ሪፖርት | ደቡብ ፖሊስ አዳማን በመርታት ላለመውረድ በሚያደርገው ትንቅንቁን ቀጥሏል

በ23ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላለመውረድ ትግል እያደረገ ያለው ደቡብ ፖሊስ ሀዋሳ ላይ አዳማ ከተማን አስተናግዶ 2-0 በሆነ ውጤት አሸንፏል።

በ22ኛው ሳምንት ወደ ባህርዳር አምርቶ ከባህርዳር ከተማ ጋር ነጥብ ተጋርቶ የመጣው ደቡብ ፖሊስ የአራት ተጫዋቾችን ለውጥ ያደረገ ሲሆን በዚህም መሠረት ሐብቴ ከድር፣ አዳሙ መሐመድ፣ አበባው ቡጣቆ እና ላኪ ሰኒን በማስወጣት በምትኩ መክብብ ደገፉ፣ ደስታ ጊቻሞ፣ ዘነበ ከድር እና ዮናስ በርታን ሲጠቀሙ ኢትዮጵያ ቡና ላይ ድልን አስመዝግቦ የመጣው አዳማ ከተማ በተመሳሳይ የአራት ተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ በዛሬው ጨዋታ የመጀመርያ ተሰላፊ የነበረው እና ወደ ሜዳ ሊገቡ ሲሉ እግሩ ላይ ጉዳት ያጋጠመው ሮበርት ኦዶንካራ በጃኮ ፔንዜ ቀይረው ያስገቡ ሲሆን መናፍ ዐወልን በሱለይማን ሰሚድ፣ ኤፍሬም ዘካሪያስን በብሩክ ቃልቦሬ፣ ከነዓን ማርክነህን በበረከት ደስታ ለውጠው ወደ ሜዳ ገብተዋል፡፡

በመጀመሪያ አጋማሽ ባለሜዳዎቹ ደቡብ ፖሊሶች ካለባቸው የመውረድ ስጋት ለመላቀቅ ማጥቃት ብቻ ምርጫቸውን በማድረግ ዘላለም ኢሳይያስ ማዕከል አድርገው የቀኝ እና የግራ መስመር አጥቂዎቻቸውን አነጣጥረው ሲጫወቱ ተስተውሏል። በተለይም ደግሞ የዛሬው ጨዋታ ልዩነት ፈጣሪ ከዚህ ቀደም የቀኝ ተከላካይ የነበረው ብርሀኑ በቀለ ወደ ፊት ተስቦ በመጫወቱ ደቡብ ፖሊስን ተጠቃሚ አድርጎታል። እንግዳዎቹ አዳማዎች ደግሞ ከአዲስ ህንፃ በሚነሱ ኳሶች እና ኳስ በሚያገኙበት አጋጣሚ ሁሉ በረጅም እያሻገሩ ለቡልቻ ሹራ በማድረስ ወደ መስመር አጋድለው ሲያጠቁ ተስተውሏል። አዳማዎች አራት የመከላከል ባህሪ ያላቸውን የአማካይ ተጫዋቾችን በመጠቀማቸው ምክንያት በዘላለም ኢሳይያስ የሚመራው የደቡብ ፖሊስ የመሀል ሜዳ የበላይነት ነበረው። 7ኛው ደቂቃ ላይ አዲስ ህንፃ ሁለት ተጫዋቾችን አልፎ ለበረከት ደስታ አቀብሎት አመቻችቶ ሳጥን ውስጥ ለነበረው ሱለይማን ሰሚድ ሰጥቶት ቢሞክረውም መክብብ ደገፉ የተቆጣጠራት ኳስ የእንግዳዎቹ የጥቃታቸው ጅማሬ ነበረች። ባለሜዳዎቹ 10ኛ ደቂቃ ላይ ከሄኖክ አየለ ያገኘውን ኳስ ተጠቅሞ ብርሀኑ በቀለ በቀኝ የሳጥኑ ጠርዝ ሆኖ አክርሮ የመታት ኳስ ጃኮ ፔንዜ በግሩም ሁኔታ ተቆጣጥሯታል። ከዚህች ሙከራ በኋላ ከሳጥን ውጭ ሄኖክ አየለ አክርሮ መትቷት ጃኮፔንዜ ያዳናት ኳስ ለግብ የተቃረበች ሙከራ ነበረች።

ከቅርብ ጊዚያት ወዲህ ምርጥ ብቃቱን እያሳየ ያለው የመሀል ተከላካዩ ደስታ ጊቻሞ ከመከላከሉም ባሻገር የሚያገኛቸውን ነፃ ኳሶች ወደፊት እያሻገረ በአዳማ ግብ ክልል ላይ ጫና እንዲፈጠር ሲያደርግ የታየ ሲሆን በተደጋጋሚ በግሉ የአዳማን አጥቂዎች ተቆጣጥሮ የያዘበት መንገድ ከተመልካቹ ተደጋጋሚ የአድናቆት ድምፆች ሲቸሩት ታይቷል። 27ኛው ደቂቃ ደስታ ከራሳቸው የግብ ክልል ወደ አዳማ የግብ ክልል በረጅሙ ያሻገረውን ኳስ ብርሃኑ በቀለ የጃኮብ ፔንዝን መውጣት አይቶ በጭንቅላቱ ገጭቶ ለጥቂት በአግዳሚው ላይ የወጣችበት ኳስ ለደቡብ ፖሊሶች የምታስቆጭ ሙከራ ነበረች። 31ኛው ደቂቃ ላይ ኳስ ከሚጀመርበት መሀል ሜዳ ዘላለም ኢሳይያስ ለቀኝ መስመር አጥቂው ብርሀኑ በቀለ ጥሩ የተመጠነች ኳስ አሻግሮለት አብርዶ በቀኝ የሳጥኑ ጠርዝ ሰብሮ በመግባት ለሄኖክ አየለ አቀብሎት በግሩም አጨራረስ ሄኖክ ወደ ግብነት ቀይሮ ፖሊስን መሪ ማድረግ ችሏል።

የሚያገኛቸውን ኳሶች በተገቢው መንገድ ለአጥቂዎች ሲያደርስ የነበረው እና የደቡብ ፖሊስ መሀል ሜዳ ሚዛኑን እንዲጠብቅ አድርጎ በጎሎች ቀጥተኛ አስተዋፅኦ የነበረው ዘላለም ኢሳይያስ 42ኛው ደቂቃ ከብርሃኑ በቀለ ጋር ማራኪ አንድ ሁለት ተቀባብሎ ያመቻቸለትን ብርሃኑ በቀለ የጃኮ ፔንዜን መዘናገት ተጠቅሞ ግብ በማድረግ ልዩነቱን ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችሏል። አዳማዎች በጨዋታው መገባደጃ ቡልቻ ሹራ ያገኘውን ነፃ ኳስ በቀጥታ ወደ ግብ ሞክሮ መክብብ ደገፉ አድኖበታል። በደቡብ ፖሊስ 2-0 መሪነት ለእረፍት ወጥተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ደቡብ ፖሊስ በማጥቃታቸው ሲቀጥሉ እንደ መጀመሪያው ግማሽ ግን አስፈሪ አልነበሩም። በአንፃሩ አዳማዎች ደግሞ የተወሰደባቸው ብልጫ ለማስመለስ እስማኤል ሳንጋሪን በኤፍሬም ዘካርያስ እና ሙሉቀን ታሪኩን በዱላ ሙላቱ በተከታታይ ሁለት ቅያሪን በማድረግ ለማጥቃት አስበው ቢገቡም እንግዳዎቹ ብልጫውን መመለስ ግን አልቻሉም። ከቅያሪው በኋላ አልፎ አልፎ እድሎች ሲፈጥሩ የነበሩት አዳማዎች 60ኛው ደቂቃ ኤፍሬም ዘካርያስ ከሱለይማን መሐመድ ያገኛትን ኳስ ተጠቅሞ በግራ መስመር በኩል አክርሮ የመታትን ኳስ ግብ ጠባቂው መክብብ ደገፉ በገሩም ሁኔታ ተወርውሮ ለጥቂት ነክቶ በቀኝ ቋሚው የወጣበት አዳማዎች የመጀመሪያ ግባቸውን የሚያገኙበት አጋጣሚ ነበረች። በረከት ደስታ ከርቀት በቀጥታ ጠንከር ያለ ምት ወደ ጎል መትቶ መክብብ ደገፉ ያወጣትም የምትጠቀስ ጥሩ ሙከራ ነበረች።

ከመጀመሪያው ግማሽ ፈጣን እንቅስቃሴያቸው ከሚፈጥረው ጫናቸው ቀዝቀዝ ያሉት ፖሊሶች ወደ ተቃራኒ ቡድን ግብ ክልል ግን መድረስ አልተሳናቸውም። 71ኛው ደቂቃ በመልሶ ማጥቃት ከደስታ ጊቻሞ ያገኛትን ኳስ ብሩክ ኤልያስ እየገፋ ቢሄድም ፔንዜ ከግብ ክልሉ ወጥቶ አድኖበታል። 87ኛው ደቂቃ ብሩክ ኤልያስ ከመሀል ወደ ቀኝ ለበኃይሉ ወገኔ ስጥቶት ሳጥን ውስጥ መትቶ አገባው ሲባል ፔንዝ ለጥቂት ያወጣበት በመጨረሻዎቹ ደቂቃ የተገኘች ግብ ልትሆን የምትችል አጋጣሚ ነበረች። ብዙም አጋጣሚዎች ያልተፈጠሩበት ሁለተኛው አጋማሽ በመጀመሪያው አጋማሽ በተቆጠሩ ሁለት ግቦች በደቡብ ፖሊስ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ከውጤቱ በኋላ ደቡብ ፖሊስ ከወራጅ ቀጠናው ሳይወጣ በ23 ነጥብ 14ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ አዳማዎች ደግሞ በ 29 ነጥብ 10ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡