ሪፖርት | መከላከያ ባህር ዳርን በመርታት የማንሰራራት ጉዞውን አስቀጥሏል

ባህር ዳር ከተማን ያስተናገደው መከላከያ በፍቃዱ ዓለሙ ብቸኛ ጎል በማሸነፍ ከደቡብ ፖሊስ ድል በኋላ ለአንድ ሰዓት ገብቶበት ከነበረው ወራጅ ቀጠና በድጋሜ ፈቀቅ ብሏል።

መከላከያ ወላይታ ድቻን ከረታው ስብስቡ ከቅጣት የተመለሰው አበበ ጥላሁንን ጉዳት በገጠመው አዲሱ ተስፋዬ በመተካት ብቻ ለጨዋታው ሲቀርብ ባህርዳሮች ከደቡብ ፖሊስ ጋር ነጥብ ከተጋሩበት ጨዋታ ሁለት ቅያሪ አድርገዋል። በዚህም ሀሪሰን ሔሱ እና ማራኪ ወርቁ ምንተስኖት አሎ እና አቤል ውዱን በመተካት በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ተካተዋል።

የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በአመዛኙ የመከላከያ የበላይነት የታየበት ነበር። የተሻለ የኳስ ቁጥጥር የነበራቸው ባለሜዳዎቹ ከወትሮው በተለየ የተሳኩ ቅብብሎችን በመከወን ወደ ባህር ዳር የሜዳ ክልል መግባት ባይቸገሩም የግብ ዕድሎችን መፍጠር ላይ ግን እምብዛም አልነበሩም። ለዛም ይመስላል በተለይም መጀመሪያ አካባቢ የሜዳውን አጋማሽ ካቋረጡ በኋላ ረጃጅም ኳሶችን ወደ ፊት መላክን ምርጫቸው ሲያደርጉ ይስተዋል ነበር። ሆኖም የባህር ዳር የተከላካይ ክፍል ሳይቸገር አብዛኞቹን ኳሶች በመደረብ ያወጣ ስለነበር ከማዕዘን ምቶች ያለፈ ዕድል ሳያገኙ እስከ 30ኛው ደቂቃ ደርሰዋል። 30ኛው ደቂቃ ላይ ግን ሽመልስ ተገኝ ከቀኝ መስመር ያሻማውን ኳስ በተከላካዮች መካከል ይገኝ የነበረው የፊት አጥቂው ፍቃዱ ዓለሙ ራሱን ነፃ አድርጎ የጨረፋት ኳስ ከመረብ አርፋለች። ቡድኑ 39ኛው ደቂቃ ላይ ልዩነቱን ሊያሰፋ ሲቃረብ ዳዊት እስጢፋኖስ ከተከላካዮች ጀርባ በጣለው ኳስ ጥሩ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚ ቢያገኝም ፍሬው ሰለሞን ግብ ጠባቂውን ካለፈ በኋላ አገባ ተብሎ ሲጠበቅ በመውደቁ አጋጣሚው ውጤት ሳያፈራ ቀርቷል።

ባህር ዳሮች የመከላከያን ኳስ ማንሸርሸር ተከትሎ ብዙውን ደቂቃ በራሳቸው ሜዳ ላይ ለመቆየት ተገደዋል። ሆኖም ኳስ በነጠቁባቸው ቅፅበቶች በተደራጀ መልኩ መልሰው ለማጥቃት ሲሞክሩ አይታይም ነበር። 15ኛው ደቂቃ ላይ ብቻ ወሰኑ ዓሊ ከግርማ ዲሳሳ ተቀብሎ በቀኝ በኩል ሳጥን ውስጥ ገብቶ የሞከረው እና ወደ ላይ የተነሳው ኳስ በእንግዶቹ በኩል የተሻለ የሚባል ሙከራ ነበር። በአንፃሩ በመጨረሻዎቹ አስር ደቂቃዎች ኳስ ይዘው በጦሩ ሜዳ ላይ መታየት የቻሉት ባህር ዳሮች ፊት ላይ ወሰኑ ዓሊ በግሉ ከሚያደርገው ጥረት መነሻነት ወደ ሳጥኑ መጠጋት ሲችሉ ቢታይም ሌላ አቤል ማሞን የሚፈትን ሙከራ ማድረግ አልቻሉም። ከጀረባው ክፍተት ሲተው በተደጋጋሚ በቀላሉ ሲጠቃ የሚታየው የጦሩን የኋላ ክፍል ከኳስ ውጪ ጫና ውስጥ መክተትም ከጣና ሞገዶቹ የፊት መስመር የሦስትዮሽ ጥምረት በኩል ሳይታይ ነበር ጨዋታው ወደ ዕረፍት ያመራው።

ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀምር ጃኮ አራፋትን በበፍቃዱ ወርቁ ቀይረው ያስገቡት ባህር ዳሮች የጨዋታ ፍጥነታቸውን ጨምረው አቻ ለመሆን ተጭነው ተጫውተዋል። የጃኮን ጉልበት እና ፍጥነት በመጠቀም እንዲሁም በግርማ እና ወሰኑ አማካይነት ሜዳውን አስፍተው በማጥቃት ተጋጣሚያቸው እንደመጀመሪያው አጋማሽ ኳስ ተረጋግቶ እንዳይዝ አድርጎታል። 55ኛው ደቂቃ ላይ ግርማ ዲሳሳ ሳጥን ውስጥ በግራ በኩል በመግባት የሞከረው እና አቤል ማሞ ያወጣበት ሙከራም ቡድኑ በተሻለ ለግብ የቀረበበት ነበር። ነገር ግን ከ60ኛው ደቂቃ በኋላ ጨዋታው በጉሽሚያዎች መቆራረጥ ሲያበዛ የእንግዶቹም የበላይነት እየተቀዛቀዘ ሄዷል።

የተፈጠረባቸውን ጫና ወደ ኋላ በማፈግፈግ መቋቋምን የመረጡት መከላከያዎች በዚህ ረገድ ቢሳካላቸውም በመልሶ ማጥቃት ከሜዳቸው ለመውጣት በሚያደርጉት ጥረት ግን አስፈሪ አልነበሩም። ኳስ ይዘው ለመቆየት በሚሞክሩባቸውም ጊዜያት ዘግይተው በባህር ዳር ሜዳ ይገኙ የነበረ በመሆኑ ጥረታቸው አስፈሪነት ይጎድለው ነበር። 70ኛው ደቂቃ ላይ ብቻ በተሻለ ቅብብል በግራ በኩል ወደ ሳጥን ገብተው ታፈሰ ሰረካ የሚያሻማ ማስሎ በቀጥታ የመታውን ሀሪሰን ሄሱ ቀድሞ አድድኖበታል። በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ባህር ዳሮች አጋማሹን የጀመሩበትን ጫና የማሳደር አኳዃን መልሰው ቢያገኙም 80ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው እንዳለ ደባልቄ በግራ በኩል ሳጥን ውስጥ ተገኝቶ የሞከረው እና ኢላማውን ካልጠበቀው ኳስ ውጪ ሌላ የተሻለ ዕድል ሳይፈጥሩ 1-0 ለመሸነፍ ተገደዋል።

ውጤቱን ተከትሎ ባህር ዳር ቢያንስ እስከነገ ጨዋታዎች በነበረበት ስድስተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ነጥቡን 24 ማድረስ የቻለው መከላከያም በወራጅ ቀጠናው አፋፍ ላይ በነበረበት 13ኛ ደረጃ ላይ ረግቷል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡