ሪፖርት | ሲዳማ ቡና መቐለን በመርታት ልዩነቱን አጥብቧል

በ24ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሀዋሳ ላይ ሲዳማ ቡና መሪው መቐለ 70 እንደርታን አስተናግዶ 2-1 በማሸነፍ ወደ ዋንጫ ፉክክሩ ይበልጥ የተጠጋበትን ድል አሳክቷል።

ሀዋሳ ከተማን ባሳለፍነው ሳምንት ድል ያደረገው ሲዳማ ቡና ከተጠቀመበት የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ በሁለት ተጫዋቾች ላይ ለውጥን አድርጓል፡፡ በዚህም ፍቅሩ ወዴሳ እና ሚሊዮን ሰለሞንን በመሳይ አያኖ እና ዮናታን ፍሰሀ ተክተው ሲገቡ ሽረን የረቱት መቐለዎችም እንደ ሲዳማ ሁሉ ያሬድ ሀሰንን በአንተነህ ገብረክርስቶስ ኦሴይ ማውሊን ደግሞ በዮናስ ገረመው በመተካት ሁለት ለውጦችን አድርገው ወደ ሜዳ ገብተዋል፡፡

የዋንጫ ፍንጭ የሚሰጥ በመሆኑ ተጠባቂ የነበረው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ባለሜዳዎቹ ሲዳማ ቡናዎች ኳስን በመቆጣጠር ከዳዊት ተፈራ አልፎ አልፎ በሚነሱ ኳሶች ጥሩ ጥምረት ሲያሳዩ የነበሩት አዲስ ግደይ ፣ ሀብታሙ ገዛኸኝ እና ይገዙ ቦጋለ ላይ ትኩረት አድርገው በመጫወት የመቐለ ተከላካዮችን ሲፈትኑ ተስተውለዋል። በአንፃሩ እንግዳዎቹ ምዓም አናብስቶች በግብ ክልላቸው ጥቅጥቅ ብለው በመከላከል በሚነጥቁባቸው አጋጣሚዎች ደግሞ አድራሻቸው የማይታወቁ ረጃጅም ኳሶችን ወደ ፊት ይጥሉ ነበር። በመጀመሪያው አጋማሽ የበላይነትን የወሰዱት ባለሜዳዎቹ በርካታ ሙከራዎችን ማድረግ ሲችሉ እንግዳዎቹ 70 እንደርታዎች አንድም አጋጣሚ ሳይፈጥሩ ቀርተዋል። 12ኛው ደቂቃ የቀኝ መስመር አጥቂው ሀብታሙ ገዛኸኝ ወደ መሀል ተሰቦ ያገኛትን ኳስ ለዮናታን ፍሰሀ አቀብሎት በቀኝ መስመር ሰብሮ በመግባት ያሻማትን ማራኪ ኳስ አዲስ ግደይ በመቀስ ምት ለመምታት አስቦ ተጨርፋ ግብ ጠባቂው ፊሊፕ ኦቮኖ የተቆጣጠረበት አጋጣሚ ሲዳማ ቡናን መሪ ማድረግ የምትችል ነበረች። ከአምስት ደቂቃ በኋላ ደዊት ተፈራ ከማዕዘን ምት ያሻገራትን ኳስ ግርማ በቀለ በጭንቅላቱ ገጭቶ ለሳንደይ ምትኩ አቀብሎት ለጥቂት በቀኝ ቋሚው የወጣችበት ኳስም የምታስቆጭ ነበረች።

በሀይደር ሸሪፋ ሲመራ የነበረው መቐለ የመሀል ክፍሉ ብልጫ እንዲወሰድበት ያደረገው እና በጨዋታው ድንቅ እንቅስቃሴ አድርጎ አንድ ጎል የሆነ ኳስ አመቻችቶ ማቀበል ከቻለው ዳዊት ተፈራ በተነሳ ኳስ ሀብታሙ ገዛኸኝ ከሳጥን ውጪ ለነበረው ዮሴፍ ዮሀንስ አቀብሎት አክርሮ ቢሞክረውም ግብ ጠባቂው ፊሊፕ ኦቮኖ ተቆጣጥሮበታል። የቀኝ እና የግራ መስመር ተከላካዮቻቸው ወደ ፊት ተጭነው እንዲጫወቱ ያደረጉት ሲዳማ ቡናዎች 34ኛው ደቂቃ ላይ ዮናታን ፍስሀ ያሻገረለትን ኳስ በመቆጣጠር ሀብታሙ ገዛኸኝ የአሌክስ ተሰማን ስህተት በሚገባ ተጠቅሞ ባስቆጠረው ግብ መሪ ሆነዋል። ከግቧ መቆጠር በኋላ ይበልጥ የተጫኑት ሲዳማ ቡናዎች 37ኛው ደቂቃ ላይ አዲስ ግደይ ከዳዊት ተፈራ ጋር በማራኪ ሁኔታ አንድ ሁለት ተቀባብሎ በመግባት ፊሊፕ ኦቮኖ ከመድረሱ በፊት በመምታት ሌላ ግብ አስቆጥሮ ልዩነቱን ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችሏል። የመጀመሪያ ግማሽ መጠናቀቂያ ላይ ሳጥን ውስጥ ይገዙ ቦጋለ በጭንቅላቱ ገጭቶ ያቀበለውን ኳስ መሬት ላይ ሳታርፍ አክርሮ ቢመታትም በአግዳሚው ለጥቂት ወጥታበታለች።

የተወሰደባቸውን ብልጫ ለማስመለስ  አስበው ከዕረፍት መልስ በተከታታይ  ሀይደር ሸሪፋን በሳሙኤል ሳሊሶ ፣ ያሬድ ከበደን በያሬድ ብርሀኑ እና አንተነህ ገብረክርስቶስን በሄኖክ ኢሳያስ ቀይረው ያስገቡት እንግዳዎቹ ተጭነው መጫወት ችለዋል። በተለይም የሳሙኤል ሳሊሶ እና ያሬድ ብርሀኑ ቅያሪ የሲዳማ ቡና  ተከላካዮችን ፈትነዋል። ባለሜዳዎቹ ደግሞ በመልሶ ማጥቃት መጫወትን ምርጫቸው አድርገዋል። በቀጣይ በታዩ ሙከራዎችም ፊሊፕ ኦቮኖ ከአሌክስ ተሰማ የተቀበለውን ኳሶ በቅርብ ርቀት የነበረው ሀብታሙ ገዛኸኝ ተጠግቶ ሲያስጨንቀው አታሎ ለማለፍ ሲል ያገኛትን ኳስ ምንም ሳያረጋት በድጋሚ ፊሊፕ ኦቮኖ ተቆጣጥሮበታል። በ49ኛው ደቂቃ ደግሞ በቀኝ የሳጥኑ ክፍል የነበረው አማኑኤል ገብረሚካኤል ከዮናስ ገረመው የተቀበለውን ኳስ ይዞ ቢገባም ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ፈቱዲን ጀማል አስጥሎታል።

ወደ ግባቸው ተስበው ሲጫወቱ የነበሩት ሲዳማ ቡናዎች የመቐለ ተከላካዮችን ከመፈተን አልቦዘኑም። በ62ኛው ደቂቃ ዳዊት ተፈራ በቅብብል ስህተት ያገኘው ኳስ ለሀብታሙ ገዛኸኝ አመቻችቶ ቢያቀብለውም ፊሊፕ ኦቮኖ በግሩም ሁኔታ ያዳናት ግብ መሆን የሚችል አጋጣሚ ነበር። ደቂቃዎች በገፉ ቁጥር መጫናቸውን የቀጠሉት መቐለ 70 እንደርታዎች በፈጠሩት ዕድል የቀኝ መስመር ተከላካዩ ስዩም ተስፋዬ በረጅሙ ያሻገረውን ያሬድ ብርሀኑ በጭንቅላቱ ገጭቶ ግብ ጠባቂው መሳይ አያኖ አድኖበታል። ከአንድ ደቂቃ በኋላ ሳሙኤል ሳሊሶ ከማዕዘን ምት ያሻገራትን ኳስ አንዶህ ኩዌክ በጭንቅላቱ ገጭቶ ለአማኑኤል ገብረሚካኤል አመቻችቶ ሲያቀብለው አጥቂው የተከላካዮች እና የግብ ጠባቂው መሳይ አያኖን መዘናጋት በመጠቀም በጭንቅላቱ ገጭቶ ግብ በማድረግ መቐለ 70 እንደርታን ወደ ጨዋታው መመለስ ችሏል።

የመሀል ሜዳ ብልጫ የተወሰደባቸው ሲዳማ ቡናዎች ደዊት ተፈራን በማስወጣት አበባየሁ ዮሃንስን ቢያስገቡም ጫናውን ማርገብ አልቻሉም። 90ኛው ደቂቃ ዮናስ ገረመው በረጅሙ ያሻገረውን ኳስ መሳይ አያኖ በአግባቡ ሳይቆጣጠረው ቀርቶ በቅርብ ርቀት የነበረው አማኑኤል አግኝቶ ቢሞክርም በአግዳሚው ተመልሳ የወጣችው ኳስ የሊጉ መሪዎች አቻ መሆን የሚችሉበት አጋጣሚ ነበር። ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳያስተናግድ በሲዳማ ቡና 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። በዚህ መሰረትም ተከታዩ ፋሲል ከተማ ማሸነፉን ተከትሎ መሪው መቐለ 70 እንደርታ የነበረው የነጥብ ልዩነት ወደ ሁለት እንዲጠብ ሲሆን ሲዳማም በአምስት ነጥቦች መከተሉን ቀጥሏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡