ሪፖርት | የሀዋሳ ከተማ እና ኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ አሠላ ላይ ተጀምሮ ቢሾፍቱ ላይ ያለ ጎል ተጠናቋል

በ26ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሀዋሳ ከተማ እና ኢትዮጵያ ቡናን ያገናኘው ጨዋታ የመጀመርያው አጋማሽ ትላንት አሠላ ላይ፤ ሁለተኛው አጋማሽ ደግሞ ዛሬ ቢሾፍቱ ላይ ተከናውኖ ያለ ጎል በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

ሀዋሳ ከተማ በ19ኛ ሳምንት በሜዳው ባህርዳርን አስተናግዶ በተፈጠረው የስፖርታዊ ጨዋነት ችግር ምክንያት በሜዳው 3 ጨዋታዎችን እንዳያደርግ ታግዶ ይግባኝ በመጠየቁ ወደ አንደ ጨዋታ ተቀንሶ የ26ኛ ሳምንት መርሀ ግብርን ከሜዳቸው ወጥተው በአሠላ ስታድየም ላይ ኢትዮጵያ ቡናን ያስተናገዱ ሲሆን ወደ መቐለ ተጉዘው በመስፍን ታፈሰ ብቸኛ ግብ መቐለ 70 እንደርታን 1 – 0 አሸንፎ ከተመለሰው ስብስብ መሳይ ጳውሎስ እና ፍቅረየሱስ ተክለብርሀን በማሳረፍ ዳንኤል ደርቤ እና ምንተስኖት አበራን በመተካት ነበር ወደ ሜዳ የገቡት። በኢትዮጵያ ቡና በኩል አዲስ አበባ ስታድየም በሲዳማ ቡና 2 – 0 ከተሸነፈው ስብስብ ኢስማኤል ዋቴንጋ፣ ቶማስ ስምረቱ፣ ቃልኪዳን ዘላለም እና ኃይሌ ገ/ተንሳይን በማሳረፍ ወንድወሰን አሸናፊ፣ አህመድ ረሽድ፣ ክሪዚስቶም ንታምቢን እና አቡበከር ናስር በመተካት ወደ ሜዳ ገብተዋል።

ሙሉ 45 ደቂቃ ንፋስ የቀላቀለ ከባድ ዝናብ እየዘነበ በተደረገው ጨዋታ ለመጫወት አዳጋች የነበረ ሲሆን በተለይ የንፋሱ አቅጣጫ ወደ ሀዋሳ አቅጣጫ ከመሆኑ የተነሳ ኳስ ለማራቅ ሲቸገሩ ተስተውሏል። በሀዋሳ ከተማ በኩል ተደጋጋሚ ኳሶችን ከመሀል ወደ ግራ መስመር እስራኤል እሸቱ ጋር በማሻገር ለማጥቃት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ሜዳው ኳስን ለመግፋት አዳጋች በመሆኑ የኢትዮጵያ ቡና ተከላካዮች በቀላሉ መጨናገፍ ችለዋል። በሙከራ ደረጃ 4ኛ ደቂቃ ላይ ምንተስኖት አበራ ከማዕዘን የተሻማ ኳስ በተከላካዮች ተገጭቶ ሲመለስ ያገኝውን ኳስ ወደ ግብ በቀጥታ እክርሮ የመታው ኳስ የግብን አግዳሚ ተጠግቶ የወጣው ኳስ የሚጠቀስ ነው።

በኢትዮጵያ ቡና ዎች መስመር በተደጋጋሚ ኳስን በማሻጋር በሁሴን ሻባኒ እና አቡበከር ናስር በተመሰረተ የማጥቃት እንቅስቃሴ በተደጋጋሚ ጎል የመግባት እድል ቢያገኙም በሜዳው አለመመቸት ምክንያት ኳስን ወደ ግብ ለመምታት እጅግ አስቸጋሪ ሆኖባቸው ነበር። ቀኝ መስመር ሁሴን ሻባኒ በተደጋጋሚ ከዳንኤል ደምሱ የሚላኩለትን ዣዥም ኳሶች ወደ ሳጥን ይዞት እየገባ ወደግብ በቀጥታ እና ወደ አቡበከር ለማሻገር የሚያደርጋቸው ጥረቶች ኢላማቸውን ሳይመቱ ቀርተዋል። 16ኛው ደቂቃ ላይ አቡበከር ናስር ሳጥን ውስጥ ተጫዋች አልፎ ከግብ ጠባቂ ጋር በመገናኘት ወደግብ አክርሮ መትቶ የዳነበትም የሚጠቀስ ሙከራ ነበር።

ከአንድ በላይ የተሳካ ቅብብል ማድርግ በማይቻል ሁኔታ ሲደረግ የነበረው የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቆ ከእረፍት ሲመለሱ ዝናቡ ቢያቆምም ሜዳው ከመጠን በላይ ውሃ በመያዙ የጨዋታው ኮሚሽነር እና ዳኞች ከቡድን አምበሎች ጋር በመሆን ጨዋታው እንደማይቀጥል በመወሰን ጨዋታው ወደ ቀጣይ ቀን 4:00 ሰዓት ለማዘዋወር ተስማምተው ጨዋታው ተቋርጧል።

ጨዋታው ዛሬ ረፋድ በአዳማ ይካሄዳል ተብሎ ቢጠበቅም ወደ ቢሾፍቱ የተሸጋገረ ሲሆን መከላከያ ዩንቨርስቲ የኢንጅነሪንግ ኮሌጅ ቅጥር ግቢ ውስጥ የተደረገው የሁለተኛ አጋማሽ ጨዋታ የመከላከያ ተቋም ግቢ ውስጥ በመካሄዱ ለደጋፊዎች ክፍት ሳይደረግ የኮሌጁ ተማሪዎች በሜዳው ታድመው ጨዋታውን ተመልክተዋል።

በዚህ አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ረጃጅም ኳሶችን በመጠቀም ግብ ለማግኝት ሲሞክሩ ተስተውሏል። በሙከራ ደረጃ 50ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ መስመር የተሻገረውን ኳስ ነፃ ሆኖ ያገኘው ደስታ ዮሐንስ ቢገጨውም ኢላማውን ሳይጠበቅ የቀረው የሚጠቀስ አጋጣሚ ነው።

የሀዋሳ ከተማ ከአዳነ ግርማ ወደፊት የሚላኩ ረዣዥም ኳሶች በመስመር ለደስታ ዮሐንስ እና መስፍን ታፈሰ የሚያሻግርላቸውን ኳሶች ወደ እስራኤል እሸቱ ሳጥን ውስጥ በማስገባት ግብ ለማግኝት ጥረት ሲያደርጉ ነበር። 65ኛ ደቂቃ ላይ ከመሀል ወደ ቀኝ መስመር አዳነ ግርማ ያሻገረለትን ኳስ እስራኤል እሸቱ ወደ ሰጥን ይዞት ገብቶ መስፍን ታፈሰ ያሸማውን ኳስ የኢትዮጵያ ቡናው ወንድወሰን አሸናፊ ወጥቶ ያዳነበት ግብ መሆን የሚችል አጋጣሚ ነበር። ወንድወሰን አጋጣሚውን ካመከነ በኋላ ተጎድቶ ለተወሰነ ደቂቃ ጨዋታው ተቋርጦ ህክምና ከተደረገለት በኋላ ወደ ሜዳ ተመልሷል ።

ኢትዮጵያ ቡናዎች በተደጋጋሚ ያደረጓቸውን ጥሩ ጥሩ ሙከራዎች ሶሆሆ ሜንሳህ በጣም ጥሩ የሚባሉ የግብ አጋጣሚዎችን አምክኗል። 63ኛው ደቂቃ ላይ አህመድ ረሽድ ከቅጣት ምት መሬት ለ መሬት ለአማኑኤል ዮሐንስ ያሻገረለትን አማኑኤል ቀጥታ ወደግብ አክርሮ መትቶ ሶሆሆ ሲያድንበት በድጋሚ 74ኛ ደቂቃ ላይ ተካልኝ ደጀኔ ያሻማውን ኳስ ሁሴን ሻባኒ በጭንቅላት በመግጨት ድንቅ ሙከራ ቢያደርግም ግብ ጠባቂው አድኖታል።

ቡናዎች በጨዋታው መገባደጃ ደቂቃ ላይ ተጭነው የተጫወቱ ሲሆን ሻባኒ ያሻገረለትን ኳስ አስራት ቱንጆ ሳጥን ውስጥ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ ወደግብ አክርሮ የመታውን ኳስ ሶሆሆ ሜንሳህ ያዳነበት በሁለተኛው አጋማሽ በኢትዮጵያ ቡና የሚያስቆጭ አጋጣሚ ነበር ።

ውጤቱ በአቻ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ ሀዋሳ ከተማ በ35 ነጥብ 7ኛ ላይ ሲቀመጥ ኢትዮጵያ ቡና በአንፃሩ በ34 ነጥብ 9ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል ።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡