ሪፖርት | ደቡብ ፖሊስ እና ወላይታ ድቻ ነጥብ ተጋርተዋል

ከ21ኛ ሳምንት መርሐ ግብር መካከል የቦታ ለውጥ ተደርጎበት አዲስ አበባ ላይ በዝግ ስታድየም የተከናወነው የደቡብ ፖሊስ እና ወላይታ ድቻ ጨዋታ ያለግብ ተጠናቋል።

ደቡብ ፖሊስ በ20ኛው ሳምንት ወደ ጎንደር አቅንቶ ከፋሲል ከነማ ጋር 1-1 ከተለያየው ቀዳሚ አሰላለፍ ውስጥ ዘነበ ከድር እና ብሩክ አየለን በማሳረፍ በምትካቸው አበባው ቦታቆ እና ኪዳኔ አሰፋን ተጠቅሟል። በወላይታ ድቻ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያ ቡናን 2-1 ከረታው ቡድን ውስጥ ዐወል አብደላ ፣ አብዱልሰመድ ዓሊ እና ባዬ ገዛኸኝ ምትክ ሄኖክ አርፌጮ ፣ ፍፁም ተፈሪና እና አንዱዓለም ንጉሴ ጨዋታውን ጀምረዋል።

ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ በታየበት የመጀመሪያ አጋማሽ ቡድኖቹ በርካታ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ባይችሉም ጠንካራ ፉክክር ማሳየት ችለዋል። በአመዛኙ መሀል ሜዳ ላይ ባመዘነው የቡድኖቹ ፍልሚያ ወደ ግብ ለመድረስ የተለያዩ መንገዶችን ተጠቅመዋል። የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ይዘው ይታዩ የነበሩት ደቡብ ፖሊሶች ከኪዳኔ አሰፋ እና ዘላለም ኢሳያስ የመሀል ሜዳ ጥምረት በሚመነጩ ኳሶች ወደ ድቻ የግብ ክልል ቀርበው ቢታዩም ግልፅ የግብ ዕድል መፍጠር አልቻሉም። ይልቁኑም ከአማካይ ክፍላቸው በሚነሱ ኳሶች በድንገት የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችን የፈጠሩት ድቻዎች ወደ ፖሊሶች ሳጥን መግባት ችለው ነበር። ከነዚህ ዕድሎች ውስጥ 36ኛው ደቂቃ ላይ ፍፁም ተፈሪ ከመሀል ሜዳ ያሳለፈለትን ኳስ ይዞ ሳጥን ውስጥ የተገኘው አንዷአለም ንጉሴ በሚገባ መቆጣጠር ሳይችል ቀርቶ ዕድሉን አባክኗል። ከደቂቃዎች በፊትም ቸርነት ጉግሳ በተመሳሳይ ከግብ ጠባቂ ጋር የመገናኘት ዕድል የነበረው ቢሆንም ቀድሞ የደረሰው ሐብቴ ከድር አድኖበታል።

በሁለተኛው አጋማሽ ቡድኖቹ የሚያጠቁበትን መንገድ ተቀያይረው ታይተዋል። ከዕረፍት በፊት በአጫጭር ቅብብሎች ወደ ፊት ለመድረስ ጥረት ያደርጉ የነበሩት ፖሊሶች ራሳቸውን ለመልሶ ማጥቃት አመቻችተው ሲመለሱ ድቻዎች ደግሞ በአመዛኙ ኳስ ይዘው እና ብልጫ ወስደው ተጫውተዋል። ይሁን እንጂ የፖሊስን የኋላ መስመር አልፈው ሀብቴን በመፈተኑ ድቻዎች ከብዷቸው ታይቷል። 61ኛው እና 71ኛው ደቂቃዎች ላይ በቸርነት ጉግሳ ያደረጉት ሙከራም ከሳጥኑ ጠርዝ ላይ የተደረጉ ነበሩ። የተለመደው የመስመር አጥቂዎቻቸውን ቅልጥፍና ማግኘት ያልቻሉት ደቡብ ፖሊሶችም 60ኛው ደቂቃ ላይ ሄኖክ አየለ በረጅሙ የደረሰውን ኳስ በግብ ጠባቂው አናት ላይ አሳልፎ ለማስቆጠር ከሞከረበት እና ከአበባው ቡታቆ ቅጣት ምት ውጪ ተጋጣሚያቸውን እምብዛም ማስጨነቅ አልቻሉም። ፊት መስመራቸው ላይ ቅያሪዎችን በማድረግ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች የተሻለ ጫና የፈጠሩት ድቻዎች ተቀይሮ የገባው እዮብ ዓለማየሁ በተሰለፈበት የቀኝ መስመር በኩል ደጋግመው ጥቃት ቢሰነዝሩም ጨዋታው ግብ ሳይቆጠርበት 0-0 ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎም ቡድኖቹ በሰንጠረዡ የነበሩበት ቦታ ላይ ለውጥ ሳያደርጉ ወላይታ ድቻ 12ኛ ደቡብ ፖሊስ ደግሞ 13ኛ ደረጃ ላይ ረግተዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡