ሪፖርት | ወልዋሎዎች ወደ መሪዎቹ የሚያስጠጋቸውን ድል አስመዘገቡ

ወልዋሎ ሪችሞንድ አዶንጎ ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ መከላከያን አሸንፎ ወደ ሊጉ መሪዎች የሚያስጠጋውን ድል አስመዝግቧል።

ባለሜዳዎቹ ባለፈው ሳምንት ደቡብ ፖሊስን ካሸነፈው ስብስባቸው ክሪስቶፈር ችዞባ፣ ብርሃኑ አሻሞ፣ አብዱልራህማን ፉሴይኒን በማሳረፍ ሪችሞንድ አዶንጎ፣ ኤፍሬም ኃይለማርያም እና እንየው ካሳሁንን ተክተው ወደ ሜዳ ሲገቡ እንግዶቹ መከላከያዎች ባለፈው ሳምንት በደደቢት ሽንፈት ከገጠመው ስብስባቸው አበበ ጥላሁን ፣ ሳሙኤል ታዬ እና አቤል ማሞ አስወጥተው በይድነቃቸው ኪዳኔ ፣ አዲሱ ተስፋየ እና ተመስገን ገብረኪዳን ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል።

ሳቢ ያልሆነ እንቅስቃሴ እና ጥቂት የግብ ሙከራዎች በታዩበት ጨዋታ የግብ ሙከራ በማድረግ ቅድሚያውን የያዙት ቢጫ ለባሾቹ ሲሆኑ ሪችሞንድ አዶንጎ የመከላከያ ተከላካዮች ስህተት ተጠቅሞ ያገኘው ዕድል ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

በመጀመርያዎቹ አስር ደቂቃዎች ከባለሜዳዎቹ በተሻለ የኳስ ቁጥጥር ማሳካት የቻሉት መከላከያዎች ብልጫ በወሰዱባቸው ደቂቃዎች የፈጠሩት ይህ ነው የሚባል ዕድል አልነበረም።
በአንፃሩ ቀስ በ ቀሰ ወደ ጨዋታው ቅኝት የገቡት ወልዋሎዎች ጫና በፈጠሩባቸው ደቂቃዎች ሁለት ያለቀላቸው ዕድል ፈጥረው ነበር። በተለይም እንየው ካሳሁን ከመስመር አሻምቶት ነፃ አቋቋም የነበረው ኤፍሬም አሻሞ መቶት ይድነቃቸው ኪዳኔ በድንቅ ብቃት ያዳናት ወልዋሎዎች መሪ ለማድረግ የተቃረበች ሙከራ ነበረች። ወልዋሎዎች ለግብ የቀረበ ሙከራ ካደረጉ ብዙም ሳይቆዩ በጋናዊው አጥቂ ሪችሞንድ አዶንጎ መሪ መሆን ችለዋል። አጥቂው አማኑኤል ጎበና በግሩም ሁኔታ ያሻገረለትን ኳስ በደረቱ አብርዶ በጥሩ ሁኔት በማስቆጠር ነበር ቡድኑን መሪ ማድረግ የቻለው።
ወልዋሎዎች ከግቡ በኃላም በአማኑኤል እና ሬችሞንድ ጥሩ ተግባቦት ሌላ ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ ችለው ነበር።

በመጀመርያው አጋማሽ ይህ ነው የሚባል ሙከራ ማድረግ ያልቻሉት መከላከያዎች በመጨረሻው ደቂቃ በሽመልስ ተገኝ አማካኝነት ከርቀት ሙከራ ቢያደርጉም ኳሷ ዓብዱልዓዚዝ ኬይታን የፈተነች አልነበረችም።

በአንፃራነዊ ከመጀመርያው አጋማሽ የተሻሉ ሙከራዎች የታዩበት ሁለተኛው አጋማሽ የጦሩ ብልጫ የታየበት ነበር። ሆኖም እንደመጀመርያው አጋማሽ ሁሉ ጠንካራ ለግብ የቀረበ ሙከራ ያደረጉባቸው ጊዜያቶች ጥቂት ነበሩ። አዲሱ ተስፋዬ በረጅሙ አሻምቶት ፍቃዱ ዓለሙ በግንባሩ ባደረገው ሙከራ ጥቃታቸው የጀመሩት መከላከያዎች ምንም እንኳ በብዙ መለኪያዎች ከባለሜዳዎቹ ተሽለው ቢታዩም ጠንቃቃው እና ወደ ራሱ ሳጥን ተጠግቶ የሚከላከለውን የወልዋሎ ተከላካይ ክፍል አልፈው ሙከራ ማድረግ አልሆነላቸውም።

በኳስ ቁጥጥር ብልጫ የተወሰደባቸው ወልዋሎዎች በግብ ሙከራ እና ንፁህ የግብ ዕድል በመፍጠር የተሻሉ ነበሩ። በተለይም በጥሩ ወቅታዊ ብቃት የሚገኘው ፕሪንስ ሰቨሪንሆ በሁለት አጋጣሚዎች ከርቀት ያደረጋቸው ሙከራዎች እና አማኑኤል ጎበና ያደረገው ሙከራ የተሻለ ለግብ የቀረቡ ነበሩ።

በርካታ የዳኝነት ስህተቶች በታዩበት የመጨራሻዎቹ አስር ደቂቃዎች የመከላከያ ተጫዋቾች እና የአሰልጣኞች ቡድን ቅሬታቸው ሲያሰሙ ተስተውለዋል። መከላከያዎች በመጨረሻዎቹ 10 ደቂቃዎች የበላይነቱን በመውሰድ በሶስት አጋጣሚዎች አቻ ለመሆን ተቃርበው ነበር። ፍሬው ሰለሞን ከዳዊት እስጢፋኖስ የተላከለት ኳስ ሞክሮ ኬይታ በጥሩ ሁኔታ የመለሰው እና ዳዊት እስጢፋኖስ ከቅጣት ምት ያደረገው ጥሩ ሙከራ ይጠቀሳሉ።

ጨዋታው በዚህ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ መከላካካዎች ተከታታይ ሽንፈቶች አስተናግደው ወደ ወራጅ ቀጠናው ይበልጥ ሲጠጉ ተከታታይ ድሎች ያስመዘገቡት ወልዋሎዎች ነጥባቸው ከመሪዎቹ ጋር ማቀራረብ ችለዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡