ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | መከላከያ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

የጦሩ እና የፈረሰኞቹን የነገ ጨዋታ የተመለከቱ ጉዳዮችን እንደሚከትለው አንስተናቸዋል።

ባሳለፍነው ሳምንት በተመሳሳይ ያለግብ በአቻ ውጤት ጨዋታዎቻቸውን ያጠናቀቁት መከላከያ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ነገ 10፡00 ላይ በመዲናዋ ይገናኛሉ። የጨዋታው ነጥቦች በእጅጉ የሚያስፈልጋቸው መከላከያዎች ሦስት ጨዋታዎችን ያለሽንፈት በመጓዝ ሰባት ነጥቦችን መሰብሰባቸው በታችኛው ፉክክር ውስጥ ነፍስ እንዲዘሩ ረድቷቸዋል። ያም ቢሆን ከተከታዮቻቸው እምብዛም ባለመራቃቸው እስትንፋሳቸውን ለማቆየት ማሸነፍ ብቸኛ አማራጫቸው ነው። ከዋና አሰልጣኙ ስትዋርት ሀል ጋር በሳምንቱ አጋማሽ የተለያየው ቅዱስ ጊዮርጊስ በአንፃሩ ከበላዮቹ ጋር ያለውን ልዩነት ማጠብብ የሚጠበቅበት ቢሆንም የተፎካካሪዎቹ ቁጥር ሦስት መሆን ግን የዋንጫ ዕድሉን አጥብቦታል። 

በኳስ ቁጥጥር ላይ የተመሰረተውን የተለመደ አቀራረባቸውን ይዘው እንደሚቀጥሉ የሚጠበቁት መከላከያዎች መጠነኛ ልምምድ ከጀመረው አጥቂያቸው ምንይሉ ወንድሙ ጉዳት ውጪ ሙሉ ስብስባቸውን የመጠቀም ዕድሉ አላቸው። የዳዊት እስጢፋኖስን እንቅስቃሴ ማዕከል በማድረግ ፍሬው ሰለሞን ወደሚነሳበት የግራ መስመር አድልቶ የሚያጠቃው ቡድኑ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ላይ ቢደክምም በቴዎድሮስ ታፈሰ እና አማኑኤል ተሾመ የተከላካይ አማካይ ጥምረት ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ግብ አለማስተናገዱ የተሻሻለው ጎኑ ነው። ነገም መሀል ላይ የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ሊያገኝ ቢችልም ወደ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል መግቢያ ላይ የሚኖረው  የቅብብል ስኬት የጎል አጋጣሚዎችን ከመፍጠር ባለፈ ከተጋጣሚው ሊሰነዘርበት የሚችለው መልሶ ማጥቃት መነሻነትን የመወሰኑ ጉዳይ የጎላ ነው። 

ከአሰልጣኝ ስታዋርት ሀል ስንብት ጥቂት ቀናት በኋላ ጨዋታውን የሚያደርገው ቅዱስ ጊዮርጊስ በመጀመሪያ የአሰላለፍ ምርጫው ላይ ለውጦችን ሊያደርግ እንደሚችል ይጠበቃል። በተለይም የመስመር አጥቂ እና ተከላካዮች  የለውጡ አካል የመሆን ዕድል ይኖራቸዋል። በደቡብ ፖሊሱ ጨዋታ ተቀይሮ የገባው በኃይሉ አሰፋ ተሻጋሪ ኳሶች አደገኛነት ተጨዋቹ የተሻለ ደቂቃ እንዲያገኝ ሊያግዙትም ይችላሉ። ከዚህ ባለፈ በቅርብ ጨዋታዎች ታደለ መንገሻን እያሳተፈ የሚገኘው የቡድኑ የሦስትዮሽ የአማካይ ጥምረትም ቅያሪዎችን ያስተናግድ ይሆናል።  በአጨዋወት ረገድ ግን በሁለቱ መስመሮች በፍጥነት ሰብሮ ለመግባት የሚሞክር እና ተሻጋሪ ኳሶችን መጠቀምን የሚያዘወትር ቡድን በጨዋታው ይጠበቃል። ፈረሰኞቹ ከመሀሪ መና ፣ ሳላዲን ሰዒድ እና ጌታነህ ከበደ ጉዳት ውጪ የሚያጡት ተጫዋች የሌለ ሲሆን ምንተስኖት አዳነም ሙሉ ለሙሉ ወደ ልምምድ መመለሱ ተሰምቷል።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– በኢትዮጵያ እግርኳስ ታሪክ በርካታ ዋንጫ በማንሳት ቀዳሚ የሆኑት ሁለቱ ክለቦች በሊጉ 27 ጊዜ ተገናኝተው መከላከያ ሁለት ጊዜ ብቻ ሲያሸንፍ 13 ጊዜ አቻ ተለያይተው 12 ጊዜ ቅዱስ ጊዮርጊስ አሸንፏል። መከላከያ 14 ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ 20 ግቦችን አስቆጥረዋል።

– አዲስ አበባ ላይ 12 ጨዋታዎችን ያከናወነው መከላከያ ሁለት ጊዜ ብቻ ድል ሲቀናው ሦስቴ ነጥብ ተጋርቶ በሰባት ጨዋታዎች ተሸንፏል።

– ቅዱስ ጊዮርጊስ 13 ጨዋታዎችን በሜዳው አድርጎ ሰባቱን ሲያሸንፍ አምስት የአቻ እና አንድ የሽንፈት ውጤቶች አስመዝግቧል።

ዳኛ

– የመጀመሪያውን ዙር የቡድኖቹን ጨዋታ የመራው ኢንተርናሽናል ዳኛ ዳዊት አሳምነው ነገም በድጋሜ እንዲዳኛቸው ተመድቧል። አርቢትሩ እስካሁን በመሀል ዳኝነት በተሰየመባቸው 11 ጨዋታዎች አንድ የፍፁም ቅጣት ምት እና አንድ የቀጥታ ቀይ ካርድ ውሳኔዎችን ሲያሳልፍ 35 የማስጠንቀቂያ ካርዶችንም መዟል።

ግምታዊ አሰላለፍ

መከላከያ (4-2-3-1)

አቤል ማሞ

ሽመልስ ተገኝ  – ምንተስኖት ከበደ – አዲሱ ተስፋዬ – ታፈሰ ሰረካ

አማኑኤል ተሾመ – ቴዎድሮስ ታፈሰ 

ሳሙኤል ታዬ – ዳዊት እስጢፋኖስ – ፍሬው ሰለሞን

 ፍቃዱ ዓለሙ

ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-3-3)

ፓትሪክ ማታሲ

ሄኖክ አዱኛ – አስቻለው ታመነ – ኢሱፍ ቡርሀና – ፍሪምፖንግ ሜንሱ

ሀምፍሬይ ሚዮኖ – ሙሉዓለም መስፍን – ታደለ መንገሻ

አቤል ያለው – ሪቻርድ አርተር – በኃይሉ አሰፋ