ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ድሬዳዋ ከተማ ከ መከላከያ

ነገ ከሚደረጉ ሰባት ጨዋታዎች መካከል የድሬዳዋ እና የመከላከያ ጨዋታ የመጀመሪያው የቅድመ ዳሰሳችን ትኩረት ነው።

በአንድ ነጥብ ልዩነት በሊጉ ሰንጠረዥ የታችኛው ፉክክር ውስጥ የሚገኙት ድሬዳዋ ከተማ እና መከላከያ ነገ 09፡00 ላይ በድሬዳዋ ይገናኛሉ። ከሜዳቸው ውጪ ሀዋሳ ላይ ካሳኩት ድል በኋላ ተቀዛቅዘው የቆዩት ድሬዎች ኢትዮጵያ ቡናን በመርታት ሁለተኛውን ዙር ቢጀምሩም ደቡብ ፖሊስን ለመግጠም ዳግም ወደ ሀዋሳ ባደረጉት ጉዞ ግን ውጤት አልቀናቸውም። በውድድሩ አጋማሽ የአማካይ ክፍላቸውን ለማጠናከር ዝውውሮችን የፈፀሙት ብሩቱካናማዎች ልምድ ያላቸው ምንያህል ተሾመ እና ኤልያስ ማሞን በቶሎ ወደ መጀመሪያ አሰላለፋቸው በማስገባት የመሀል ክፍላቸውን አዲስ አይነት መልክ ለማላበስ እየጣሩ ነው። ድሬዎች በዚህ ሳምንት የፈፀሟቸው የያሬድ ዘውድነህ እና ኤርሚያስ ኃይሉ ዝውውሮች ሙሉ ለሙሉ በመጠናቀቃቸውም ከመጀመሪያው ዙር በተሻለ የተጫዋች አማራጮቻቸው ሰፍተው ይታያሉ። ከዚህ በተጨማሪ ናሚቢያዊው አጥቂ ኢታሙና ኬይሙኒም ከብሔራዊ ቡድን ግልጋሎት መልስ ቡድኑን እንደሚያገለግል ሲጠበቅ በተቃራኒው በረከት ሳሙኤል በቅጣት ሳሙኤል ዮሀንስ እና ፍቃዱ ደነቀ ደግሞ በጉዳት ከጨዋታው ውጪ ሆነዋል።

በአዲስ አበባ ስታድየም ሁለት ተከታታይ ሽንፈቶችን ያስተናገደው መከላከያ የቁልቁል ጉዞውን ቀጥሎ በወራጅ ቀጠናው ውስጥ ተገኝቷል። መጠነኛ መሻሻል ታይቶበት የነበረው የቡድኑ የመለላከል ሂደትም ሆነ በቀላሉ ተፅዕኖ ውስጥ የሚገባው የአማካይ ክፍሉ እንዲሁም ግብ ማስቆጠር እየተሳነው የሚገኘው የአጥቂ መስመሩ ከተደጋጋሚ የተጫዋቾች መቀያየር ጋር ተዳምሮ ጦሩን ደካማ አድርጎታል። በነገውም ጨዋታ በተደጋጋሚ እየተቋረጠ ለጥቃት የሚያጋልጠውን ደካማ የኳስ ቁጥጥር ካላስተካከለ ወደ መከላከል ከሚደርገው ደካማ ሽግግር አንፃር ለጥቃት መጋለጡ የሚቀር አይመስልም። ከነገው ጨዋታ በፊት ለአሰልጣኝ ስዩም ከበደ ትልቅ እፎይታ የሚሆነው ዜና የመሀል ሜዳውን ሚዛን የሚጠብቀው ቴዎድሮስ ታፈሰ ከኦሊምፒክ ቡድኑ መመለስ ሲሆን በተመሳሳይ ፍቃዱ ደነቀም ጉዳት ለበዛበት የአጥቂ ክፍሉ ተጨማሪ አማራጭ ይሆናል። ከዚህ ውጪ ተመስገን ገብረኪዳንም ያገገመ ሲሆን ምንይሉ ወንድሙ ግን አሁንም ጉዳት ላይ ይገኛል።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ሁለቱ ክለቦች እስካሁን 15 ጊዜ የተገናኙ ሲሆን መከላከያ ከፍተኛ የበላይነት አለው። በዚህም ድሬዳዋ ሁለት ጊዜ ብቻ ሲያሸንፍ መከላከያ 9 ጊዜ አሸንፏል። ቀሪዎቹ 4 ጨዋታዎች በአቻ ውጤት የተለያዩባቸው ነበሩ። መከላከያ 25 ፣ ድሬዳዋ 11 ጎሎች አስመዝግበዋል።

– ድሬዳዋ ከተማ ከተማ ሜዳው ላይ ስምንት ጨዋታዎችን ያደረገ ሲሆን አራት የሽንፈት ፣ ሦስት የድል እና አንድ የአቻ ውጤት አስመዝግቧል።

– ሰባት ጊዜ ከአዲስ እበባ የወጣው መከላከያ ሁለት ጊዜ በድል ሲመለስ በቀሪዎቹ ጨዋታዎች ሦስት የሽንፈት እና ሁለት የአቻ ውጤቶች ገጥመውታል።

ዳኛ

– ኢንተርናሽናል ዳኛ ለሚ ንጉሴ ይህን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት ይመራዋል። ለሚ በአምስት ጨዋታዎች 16 የቢጫ ካርዶች እና አንድ የፍፁም ቅጣት ምት ውሳኔዎችን አሳልፏል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ድሬዳዋ ከተማ (4-ሳምሶን አሰፋ

ገናናው ረጋሳ – አንተነህ ተስፋዬ – ፍሬድ ሙሺንዲ – ዘነበ ከበደ

ረመዳን ናስር – ሚኪያስ ግርማ – ምንያህል ተሾመ – ሬምኬል ሎክ

ሀብታሙ ወልዴ – ኢታሙና ኬይሙኒ

መከላከያ (4-4-2 ዳይመንድ)

አቤል ማሞ

ሽመልስ ተገኝ – አዲሱ ተስፋዬ – አበበ ጥላሁን – ታፈሰ ሰረካ

ቴዎድሮስ ታፈሰ

ዳዊት ማሞ – ፍሬው ሰለሞን

ዳዊት እስጢፋኖስ

ፍፁም ገብረማርያም – ፍቃዱ ደነቀ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *