ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | አዳማ ከተማ ከ መከላከያ

ቀጣዩ ትኩረታችን በመካከላቸው የአምስት ነጥቦች ልዩነት ብቻ ቢኖርም በተቃራኒ ወቅታዊ አቋም ላይ የሚገኙት አዳማ እና መከላካያን የሚያገናኘው ጨዋታ ነው።

ነገ 09፡00 ላይ የአዳማው አበበ ቢቂላ ስታድየም ከሰንጠረዡ ወገብ እየተንሸራተተ የሚገኘው ባለሜዳውን ላለመውረድ እየታገለ ከሚገኘው መከላከያ ጋር ያፋልማል። ኢትዮጵያ ቡናን በማሸነፍ ከተከታዮቻቸው በመጠኑ ከፍ ማለት ችለው የነበሩት አዳማዎች በሳምንቱ በደቡብ ፖሊስ በደረሰባቸው ሽንፈት ከወራጅ ቀጠናው ያላቸው ልዩነት የስድስት ነጥቦች ብቻ እንዲሆን አድርጓል። በሁለት ተከታታይ ድሎች ከአደጋው ቀጠና ወጥቶ አፋፍ ላይ የተቀመጠው መከላከያ በበኩሉ ህልውናውን ለማስቀጠል ተጨማሪ ነጥቦች የሚያስፈልጉት በመሆኑ ለጨዋታው የሚሰጠው ትርጉም ገና ችግር ውስጥ ካልገባው ተጋጣሚው አንፃር ሲታይ ከፍ ያለ ነው። ከዚህ ባለፈም ጦሩ በአዳማ የ5-1 ሽንፈት አስተናግዶ የውድድር ዘመኑን ቁልቁለት የጀመረበትን የመጀመሪያው ዙር ትዝታውን ይዞ ነው ወደ ጨዋታው የሚያመራው።

በግብ ከተንበሸበሸበት የሽረው ጨዋታ በኋላ በአምስት ጨዋታዎች ከሁለት ጊዜ በላይ ኳስ እና መረብን ማገናኘት የተሳነው አዳማ ከተማ የነገውን ጨዋታ ማጥቃት ላይ ተመስርቶ ለማድረግ እንደሚገባ ቢጠበቅም ይህ ደካማ ክብረ ውሰኑ ተፅዕኖ የሚያሳድርበት ይመስላል። አይነኬ የሚመስሉ ተጫዋቾችን ጨምሮ በተለያዩ ምክንያቶች ተደጋጋሚ ለውጦች የሚደረግበት የቡድኑ የወገብ በላይ ክፍል የቀደመ የመናበብ ደረጃውን ማግኘት አለመቻሉ ደግሞ ለዚህ እንደምክንያትነት ይነሳል። በርግጥ ነገ ሮበርት ኦዶንካራን ጨምሮ ከነዓን ማርክነህ እና ብዙአየሁ እንዳሻውን ከጉዳት የሚያገኝ ቢሆንም መሀል ሜዳ ላይ የተሻል ዕርጋታ እየታየበት ያለው ተጋጣሚው ላይ ብልጫ ለመውሰድ እንዳይከብደው ያሰጋል። ከዚያ ይልቅ በፈጣን ሽግግር የጦሩ የኋላ ክፍል ከመደራጀቱ በፊት አጋማሹን መሻገር የሚችሉባቸው ቅፅበቶች ከተገኙ ለአዳማዎች የተሻሉ ይሆናሉ። ዳዋ ሆቴሳ እና አንዳርጋቸው ይልሀቅን በጉዳት የማያሳትፉት ባለሜዳዎቹ የመጨረሻ ዕድሎችን ለማግኘት እንደተለመደው የከነዓንን ድንቅ ብቃት መጠበቃቸውም አይቀሬ ነው።

ከስምንት ጨዋታዎች በኋላ ግብ ሳያስተናግዱ ባህር ዳርን መርታት የቻሉት መከላከያዎች ደደቢትን በፎርፌ ያሸነፈው ወላይታ ድቻን ለመከተል ከጨዋታው ሙሉ ነጥብ ይሻሉ። በነገው ጨዋታ ኋላ መስመር ለውጥ ያደርጋሉ ተብሎ ባይጠበቅም አዲሱ ተስፋዬ ከቅጣት መመለሱ የአሰልጣኝ በለጠን አማራጭ እንደሚያሰፋ ሲጠበቅ ዳዊት ማሞም ቅጣቱን ጨርሷል። ቡድኑ ፊት ላይ ምንይሉ ወንድሙን አሁንም የማያገኝ ቢሆንም በባህር ዳሩ ጨዋታ በብቸኛ አጥቂነት የተጠቀመው ፍቃዱ ዓለሙ ግብ ማስቆጠሩ መልካም የሚባል ነው። ከዚህ ባለፈ አማካይ ክፍላቸው በቀላሉ ኳሶችን ይቀማበት የነበረው ሂደት መሻሻልን ማሳየቱ የአዳማ ወደ ፊት ገፍቶ ከመጫወት ጋር ተዳምሮ ለመከላከያዎች ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ ሲደርሱ የሚገጥማቸውን አጥር የማለፍ ችግራቸውን ሊያቃልላቸው ይችላል። ነገር ግን መሀል ሜዳ ላይ ብልጫን በመውሰድ ለማጥቃት የሚጥሩት እንግዶቹ ለመልሶ መጣቃት መጋለጥ እና በማጥቃት ሂደት ውስጥ የሜዳውን ስፋት በመጠቀም ተጋጣሚን የማስጨነቅ መቻል ላይ ሊቸገሩ የሚችሉበት ዕድል አለ።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ሁለቱ ቡደኖች በአጠቃላይ በሊጉ 26 ጊዜ ሲገናኙ አዳማ በ8 መከላከያ በ7 ጨዋታዎች ሲያሸንፉ በ11 ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል፡፡ በእነዚህ ግንኙነቶች መከላከያ 19 ግቦች ሲያስቆጥር አዳማ 22 አስቆጥሯል፡፡

– አዳማ ከተማ በሜዳው ካደረጋቸው 11 ጨዋታዎች ሁለት ሽንፈት እና ሦስት የአቻ ውጤትን ሲያስመዘግብ ስድስት ጨዋታዎችን በድል መወጣት ችሏል።

– ከሜዳው ውጪ አስር ጨዋታዎችን ያከናወነው መከላከያ ሦስቱን ብቻ በድል ሲወጣ በሦስቱ ነጥብ ተጋርቶ አራት ሽንፈቶች ገጥመውታል።

ዳኛ

– ጨዋታው ለኢንተርናሽናል ዳኛ በአምላክ ተሰማ የሊጉ አምስተኛ ጨዋታ ሲሆን በእስካሁኖቹ አራት ጨዋታዎች ሰባት የማስጠንቀቂያ ካርዶችን እና አንድ የፍፁም ቅጣት ምት ሲሰጥ አንድ ተጫዋች ደግሞ በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ አሰናብቷል። አርቢትሩ በውድድር ዓመቱ መጀመሪያ የመራው ጨዋታ አዳማ ከተማ ቅዱስ ጊዮርጊስን ያስተናገደበትም ነበር።

ግምታዊ አሰላለፍ

አዳማ ከተማ ( 4-2-3-1)

ሮበርት ኦዶንካራ

ሱለይማን ሰሚድ – ምኞት ደበበ – ቴዎድሮስ በቀለ – ሱለይማን መሀመድ

አዲስ ህንፃ – ኢስኤል ሳንጋሪ

ኤፍሬም ዘካርያስ – ከነዓን ማርክነህ – በረከት ደስታ

ቡልቻ ሹራ

መከላከያ (4-2-3-1)

አቤል ማሞ

ሽመልስ ተገኝ – ምንተስኖት ከበደ – አዲሱ ተስፋዬ – ታፈሰ ሰረካ

አማኑኤል ተሾመ – ቴዎድሮስ ታፈሰ

ሳሙኤል ታዬ – ዳዊት እስጢፋኖስ – ፍሬው ሰለሞን

ፍቃዱ ዓለሙ