የአሰልጣኞች አስተያየት | አዳማ ከተማ 0-0 መከላከያ

በ24ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አዳማ  ከተማን ከመከላከያ ያገናኘው ጨዋታ ያለ ጎል ከተጠናቀቀ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች እንደሚከተለው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

”በዚህ ዓመት ስብስብ ላይ ስህተት ተሰርቷል ” አስቻለው ኃይለሚካኤል (አዳማ ከተማ)

ስለ ጨዋታው

ጨዋታውን እንዳያችሁት ብልጫ ነበረን። የአጥቂ ችግር ነው የነበረብን። ተቃራኒ ቡድን አቻውን ይፈልጉታል፤ ይዘው የመጡትንም እቅድ አሳክተዋል። ምናልባት የአጥቂ ችግር ነው ብዬ አስባለሁ። እንደምታዩት የመሐል ተጫዋቾችንን በአጥቂ ስፍራ እየተጠቀምን ነው። በዚህ ዓመት ስብስብ ላይ ስህተት ተሰርቷል። ውስን አጥቂ ነው ያሉት። እኔም በዝግጅት ሰዓት አልነበርኩም።

ስለ ተጫዋቾቹ ብቃት

ይሄ የቀን ጉዳይ ነው። እከሌ እከሌ አትልም፤ እንደ ቡድን ጥሩ ነበርን። በመጀመሪያው አስር አስራ አምስት ደቂቃ ግብ ብናስቆጥር ኑሮ ውጤቱ ይለወጥ ነበር።  በልጠናቸው ነበር። ብልጫ ወስደን ተቆጣጥረናቸው ነበር ።

ወደ ወራጅ ቀጠና መጠጋት

ከታችኞቹ ጋር ልዩነት አለን። ግን ገና ቀሪ ጨዋታዎች አሉ። ገና ቢሆንም ጨዋታዎች እያነሱ ነው የሚሄዱት ። በድካማችን ላይ ጠንክረን እንሰራለን። የጨዋታ ትንሽ የለውም ከአሁን በኋላ ለሁሉም ጨዋታው እኩል ትኩረት እና ዝግጅት አድርገን ከዛ ቀጠና ለመውጣት ጥረት እናደርጋለን።

”ችግር ውስጥ ነው ያለነው፤ የሚያስፈልገን ሶስት ነጥብ ነው” በለጠ ገብረኪዳን (መከላከያ)

ስለ ጨዋታው

ጨዋታው እንዳያችሁት ጥሩ ፉክክር ይታይበታል ብዬ ነበር። ምክንያቱም አዳማም መከላከያም ኳስ የሚችሉ ቡድኖች ስለሆኑ ጨዋታው ጥሩ እና ተመጣጣኝ ነበር። ከእረፍት በፊት ትንሽ አለመረጋጋት ነበረብን። ከእረፍት በኋላ ግን ከእነሱ ተሽለን ጥሩ ለመስራት ሞክረናል። ለከፈሉት መስዋዕትነት በተጫዋቾቼ ደስተኛ ነኝ። በውጤቱም ደስተኛ ነኝ ።

ውጤቱን ፈልጋችሁት ነበር?

እንዳያችሁት አቻ ምንም አይጠቅመንም። የመጣነው ለማሸነፍ ነበር። ከመጀመሪያው ጀምሮ ብዙ ነጥቦችን የጣልነው። በእንደዚህ አይነት ችግር ከመሸነፍ አቻ ይሻለናል። ሆኖም እኛ ችግር ውስጥ ነው ያለነው የሚያስፈልገን ሶስት ነጥብ ነው ።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡