አጫጭር መረጃዎች

ትላንት እና ዛሬ የተሰሙ አጫጭር የኢትዮጵያ እግርኳስ መረጃዎች እንዲህ አቅርበናቸዋል

– የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሀገር ውስጥ እና የውጭ ተጫዋቾች የ2012 የዝውውር ቀንን ይፋ አድርጓል፡፡ በዚህም መሠረት ከሐምሌ 25 ጀምሮ እስከ ጥቅምት 12 ቀን 2012 የሚቀጥል ሲሆን በቀጣዩ አመት የግማሽ ዓመት የዝውውር መስኮቱ ደግሞ ከጥር 1 እስከ 30 ድረስ የሚፈፀም መሆኑን ፌዴሬሽኑ ገልጿል፡፡

– የኢትዮጵያ ከ13 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በትናንትናው ዕለት ወደ ቻይና አምርቷል። በኤርሚያስ ዱባ የሚመራው ቡድኑ ከነገ ጀምሮ እስከ ሰኔ 23 ድረስ የሚካሄደው የቻይና-አፍሪካ ወዳጅነት የታዳጊዎች ውድድር ላይ ለመሳተፍ ነው ወደ ስፍራው ያመራው።

– የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ባወጣው ማስታወቂያ መሠረት ለመጨረሻ ፈተና ሰባት ግለሰቦችን ፈትኖ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አዲስ ማናጀር ሾሟል፡፡ በዚህም መሠረት የቀድሞው የአዲስ አበባ ስፖርት ክለብ ስራ አስኪያጅ እና ሰናይ መስማት የተሳናቸው የእግር ኳስ ክለብ መስራች እንዳለየሱስ አባተን ሾሟል፡፡

– የኢትዮጵያ ሴቶች ዋንጫ (ጥሎ ማለፍ) የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎች ዛሬ እና ነገ ይደረጋሉ። መከላከያ ከ ሀዋሳ ከተማ 8:00 ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም ሲጫወቱ ኢትዮጵያ ንግድ ከ ጌዴኦ ዲላ ነገ 4:00 ላይ በባንክ ሜዳ ይጫወታሉ።

-የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሊጠናቀቅ ጥቂት የቀረው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን በትኩረት ሊከታተለው መሆኑን ገልጿል፡፡ ከዚህ ቀደም ፌድሬሽኑ በገለፀው መሠረት ወሳኝ ጨዋታዎችን ለመቅረፅ እንዳሰበ የገለፀ ቢሆንም ወጥነት ባለው መልኩ ግን ተግባራዊ ሳያደርግ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ ነገር ግን ከዛሬ የ28ኛ ሳምንት ጀምሮ ላለመውረድ እና ለዋንጫ ፉክክር መቐለ፣ አዳማ፣ ይርጋለም፣ ሽረ እና ሀዋሳ ላይ የሚደረጉ አምስት ትኩረት ሳቢ ጨዋታዎችን በ15 ካሜራዎች ለማስቀረፅ ዝግጅቴን አጠናቅቂያለሁ ብሏል፡፡

-አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ ለብሔራዊ ቡድኑ የወዳጅነት ጨዋታን ቢያገኙም የሊጉ መቆራረጥ እክል በመሆኑ ሀሳባቸውን መፈፀም እንዳልቻሉ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡ አሰልጣኙ ከአይቮሪኮስት ብሔራዊ ቡድን ጋር በዚህ ወር መጨረሻ ላይ ለማድረግ እቅድ የያዙ ቢሆንም ሊጉ በወቅቱ ባለመጠናቀቁ ምክንያት ለማከናወን አልቻልንም ብለዋል “በዚህ ሰአት ተጫዋች ልምረጥ ብል ክለቦች ወሳኝ ጨዋታ ላይ በመሆናቸው ደስተኛ አለመሆናቸውን አስቀድሜ ባገኘሁት መረጃ ሰምቻለሁ። ሲቀጥል ደግሞ ሊጉ ተቋርጦ ረዘም ያለ ጊዜ መቆየቱም በታሰበው ልክ እንዳንሄድ አድርጎናል ብለዋል፡፡ ለአፍሪካ ዋንጫ ቴክኒክ ኮሚቴ ተመርጠው ግብፅ የሚገኙት አሰልጣኙ በቀጣዩ መስከረም ወር ላይ ከተለያዩ የአረብ እና የአፍሪካ ሀገራት ጋር ባለኝ መልካም ግንኙነት በርካታ ጨዋታ ለማድረግ አስቤያለሁ ብለዋል፡፡

-መከላከያ እግር ኳስ ክለብ በቅርቡ በነቀምት ከተማ ሲጫወት የነበረው እና በተተኮሰ ጥይት ህይወቱ ላለፈው የወንድሰን ዮሐንስ ቤተሰቦች የገንዘብ ድጋፍን አድርገዋል፡፡ ተጫዋቹ በህይወት በነበረበት ወቅት በርከት ያሉ የቤተሰቡን አባላት በብቸኝነት የሚረዳ በመሆኑ እና ለነሱ ቀጣይነት ላለው የህይወት ጉዞ ሲባል በርካታ ክለቦች እና ተጫዋቾች ድጋፍ እያደረጉ ሲሆን በትላንትናው እለትም የመከላከያ እግር ኳስ ክለብ በስፍራው በመገኘት የ21 ሺህ ብር የገንዘብ ድጋፍን አድርገዋል፡፡ የሀዲያ ሆሳዕና ደጋፊዎችም በተመሳሳይ ክለቡ ከሺንሺቾ በተጫወተበት ዕለት 16,748 ከደጋፊዎች ማሰባሰባቸው ይታወሳል።

– የወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ተጫዋቾች ለህክምና የገንዘብ ድጋፍ እየተሰበሰበላቸው ለሚገኙት ሲሳይ ዴኔቦ እና ሞገስ ታደሰ 27 ሺህ ብር ለግሰዋል። ከዚህ ቀደም መከላከያ፣ ቡና፣ ለገጣፎ፣ ሰበታ፣ ጅማ አባ ጅፋር፣ ፋሲል ከነማ፣ ድሬዳዋ፣ መቐለ እና ሉሲዎቹ በተመሳሳይ ድጋፍ ማድረጋቸው ይታወሳል።

-ቅዱስ ጊዮርጊስ ዳግም አሰልጣኝ ሰርዮቪች ሚሊቱን “ሚቾ”ን ሊሾም እንደሚችል ተሰምቷል፡፡ ከ1997-2002 ድረስ በቅዱስ ጊዮርጊስ ስኬታማ ጊዜን ያሳለፉት ሰርቪያዊው አሰልጣኝ አሰልጣኝ በደቡብ አፍሪካው ክለብ ቀሪ የዘጠኝ ወራት ውል ያላቸው ቢሆንም እየተሰሙ ባሉ መረጃዎች ቅዱስ ጊዮርጊስ ከክለቡ ጋር በሚያደርገው የውል ማፍረስ ድርድር በኃላ ዳግም ወደ ፈረሰኞቹ ቤት ሊመጡ እንደሚችሉ ተሰምቷል፡፡

– ኢትዮጵያ መድን ከአሰልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድ ጋር ተለያይቷል። አሰልጣኙ ቢሾፍቱ አውቶሞቲቭን በመልቀቅ በዓመቱ መጀመርያ ክለቡን ተቀላቅለው ጥሩ ጉዞ በማድረግ እስከመጨረሻዎቹ ሳምንታት ድረስ ወደ ፕሪምየር ሊግ ለማደግ ከወልቂጤ ጋር ፉክክር ሲያደርጉ እንደነበር ይታወሳል።

– 40 ቀናት በፊት ህይወታቸው ያለፈው የኢትዮጵያ መድን ስራ አስኪያጅ አቶ አበባው ከልካይ መታሳቢያ ይሆን ዘንድ ልጆቻቸው እንዲሁም ወዳጅ ዘመዳቸው የጨዋታ ፕሮግራም በ47 ሜዳ ዛሬ አከናውነዋል። አቶ አበባው በኢትዮጵያ እግርኳስ የአስተዳደር ስራዎች ላይ በመስራት እንዲሁም የተለያዩ ጥናታዊ ፅሁፎችን ያበረከቱ የስፖርት ሰው ነበሩ።

– የአሸናፊዎች አሸናፊ ጨዋታ ለማከናወን ፌዴሬሽኑ ቀን ቆርጧል። የፊታችን እሁድ እና ማክሰኞ የሚጠናቀቀው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ መደበኛ የምድብ ውድድር አንድ ጨዋታ እየቀረው ሦስቱንም የምድቡ አሸናፊዎችን ለይቷል ። አወዳዳሪው አካል የአሸናፊዎች አሸናፊ በድሬዳዋ ማድረጉን መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን ከሰኔ 30 ጀምሮ በአንድ ሳምንት ውስጥ ሰበታ፣ ወልቂጤ እና ሆሳዕና እርስ በዕርስ ተጫውተው በነጥብ በልጦ የሚገኘው ቡድን አጠቃላይ ቻምፒዮን ይሆናል።

የከፍተኛ ሊግ የሳምንቱ ጨዋታዎች (የምድብ ሐ ማክሰኞ ይካሄዳል)

እሁድ ሰኔ 16 ቀን 2011
አውስኮድ 9:00 ቡራዩ ከተማ
አቃቂ ቃሊቲ 9:00 ለገጣፎ ለገዳዲ
ገላን ከተማ 9:00 ደሴ ከተማ
ፌዴራል ፖሊስ 9:00 አክሱም
ኢትዮ ኤሌክትሪክ 9:00 ወሎ ኮምበልቻ
ሰበታ ከተማ 9:00 ወልዲያ

እሁድ ሰኔ 16 ቀን 2011
ወልቂጤ ከተማ 9:00 ኢትዮ. መድን
ድሬዳዎ ፖሊስ 4:00 የካ ክ/ከተማ
ዲላ ከተማ 4:00 አዲስ አበባ
ኢኮስኮ 4:00 ሀላባ ከተማ
ናሽናል ሲሜንት 4:00 ወላይታ ሶዶ
ሀምበሪቾ 9:00 ነገሌ አርሲ

– የኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ የማጠቃለያ ውድድር በቅርቡ እንደሚጀመር ይጠበቃል። መደበኛው የምድብ ውድድርን እያገባደደ የሚገኘው አንደኛ ሊግ የምድቡ የመጀመርያ ሦስት ደረጃዎች የያዙ 18 ክለቦችን የሚያወዳድር ሲሆን ስድስት ክለቦችም ወደ ከፍተኛ ሊግ ያድጋሉ። ይህን ውድድር ባቱ ከተማ እንደምታስተናግድ ሲገለፅ የቆየ ቢሆንም አሁን እየወጣ ባለ መረጃ ደግሞ ጅግጅጋ ሊካሄድ እንደሚችል ተገልጿል።

– የ2019 የአፍሪካ ዋንጫ በትናንትናው ዕለት ሲጀመር አስተናጋጇ ግብፅ ዚምባብዌን 1-0 አሸንፋለች። መሐመድ ትሬዚጌ ብቸኛዋን እና የውድድሩን የመጀመርያ ጎል ያስቆጠረ ተጫዋች ነው።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡