አፍሪካ | ራጃ ካሳብላንካ የካፍ ሱፐር ካፕ አሸናፊ ሆኗል

የ2018 ካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ አሸናፊ የሆነው የሞሮኮው ራጃ ካሳብላንካ የቻምፒየንስ ሊግ ባለ ድሉ የቱኒዚያው ኤስፔራንስን 2-1 በማሸነፍ በታሪኩ ለሁለተኛ ጊዜ የመድረኩን ክብር አሳክቷል። በዶሀ የተደረገው ይህ ጨዋታ በኢትዮጵያዊው ዳኛ ባምላክ ተሰማ መሪነት ነበር የተካሄደው።
በታኒ ቢን ጃሲም ስታድየም ምሽት 1:00 ላይ የተደረገው ጨዋታ በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ከአህጉሪቱ ውጪ በ2022 ዓለም ዋንጫ አስተናጋጇ ሀገር እንደመካሄዱ የበርካቶችን ትኩረት መሳብ ችሏል።


ራጃ በ22ኛው ደቂቃ አብዱላሂ ሀፊዲ ባስቆጠረው ጎል ቀዳሚ ሲሆኑ ቀጥሎ ባሉት ደቂቃዎችም የላይነቱን መውሰድ ችለው ነበር። ሆኖም ዮስፍ ቤላይሊ በ57ኛው ደቂቃ ኤስፔራንስን አቻ አድርጓል። በ65ኛው ደቂቃ ደግሞ አምበሉ ባድር ቤናውን የራጃን አሸናፊነት ያረጋገጠች ጎል አስቆጥሯል።

ድሉን ተከትሎ የካሳብላንካው ታላቅ ክለብ ራጃ አትሌቲክ ከ19 ዓመታት በኋላ ከሱፐር ካፕ ድል ጋር ሲገናኝ በኅዳር ወር የአል አህሊ አሰልጣኝ በነበሩበት ወቅት በቻምፒየንስ ሊግ ፍፃሜ በኤስፔራንስ ተሸንፈው ከስራቸው የተሰናበቱት የአሁኑ የራጃ አሰልጣኝ ፓትሪስ ካርቴሮን ሽንፈታቸውን ተበቅለዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *