ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ሲዳማ ቡና ከ ወላይታ ድቻ

በገለልተኛ ሜዳ በሚደረገው የሲዳማ እና ድቻ ጨዋታ ዙሪያ የሚያተኩረው ዳሰሳችንን እንሆ…

ሲዳማ ቡና እና ወላይታ ድቻ እንደመጀመሪያው ዙር ሀሉ አሁንም ጨዋታቸውን አዲስ አበባ ስታድየም ላይ ነገ ከ 11፡00 ጀምሮ ያደርጋሉ። ሁለቱ ቡድኖች በመካከላቸው ካለው ፉክክር ባለፈ በሰንጠረዡ ላይ እና ታች ላይ ባሉበት ፉክክር የሚጠቅማቸውን ጨዋታም ነው የሚያከናውኑት።

ሁለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ሲዳማ ቡና መቐለ ዛሬ ነጥብ መጣሉን ተከትሎ የዘጠኝ ነጥብ ልዩነቱን ወደ ሦስት ዝቅ ለማድረግ ይጫወታል።  ከዚህ ባለፈም ሳምንት በፋሲል ከነማ ከደረሰበት ሽንፈት በፍጥነት ማገገም ሲጠበቅበት ከተከታዩ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያለውን የአንድ ነጥብ ልዩነት ለማስፋትም የነገው ጨዋታ እጅግ ወሳኝ ነው። ሲዳማ ቡና በነገው ጨዋታ አበባየው ዮሀንስ እና ጫላ ተሺታን በጉዳት የማይጠቀም ሲሆን መሀመድ ናስር ከቅጣት ይመለስለታል።

የደቡብ ፖሊስን ግስጋሴ ተከትሎ ራሱን በወራጅ ቀጠናው ውስጥ ያገኘው ወላይታ ድቻ የነገው ጨዋታ ወደ 11ኛነት ከፍ ለማለት በእጅጉ የሚያስፈልገው ነው። ምንም የቅጣትም ሆነ የጉዳት ዜና የሌለበት ድቻ ቦታውን ለመከላከያ አስረክቦ ከአደጋው ክልል ፈቀቅ ለማለት ላለፉት አምስት ጨዋታዎች ግብ እያስቆጠረ መምጣቱ እና በተለይም የአጥቂው ባዬ ገዛኸኝ መልካም አቋም ላይ መገኘት ተጠቃሚ ያደርገዋል።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 11 ጊዜ ተገናኝተው ድቻ አንድ ጨዋታ ሲያሸንፍ ፣ በአራት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል። ሲዳማ ቡና ደግሞ 6 ጊዜ አሸንፏል። በጨዋታዎቹ ድቻ 5  ሲዳማ ደግሞ 11 ጎሎች አስቆጥረዋል።
                                                                             

– ወላይታ ድቻ ሲዳማ ቡና ላይ ካስመዘገበው ብቸኛው የ2007ቱ የ2-1 ድል በኋላ ማሸነፍ አልቻለም።

– ዘንድሮ በመጀመሪያው ዙር በተመሳሳይ ሁለቱን ቡድኖች አዲስ አበባ ስታድየም ያገናኘው ጨዋታ በሲዳማ ቡና 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ዳኛ

– ጨዋታው በኢንተርናሽል ዳኛ  አማኑኤል ኃይለሥላሴ የመሀል ዳኝነት ይመራል። አርቢትሩ እስካሁን ሰባት ጨዋታዎች 24  የቢጫ ካርዶች እና ሦስት የፍፁም ቅጣት ምቶች ሰጥቷል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ሲዳማ ቡና (4-3-3)

መሳይ አያኖ

ግሩም አሰፋ – ሰንደይ ሙቱኩ – ግርማ በቀለ – ሚሊዮን ሰለሞን

ወንድሜነህ ዓይናለም – ዮሴፍ ዮሃንስ – ዳዊት ተፈራ 

አዲሱ ተስፋዬ – መሀመድ ናስር –  አዲስ ግደይ

ወላይታ ድቻ (4-2-3-1)

መኳንንት አሸናፊ

እሸቱ መና – ተክሉ ታፈሰ – ውብሸት ዓለማየሁ –  ያሬድ ዳዊት

በረከት ወልዴ – ኃይማኖት ወርቁ

ቸርነት ጉግሳ – አብዱልሰመድ ዓሊ – ፀጋዬ አበራ

ባዬ ገዛኸኝ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *