሩ ወዳጆች ሆነው አሳለፉ፡፡

በቀጣዩ ዓመት ታህሳስ ወር ጣልያን በድጋሚ በኦስትሪያ 3-1 ስትሸነፍ ፖዞ ተስፋ መቁረጥ ላይ ወደቀ፡፡ ስራውን በገዛ ፈቃዱ ለቀቀና ለጨዋታዎች የሚያደርገውን ጉዞ ገታ አድርጎ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ እንደገና ለመጀመር ወጠነ፡፡ በአንደኛው የአለም ጦርነት ወቅትም <አልፒኒ> ተብሎ በሚጠራው የሃገሪቱ ጦር ሰራዊት ውስጥ የአንድ ዕዝ ሻለቃ በመሆን አገለገለ፡፡ ከጦርነቱ መጠናቀቅ በኋላ በፈረንሳይ የሚዘጋጀው የ1924ቱ ኦሎምፒክ ከመጀመሩ ጥቂት ወራት በፊት እንደተለመደው ጣልያን በኦስትሪያ 4-0 ስትረታ ለሁለተኛ ጊዜ የብሄራዊ ቡድኑ ቴክኒክ ኮሚቴ አባል በመሆን ተሾመ፡፡ በውድድሩ ጣልያኖች በፓሪስ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ አሳዩ፡፡ በጠባብ ውጤት በሲውዘርላንድ ሽንፈትን ከማስተናገዳቸው በፊት ስፔንና ሉክዘንበርግን ድል መቱ፡፡ ይሁን እንጂ የፖዞ የህይወት ፈተና አላበቃም፤ ባለቤቱ አረፈችና በድጋሚ ራሱን ከስራ አገለለ፡፡ ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታትም የ<ፒሬሊ> ኩባንያ አስተዳዳሪ በመሆን አገለገለ፡፡ ትርፍ ሰዓቱንም ከጠባቂ ውሻው ጋር በመሆን ተራሮች ላይ ጉዞዎችን በማድረግ አሳለፈ፡፡ በ1929 ደግሞ ለሶስተኛ ጊዜ የጣልያን እግርኳስ ፌዴሬሽን ለፖዞ ጥሪ አቀረበለት፡፡ ከዚያ በኋላ ፖዞና ጣልያን የማይነጣጠሉ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ሆኑ፤ ለተከታታይ ሃያ ዓመታት ለሃገሪቱን “ደከመኝ- ሰለቸኝ!” ሳይል ለፋላት፤ ጣልያንን የአውሮፓ ምናልባትም የአለም ኃያል የእግርኳስ ሃገር አደረጋት፡፡

ፖዞ መጀመሪያ ስራውን ሲረከብ በስድሳ አራት ክለቦች የታጨቀ የሊግ ውድድር ገጠመው፡፡ መደበኛ አውታሩን የጠበቀ የአንደኛ ዲቪዥን መዋቅር ሲያቋቁም አብዛኞቹ ክለቦች ከፌዴሬሽኑ ስር ወጡ፡፡ ለሶስተኛ ጊዜ ወደ እግርኳስ አመራሩ ቢሮ ሲመለስ ግን ሊጉ <ፕሮፌሽናል> ሆኖ ጠበቀው፤ ሃገሪቱ ላይም ስፖርትን የፖለቲካ ትርፍ ማጋበሻና የቅስቀሳ መሳሪያ የሚያደርገው የፋሺስት አስተዳደራዊ ስርዓት ነግሶ ነበር፡፡ ስለዚህም ገዢው መንግስት ስታዲየሞችን በማሰራትና የመሰረተ ልማት አውታሮችን በማስፋፋት ረገድ ጉልህ ድርሻ ተጫወተ፡፡ ከፍተኛ የሆነ መዋዕለ-ነዋይ ፈሰስ ማድረጉንም ተያያዘው፡፡ ” ከጠረፍ ውጪም ይሁን ውስጥ፣  ስፖርታዊ በሆነና ባልሆነ ምክንያት እኛ ጣልያኖች ታላላቅ ባላንጦቻችን ላይ አስገራሚ የበላይነት እያሳዩ ያስደሰቱንን እነዚያን ምርጥ የተጫዋቾች ትውልድ ስናይ እጆቻችንን ወደ ላይ አወዛውዘናል፤ እስካሁንም በደስታ ከፍ እያደረግን እንገኛለን፡፡ የቡድኑ ተምሳሌት ጀብደኞቹና ድል አድራጊዎቹ የሙሶሎኒ ጣልያናዊያን የጦር ሰራዊት ሰልፈኞች ነበሩ፡፡” ሲል የሙሶሎኒ ፕሬስ አታሼ የነበረው ሎንዶ ፌራቲ  ከ1938ቱ የአለም ዋንጫ ድል በኋላ <ሎ ስፖርት ፋሺስታ> በተባለው ጋዜጣ ላይ የቡድኑን አልቀመስ ባይነት አጉልቶ ፃፈ፡፡

ፖዞ ከፋሺስታዊው የአገዛዝ ስርዓት ጋር ምን ያህል ቁርኝት እንደነበረው እስካሁንም ግልጽ አይደለም፡፡ ከሙሶሎኒ ጋር የመሰረተው ግንኙነት በአስራ ዘጠኝ ሃምሳዎቹና ስድሳዎቹ ላይ ከአካባቢው እንዲርቅ ገፋፍቶታል፤ በዚህ ምክንያትም ለ1990ው የአለም ዋንጫ ዝግጅት ከቱሪን ከተማ ወጣ ብሎ የተገነባው የዴል አልፒ ስታዲየም በእርሱ መጠሪያ እንዳይሰየም ተደርጓል፡፡ ይሁን እንጂ በ1990ዎቹ ፖዞ ፀረ-ፋሺስት ትግልን ይደግፍ እንደነበርና በ<ቢዬላ> ከተማ ዙሪያ ለሰፈሩ የስርዓቱ ተቃዋሚዎች ደግሞ በድብቅ ምግብ በማቅረብ እንደሚረዳ የሚያሳዩ ማረጋገጫ የተገኘላቸው መረጃዎች መውጣት ጀመሩ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በሁለተኛው የአለም ጦርነት ወቅት ከፈረንሳይ፣ ታላቋ ብሪታኒያ፣ ሶቪየት ህብረት፣ አሜሪካና ቻይና የተውጣጡ የጦር ምርከኞችና እስረኞችን በማስመለጥ በኩል ትልቅ ሚና ተወጥቷል፡፡

አሉባልታዎቹ እንዳሉ ሆነው ፖዞ ቡድኑን ለማነሳሳት እና የኃያልነት ደረጃ ላይ እንዲደርስ ለማድረግ ሙሉ ለሙሉ የወታደራዊውን መንግስት ፈላጭ ቆራጭነት ተጠቅሞበታል፡፡ ” ከአንድ በላይ መራጭ የማቻቻል ስራን ይሰራል፤ በእንዲህ አይነቱ ሁኔታ ደግሞ ታላቅ የእግርኳስ ቡድን ፍጹም ሊገነባ አይችልም፡፡” ይላል ፖዞ፡፡ አሰልጣኙ ሰው በማስተዳደር ረገድ እጅግ ብልጥ ነበር፡፡ በክለብ ደጋፊዎቻቸው የመመለክ ያህል ከሚወደዱ ተጫዋቾቹ ጋር ጥብቅ አባታዊ ቅርበት ይመሰርታል፡፡ ለምሳሌ ያህል፦ በልምምድ መርኃግብር ወቅት የሚደረጉ ግጥሚያዎችን በመሉ እርሱ ይዳኛል፤ አንድ ተጫዋች ግላዊ የእርስ በርስ ቅያሜን ተገን አርጎ ለቡድን አጋሩ ኳስ የማቀበል ፍላጎት እንዳላሳየ ከተሰማው ከጨዋታው ያስወጣዋል፤ ሁለት የማይግባቡ ተጫዋቾች ካሉም አንድ ክፍል እንዲጋሩ ያስገድዳቸዋል፡፡ ውሳኔው ዘወትር በከፍተኛ መጠን ያወዛግብ እንጂ ይህ የእርሱ ለሃገር ፍቅር መስዋዕትነት የመክፈል ትርጉም ነበር፡፡ አንድ አብነት ለመጨመር ያህል ከሃንጋሪ ጋር የወዳጅነት ግጥሚያ ለማካሄድ ወደ ቡዳፔስት አቅንተው 5-0 ድል ባደረጉበት ወቅት የጣልያን ተጫዋቾች <ኦስላቪያ> እና <ግሪዚያ> የተባሉ አንደኛው ዓለም ጦርነት የተካሄደባቸው የጦር አውድማዎችን እንዲጎበኙ አደረገ፡፡ ከዚያም <ሪዱፕጊሊያ> የሚገኙ የመቃብር ሐውልቶችን አሳያቸው፡፡ ” በአሳዛኙና አስፈሪው ትዕይንት የተጫዋቾቹ ልብ መነካቱ የሰብዓዊነት ስሜታቸው መግለጫ ስለሆነ መልካምነቱን ነገርኳቸው፡፡

እኛ የምንጠየቀው የትኛውም ዓይነት ማህበራዊ ግዴታ እና መክፈል የሚጠበቅብን መስዋዕትነት በእነዚያ ኮረብታማ ስፍራዎች ውድ ህይወታቸውን  ካጡት ወገኖቻችን ጋር ፈጽሞ ለንጽጽር የሚቀርብ እንዳልሆነ እንዲረዱ ያግዛቸዋል፡፡” ሲል ጉብኝቱን አሰመልክቶ በግለ ታሪክ መጽሃፉ ውስጥ ሃሳቡን አስፍሯል፡፡ ሁኔታዎች ሲመቻቹ ደግሞ ተጫዋቾቹን በጥብቅ ወታደራዊ ስርዓት አሰልፎ <የፒዬቭ ወንዝ ቁርሾ> ተብሎ ከሚጠራው ጦርነት ማግስት በኢ.ኤ.ማሪዮ የተጻፈና ከ1943 በኋላ ደግሞ በኡምቤርቶ ሁለተኛ አማካኝነት የሃገሪቱ ብሄራዊ መዝሙር ተደርጎ የተመረጠውን <ላ-ለጄንዳ ዴል ፒዬቭ> የተሰኘ የጣልያን አርበኞች ዘፈን ያቀነቅንላቸዋል፡፡

ይህ ሁሉ ሆኖ ፖዞ እንግሊዝ-ነክ የሆኑ ነገሮችን የሚያደንቅ እና እንግሊዛዊነት የተጸናወተው፣ ያለፈውን ወርቃማና ሚዛናዊ የእግርኳስ ዘመን ለማውሳት የሚችል፣ የሃገራት እግርኳስ ውድድሮች መለያ ባህሪያት የሆኑትና በማሸነፍ ብቻ የሚሰጡ ጉርሻዎች ጎጂነት አብዝቶ የሚያስጨንቀው ሰው ነበር፡፡ ስለዚህ ሁኔታ ፖዞ ሲያብራራ ” የጨዋታው መርህ በየትኛውም መንገድ ማሸነፍ ሆኗል፤ በዚህ በባላንጣ ላይ የሚደርሰው መራሩ ቂም ነው፤ ውጤቱም የሊግ ውድድሩ መገባደጃ ከመድረሱ በፊት ውጤቶችን ቀድሞ የመሰብሰብ ጉዳይ እየሆነ ይገኛል፡፡” ይላል፡፡ ፖዞ ወደ ጥንቱ 2-3-5 ፎርሜሽን ቢያደላም ይህን የተጫዋቾች የሜዳ ላይ አደራደር በተገቢው ሁኔታ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችልና በሜዳው የተለያዩ ክልሎች በተለይ ደግሞ በመሃለኛው ክፍል እንደልቡ መንቀሳቀስ የሚያዘወትርና የፈጠራ ክህሎትን የታደለ የመሃል ተከላካይ-አማካይ (Center-Half) ችግር ነበረበት፡፡ በዚህም ምክንያት አሰልጣኙ በ1930ው የአለም ዋንጫ ላይ ለአርጀንቲና ብሄራዊ ቡድን የተጫወተውን ሉዊዚቶ ሞንቲ መረጠ፡፡ ሞንቲ በ1931 ጁቬንቱስን ተቀላቅሎ <ኡሪየንዲ> የመሆን እድል አገኘ፡፡ ኡሪየንዲ በወቅቱ ጣልያናዊ ዝርያ ኖሯቸው ለደቡብ አሜሪካ ሃገራት መጫወት ለቻሉ ተጫዋቾች የተሰጠ ስያሜ ነበር፡፡ ለቢያንኮኔሪው ክለብ ሲፈርም ሰላሳኛ ዓመቱ ላይ የደረሰው ይህ ተጫዋች ከልክ ያለፈ የሰውነት ክብደት ይዞ ተገኘ፡፡ ለአንድ ወር የቆየ ወታደራዊ ስልጠና ቢወስድም አካላዊ የፍጥነት ችግሩን ሊቀርፍ አልቻለም፡፡ ይሁን እንጂ ሞንቲ ግዝፈቱ ሜዳውን በሙሉ ለማካለል ብቁ እንዳይሆን አላገደውም፡፡ <ደብል አንቾ> ወይም <Double Wide> የሚል መጠሪያ ያገኘውም በዚህ ሳቢያ ይመስላል፡፡

ፖዞ ምናልባትም በጁቬንቱስ ጥቅም ላይ ይውል የነበረው ፎርሜሽን ተጽዕኖ አሳድሮበት ሞንቲን <ሴንትሮ ሚዲያኖ> አድርጎ ተጠቀመበት፡፡ ሚናው ለቻርሊ ሮበርትስ ያልተጠጋ፥ ኸርቢ ሮበርትስንም ያልወከለ ነገር ግን ከሁለቱ ተጫዋቾች የአጨዋወት ባህሪ የተዳቀለ ነበር፡፡ ተጋጣሚ ቡድን የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ሲያሳይ ሞንቲ ወደ ኋላ ያፈገፍግና የመሃል አጥቂው ላይ የአንድ ለ-አንድ ጥብቅ ክትትል (Man Marking) ማድረግ ይጀምራል፤ የራሱ ቡድን የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ሲወስድ ደግሞ ወደ ተቃራኒ ቡድን የመከላከል ወረዳ ይጠጋና የቡድኑ የማጥቃት ጨዋታ ዑደት አቀጣጣይ ወይም መዘውር (Attacking Fulcrum) ይሆናል፡፡ ምንም እንኳ ተጫዋቹ የሶስተኛው ተከላካይ (Third Back) ኃላፊነትን የማይወጣ ቢሆንም ተለምዷዊው የመሃል ተከላካይ-አማካይ (Centre-Half) ከሚጫወትበት አመዛኝ እንቅስቃሴያዊ ቦታም እጅግ አፈግፍጎ ስለሚጫወት ከመሃል አጥቂው ግራና ቀኝ የሚጫወቱት የፊት መስመር ተሰላፊዎች (Inside-Forwards) ወደ ኋላ እየተመለሱ የመሃል-ክንፍ አማካዮችን (Wing-Halves) ያግዛሉ፡፡ ስለዚህም መዋቅራዊ የተጫዋቾቹ አቀራረብ ቅርጽ 2-3-2-3 ወይም W-W ሆነ፡፡ በ1939 በሚላን የፖዞ ጣልያን ከእንግሊዝ ጋር 2-2 አቻ ከተለያየች በኋላ ብቻ በተለምዶ <ሜትዶ> (Metodo)፥ ፖዞ ደግሞ <ሲስተማ> (Sistema) ብሎ የሚጠራው የW-M ፎርሜሽን በጣልያን የተወደሰበትን ሙሉ አንድምታ የያዘ አንድ የቤርናንዲኒን ጽሁፍ እንዳነበበ ብሪያን ግላንቪል ገልጿል፡፡ የ<ላ ጋዜታ ዴሎ ስፖርት> ጋዜጠኛ እንደፃፈውም በወቅቱ ይህ ፎርሜሽን “ከሁሉም እጅግ ተደናቂ የተጫዋቾች የሜዳ ላይ አደራደሮች የተውጣጡ ወሳኝ ነገሮችን ያካተተ የአጨዋወት ስርዓት” መሰለ፡፡

ቅርጽ አንድ ነገር ነው፡፡ ዘይቤ ደግሞ ሌላ፡፡ ምንም እንኳ ፖዞ ሲበዛ ተጠራጣሪ የነበረ ቢሆንም በዋነኝነት የፈጠራ ያልሆነ ተግባራዊ እውነታ (Pragmatic) ላይ ጥገኛ የመሆን ባህሪ አሳይቷል፡፡ አሰልጣኙ በቴክኒክ የበቃ ቡድን እንደነበረው የማይታበል ሃቅ ነው፡፡ በተለይም ሞንቲን ወደ ቡድኑ ከመቀላቀሉ በፊት በ1931 ጣልያን ስኮትላንድን 3-0 ስታሸንፍ ይህን አረጋግጣለች፡፡ <ኮሪየሮ ዴላ ሴራ> ስለ እድለ ቢሶቹ ተጓዦች በሰራው ዘገባ ” ተጫዋቾቹ ፈጣኖች ናቸው፡፡ በአካል ብቃት ረገድ በአግባቡ የተዘጋጁ፣ ኳሷን በእግር አክርሮ በመምታትና በጭንቅላት በመግጨት የተካኑ ይሁኑ እንጂ በሜዳው ላይ ማራኪ ጨዋታ ከማሳየት አንጻር ገና ጀማሪዎች ይመስሉ ነበር፡፡” አለ፡፡ ይህ እንግዲህ ለየትኛውም ቡድን እንደ ጠንካራ ትችት ሊወሰድ ይችል ይሆናል፡፡ አጫጭር እና ጥልፍልፍ ያሉ ውስብስብ ቅብብሎች (Weaving-Pattern Passing) ላይ ተመስርተው እግርኳስን ሲጫወቱ ላደጉ ተጫዋቾች ግን ጋዜጣው ላይ የቀረበው ሒስ ከዘለፋና ማጥላላት ያላነሰ ተግባር ነው፡፡

በ1930 የመጀመሪያውን የጨዋታ ተሳትፎ ያደረገው የዚያን ጊዜው ታላቅ የመሃል አጥቂ ጁሴፔ ሜአዛ ሁሌም ከኮርማ ታጋዮች ጋር ይነጻጸር ነበር፡፡ የወቅቱ ዝነኛ ዘፈንም “በተመጠነ የጊዜ ልዩነት ፈጣንና ዝግ ያሉ የእግር ምቶችን ያዋሃደ አስደሳች የጭፈራ አይነትን በሚወክል ሙዚቃዊ ስልት ጎሎችን ያስቆጥራል፡፡” የሚል ይዘት ያለው ግጥም አካቶ አጥቂውን ያሞካሽ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ያ የጋለ ስሜት እና አስደሳች ድባብ ለረጅም ጊዜ አልዘለቀም፤ እንዲያውም በሌሎች ተጫዋቾች ብቃት ወዲያውኑ ደበዘዘ፡፡ ሜአዛ ዘይቤያዊ የፊት መስመር ተሰላፊ ሆኖ ቢሰነብትም የሲልቪዮ ፒዮላ፣ ራይሞንድ ኡርሲ እና ዢኖ ኮላውዚ የብቃት ደረጃ አስገራሚ ነበር፡፡ የአካል ብቃት እና አልሸነፍ ባይነት ደግሞ የጨዋታው ማዕከላዊ እሴቶች ሆኑ፡፡ በ1932 <ሎ ስታዲያ> በተባለ ጋዜጣ ርዕሰ አንቀጽ ላይ ” በፋሺስቶች የአገዛዝ ዘመን አስረኛ ዓመት አካባቢ ወጣቶቹ ለተጋድሎ ጠንክረው ተዘጋጁ፤ ግጥሚያዎችን ለማድረግም በረቱ፤ ከሁሉ በላይ ግን ለጨዋታው ትጉህነታቸውን አሳዩ፡፡ ወኔ፣ ቆራጥነት፣የተፋላሚነት ኩራት እና ከራሳችን ጋር የመወዳደር ስሜት ተለይቶን አያውቅም፡፡” የሚል ሃሳብ ያዘለ ጽሁፍ ወጣ፡፡

በእግርኳስ አጨዋወት የመከላከል ሒደት ውስጥ ተጫዋቾች-በ-ተጫዋቾች ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር እንዲደረግባቸው የሚፈቅደውን ስርዓት (Man Marking) በዋነኝነት ጥቅም ላይ ካዋሉት ቀደምት አሰልጣኞች መካከል ፖዞ አንዱ ነው፡፡ ይህም እግርኳስ አንድ ቡድን የራሱ ጨዋታ ላይ ብቻ የሚያተኩር ሳይሆን የተጋጣሚን እንቅስቃሴም እያጤነ ተቃራኒ ቡድን የተዘጋጀበትን አጨዋወት በአግባቡ እንዳይተግብር የሚያደርግ መሆኑን ያሳያል፡፡ በ1931 በቢልባኦ ስፔን ጣልያንን በወዳጅነት ጨዋታ ስትገጥም የፖዞው ሬናቶ ሴዛሪኒ ” የባላጋራ ቡድን የአስራ አንዱንም ተጫዋቾች መሪ በቁጥጥር ስል አውዬ ስኬታማ ከሆንኩ አጠቃላዩ የተጋጣሚ ቡድን መዋቅር ይንኮታኮታል፡፡” በሚል እውነታ ላይ ተመስርቶ  የባለሜዳዋን ሃገር ተጫዋች ኢግናሲዮ አግዊሬዛባላን ሲከታተለው ዋለ፡፡

ሰውን በሰው በማስያዝ የመከላከል ስልት መጠቀም የእግርኳስ አቀራረብ ውበታዊ ይዘት ላይ አብዝተው የሚያከሩትን ወገኖች (Purists) አሳሰበ፡፡ በ1934ቱ የአለም ዋንጫ ወቅት ደግሞ የፖዞ ቡድን ላይ የስነ ምግባር ጥያቄዎች መነሳት ጀመሩ፡፡ ከቶርናመንቱ አንድ ዓመት ቀደም ብሎ በመገለል መርሆዋቸው ከጸኑት እንግሊዞች ጋር 1-1 አቻ ከተለያዩ በኋላ ጣልያን በሜዳዋ የምታደርጋቸው ጨዋታዎች በሃገሪቱ ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ግጥሚያዎች መካከል ተመራጮቹ ሆኑ፡፡ በተለይ ደግሞ የዉንደርቲም ቡድን ሃያልነት ወደ መገባደጃው እየተቃረበ እንደመጣ በሚታሰብበት ጊዜ የጣልያናውያኑ ጨዋታ ተጠባቂነት ከፍ ወዳለ ደረጃ ተሸጋገረ፡፡ እይታውን አሉታዊ ነገሮች እየጋረዱት የነበረው ሜይዝልም የታላቁ ቡድን መጨረሻ መቃረቡን የሚያረጋግጥ ባህሪ ማሳየት ጀመረ፡፡ በግማሽ ፍጻሜው የዋናው ግብ ጠባቂ ሂደን አለመኖር እንደሚጎዳቸው ገለጸ፤ ከክለቦቻቸው ጋር በተለያዩ ሃገራት ግጥሚያዎችን ለማድረግ አድካሚ ጉዞዎች ያካሄዱት ተጫዋቾች የብቃታቸው ጥግ ላይ እንዳልሆኑ አሳወቀ፤ ቡድኑ አካላዊ ጥንካሬ እና ስነ ልቦናዊ ብርታት እንደሚያንሰው የሚያብራራው የእንግሊዛውያኑ የሰላ ሒስም ቆሽቱን አሳረረው፡፡ ብሪታኒያውያን የእግርኳስ ባለሙያዎች የወቅቱን የአርሰናል የመሃል አጥቂ ክሊፍ ባስቲንን ቢዋሳቸው ዉንደርቲም ወደ ድል ሊያመራ ይችል እንደነበር ገለጹ፡፡ በቡድኑ የፊት መስመር ላይ የነበረውን ችግርም አጋለጡ፡፡

በ1934ቱ የአለም ዋንጫ ግማሽ ፍጻሜ ጣልያንና ኦስትሪያ፥ ፖዞና ሜይዝል ተፋጠጡ፡፡ በእርግጥ የዚያኔ ለውድድሩ የተቸረው ግምት ወደ አዘቅት እየተምዘገዘገ  ነበር፡፡ ኦስትሪያ ስፖርታዊ ጨዋነትን ጥሳ በሩብ ፍጻሜው ሃንጋሪን ስትረታ  ከባድ ግጭት ውስጥ ተሳታፊ ሆነች፡፡ ይባስ ብሎ በተመሳሳይ እርከን በጣልያንና ስፔን መካከል የተደረገው ጨዋታ 1-1 አቻ ሲጠናቀቅ ውድድሩ ወደ የለየለት ረብሻ አመራ፡፡ ጥሩ ክህሎትን የታደለው ሞንቲ ለከባዱ ግብግብ ራሱን በጥሩ ሁኔታ አዘጋጅቶ ነበር፤ የስፔኑ ግብ ጠባቂ ሪካርዶ ዛሞራ ደግሞ በተደጋጋሚ በደረሰበት አደጋ በሚቀጥለው ቀን የተካሄደውን የድጋሚ ጨዋታ ለማድረግ እስከሚያቅተው ድረስ ተጎዳ፡፡ ሶስት አልያም አራት ተጫዋቾች በከፍተኛ ህመም ከሜዳ ለመውጣት መገደዳቸውን የሚዘግቡ ምንጮች የተለያዩ ምክንያቶችን ቢያቀርቡም ስፓኒያርዶቹን ይበልጥ ያንገበገባቸው በጁሴፔ ሜአዛ የጭንቅላት ግብ አማካኝነት 1-0 መሸነፋቸው ነበር፡፡

በሩብ ፍጻሜው የተጠበቀው የአጨዋወት ዘይቤ ፍጭት ደማቅ ድባብ አልታየበትም፡፡ ሲንድለር በሞንቲ ጥብቅ ክትትል ሲደረግበት ዋለ፤በመጀመሪያዎቹ አርባ ደቂቃዎች ኦስትሪያ ምንም አይነት የግብ ሙከራ ማድረግ አልቻለችም፡፡ ጁሴፔ ሜአዛ በጨዋታው ላይ በሂደን ተተክቶ የተሰለፈውን ግብ ጠባቂ ፒተር ፕላዘርን አልፎ ያቀበለውን ኳስ ሌላው የደቡብ አሜሪካ ተወላጅ ጣልያናዊ ኤንሪኮ ጉዋይታ ከመረቡ ጋር በቀላሉ አዋሃደውና ጣልያን በዚችሁ ጎል አሸነፈች፡፡ የዳኑቢያኑን እግርኳሳዊ አስተምህሮ ክብር ለማስጠበቅ በሌላ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ጀርመንን ከውድድሩ ውጪ ያደረገችው ቼኮስሎቫኪያ ቀረች፡፡ በፍጻሜው አልፎአልፎ ጣልያንን ስጋት ላይ የሚጥል እንቅስቃሴ ታደርግ ያዘች፡፡ ሰባ ስድስተኛው ደቂቃ ላይም በአንቶኒን ፐክ አማካኝነት የመምራት አጋጣሚ አገኘች፡፡ ፍራንቲሴክ ስቮቦዳ የግቡ ቋሚ መለሰበት፤ ጂሪ ሶቦትካ ደግሞ እጅግ ለግብነት የቀረበ እድል አመከነ፡፡ ጨዋታው ሊጠናቀቅ ስምንት ደቂቃ ሲቀር ኡርሲ አክርሮ ወደ ቼኮስሎቫኪያ የጎል ክልል የለጋት ኳስ ባልተለመደ አኳኋን አቅጣጫዋን ቀይራ ግብ ጠባቂው ፍራንቲሴክ ፒያንካን አለፈች፡፡ ጣልያን አቻ ሆነች፤ ጨዋታው ላይም በመጨረሻ ነፍስ ዘራችበት፡፡ በተጨማሪ ሰዓት ሰባተኛው ደቂቃ ላይ ሲያነክስ የከረመው ሜአዛ ከቀኝ መስመር ረዥም ኳስ አሻገረ፤ ጉዋይታ ተቀበለውና ለአንጌሎ ስቺያቮ አሳለፈለት፡፡ የመሃል አጥቂው ጆሴፍ ስቲሮኪን አልፎ ማሸነፊያዋን ግብ አስቆጠረ፡፡

አንጄሎ ከጨዋታው በኋላ ” ተስፋ ከመቁረጥ በሚመጣ ጥንካሬና ድፍረት ተገፋፍተን ነበር፡፡” ሲል ተናገረ፡፡ የሙሶሊኒ ጣልያን አንገብጋቢውን ድል አሳካች፤ ይሁን እንጂ በሁሉም አካባቢ የሰፈነውን ጀብድ ለመፈጸም የሚታይ ጉጉትና ብርታት እንዲሁም ራስን ዝቅ አድርገውም ቢሆን ያን ታላቅ ስኬት ለማሳካት የሄዱበት መንገድ ጎምዛዛ ጣዕም ትቶ አለፈ፡፡ ቤልጂየማዊው ዳኛ ጆን ላንጂነስ ” በአብዛኛዎቹ ሃገራት ዘንድ የአለም ዋንጫው እንደ ስፖርታዊ ውድቀት ተቆጥሯል፤ በሁሉም ስፖርታዊ ስነ-ምግባሮች አሸናፊ ሆኖ ለመገኘት የታየው ፈቃደኝነት አናሳ ነበር፡፡ ከሁሉ የከፋው ደግሞ አጠቃላይ የውድድሩ ድባብ ላይ ይህ መጥፎ መንፈስ አንዣቦ መዝለቁ ነው፡፡” በማለት በቶርናመንቱ የተስተዋለውን ስርዓት አልበኝነት ነቀፈ፡፡

በዚያው ዓመት ህዳር ወር ላይ እንግሊዝና ጣልያን በተገናኙበት ወቅት ጨዋታው በተጀመረ ሁለተኛው ደቂቃ ላይ ሞንቲ ከእንግሊዙ ቴድ ድሬክ ጋር ተጋጭቶ የእግሩ አጥንት ተሰበረ፡፡ የጣልያኖቹ አጸፋዊ ምላሽ እጅጉን መራር በመሆኑ ክስተቱ የ<ሃይብሪ ፍልሚያ> ተብሎ የሚጠራበትን ስያሜ አገኘ፡፡፡ “ለመጀመሪያውዎቹ አስራ አምስት ደቂቃዎች ሜዳው ላይ ሲካሄድ የነበረውን ጨዋታ  እግርኳስ ብሎ ለመጥራት ያስቸግራል፡፡ ጣልያናውያኑ በጣም ስለተሸበሩ እንደ እብድ ሆኑ፤ ሜዳ ላይ የሚንቀሳቀሰውን ማንኛውንም ነገር ይነርቱ ጀመር፡፡” ሲል ስታንሊ ማቲውስ ተናግሯል፡፡  እንግሊዛውያኑ የእነርሱን ስሜታዊ መሆን ተጠቀሙበትና 3-0 የመምራት አጋጣሚን ፈጠሩ፡፡ ይሁን እንጂ ቪቶሪዮ ፖዞ በእረፍት ሰዓት ቡድኑን ካረጋጋ በኋላ በጥሩ ተነሳሽነት ተጫውተው በሁለተኛው አጋማሽ ውጤቱን ወደ 3-2 አጠበቡት፡፡

ከጠብ አጫሪነታቸውና ተጠራጣሪነታቸው ውጪ ያለምንም ጥያቄ ጣልያኖች ባለክህሎት ነበሩ፡፡ ፖዞ የቡድኑ ጠንካራ ጎን ላይ እምነቱን ጥሎ በ1938 የአለም ዋንጫ አሸናፊነታቸውን በድጋሚ አረጋገጡ፡፡ አሁንም ግን የመከላከል አደረጃጀታቸው ዋነኛ ጥንካሬያቸው እንደሆነ ታየ፡፡ “የጣልያን ቡድን ሃያልነት ትልቁ ምስጢር የመስመር ተከላካዮቹን ቀዳሚ የመከላከል ሚና ሳያስተጓጉል በጥቂት የፊት መስመር ተሰላፊዎች ብቻ የማጥቃቱን ሒደት መምራት መቻሉ ነው፡፡” ብሎ ጋዜጠኛው ዛፓ ጽፏል፡፡ ያኔ ኦስትሪያ በጀርመን ተጠቃላ ተይዛ ነበር፤ ቀደም ሲል በተካሄዱ የአለም ዋንጫዎች ከሁለት የግማሽ ፍጻሜ ተፋላሚዎች የተውጣጡ ተጫዋቾችን ያካተተው ቡድን አመርቂ መግባባትን ሊያሳይ አልቻለም፡፡ በመልሱ ጨዋታ በካርል ራፐኑ ሲውዘርላንድ ተሸንፎ በመጀመሪያ ዙር ከውድድሩ ተሰናበተ፡፡ ቼኮስሎቫኪያም በብራዚል ተረታችና ከመጨረሻዎቹ ስምንት ቡድኖች ውጪ ሆነች፡፡ ኦስትሪያ ግን የአጨዋወት ዘይቤያቸውን በዳኑቢያኑ መርህ ባደረጉት ቡድኖችና በቪቶሪዮ ፖዞ መካከል እስከሚደረገው የመጨረሻ ጨዋታ ድረስ ዘለቀች፡፡ አሁንም ጣልያኖቹ በጣም ፈጣንና ቀልጣፋ መሆናቸውን አስመሰከሩ፡፡ የዘር ሃረጉ ከወደ ጣልያን የሚመዘዘው ደቡብ አሜሪካዊ/ኡሪየንዶ (Uriondo)/ ሚሼሌ አንድሪኦሎ ሞንቲን ተክቶ በመሃል ተከላካይ-አማካይነት (Centre-Half/Centro Mediano) ሚና የሃንጋሪውን ወሳኝ የመሃል አጥቂ ጂኦርጂ ሳሮሲን ጥብቅ ቁጥጥር ሲያደርግበት ቆየ፡፡ የሜይዝል እግርኳሳዊ አረዳድ፣ የጨዋታ አቀራረብ እና የቡድኑ ትግበራዊ አካሄድም ስንፍና የተጫጫነውና ጊዜው ያለፈበት መስሎ ታየ፡፡

ኃያልነታቸው እያከተመ ለመጡት ሃገራት “እንዴት ብንጫወት ነው የሚበጀን?” የሚል ምሬት አዘል ጥያቄ ሳያስነሳ የሚታለፍ አልነበረም፡፡ ፈረንሳዊው ጋዜጠኛ ዢያን እስኬናዚም ተመሳሳዩን መጠይቅ አቀረበ፡፡ ” ጨዋታውን እንውደደው ወይስ ወዲያ እንበለው?” መልስ ሳያገኝ የቀረ ጥያቄ ሆነ፡፡

ይቀጥላል...


ስለ ደራሲው 

ጆናታን ዊልሰን ዝነኛ እንግሊዛዊ የስፖርት ጋዜጠኛ ሲሆን በተለያዩ ጋዜጦች፣ መጽሄቶች እና ድረገጾች ላይ ታክቲካዊና ታሪካዊ ይዘት ያላቸው የእግርኳስ ትንታኔዎችን የሚያቀርብ ጉምቱ ጸኃፊ ነው፡፡  ባለፉት አስራ ሁለት ዓመታትም የሚከተሉትን ዘጠኝ መጻህፍት ለህትመት አብቅቷል፡፡

Behind The Curtain: Travels in Eastern European Football (2006)

Sunderland: A Club Transformed (2007)

Inverting the Pyramid: The History of Football Tactics (2008)

The Anatomy of England (2010)

Brian Clough: Nobody Ever Says Thank You: The Biography (2011)

The Outsider: A History of the Goalkeeper (2012)

The Anatomy of Liverpool (2013)

Angels With Dirty Faces: The Footballing History of Argentina (2016)

The Barcelona Legacy: Guardiola, Mourinho and the Fight For Football’s Soul (2018)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *