የኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ የማጠቃለያ ውድድር ሁለተኛ ቀን ውሎ

የኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ የማጠቃለያ ውድድር በባቱ ከተማ መካሄዱን ቀጥሎ ዛሬ በሁለተኛ ቀን ውሎ አራት ጨዋታዎች ተከናውነዋል። ሱሉልታ፣ ደብረብርሀን እና ባቱም አሸናፊ ቡድኖች ሆነዋል።

03:00 በጀመረው የዕለቱ የመጀመርያ ጨዋታ ሱሉልታ ከተማ ከ ቡሌ ሆራን አገናኝተው ብዙም ሳቢ ሳይሆን ቆይቶ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ድራማዊ ትዕይንት አስመልክቶን በሱለልታ 3-2 አሸናፊነት ተጠናቋል።

መሐል ሜዳ ላይ ብቻ ተገድቦ ወደፊት በማይሄድ እንቅስቃሴ የታጠረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የጎል ዕድል ሳይፈጠር ቆይቶ 22ኛው ደቂቃ ለሱሉልታ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ፍሬዕዝራ መንግሥቱ ወደ ጎልነት ቀይሮ ሱሉልታዎችን ቀዳሚ አድርጓል። ከጎሉ መቆጠር በኋላ ሱሉልታዎች በተሻለ መንቀሳቀስ ቢችሉም 35ኛው ደቂቃ ቡሌ ሆራዎች ከቅጣት ምት ሙሉቀን ተስፋዬ ባስቆጠራት ግሩም ጎል የመጀመርያው አጋማሽ በአንድ አቻ ውጤት ወደ እረፍት አምርቷል።

በጎል ሙከራ ያልታጀበ በመሐል ሜዳ ኳስ በማንሸራሸር በቀጠለው የሁለቱ ቡድኖች እንቅስቃሴ ከእረፍት መልስም የተመለከትን ቢሆንም በአንፃራዊነት ቡሌ ሆራዎች ግልፅ የማግባት አጋጣሚ አይፍጠሩ እንጂ ከሱሉልታ በተሻለ መልካም እንቅስቃሴ አድርገዋል። በመጨረሻም የጨዋታው ድራማዊ ክሰትት ከ84ኛው ደቂቃ ጀምሮ አስመልክቶናል። 84ኛው ደቂቃ ከግራ መስመር የተሻገረውን ኳስ ቀነኒ አብዱላሂ በግንባሩ በመግጨት ባስቆጠረው ሁለተኛ ጎል ቡሌ ሆራ መምራት ችሎ ነበር ። ይሁን እንጂ የጨዋታው መደበኛ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በተጨማሪ ደቂቃ በተሰጠበት ቅፅበት የቡሌ ሆራ ተከላካይ ኳስ በእጅ በመንካቱ ለሱሉልታዎች ፍፁም ቅጣት ምት ሲሰጥ ፍሬዕዝራ መንግስቱም ለቡድኑ አቻ ያደረገበት ለእራሱ ሁለተኛ ጎል አስቆጥሯል።

በዚች ጎል የተነቃቁት ሱሉልታዎች የጨዋታው መጠናቀቂያ ሽርፍራፊ ሰከንድ ላይ የሱሉልታው አሰልጣኝ ሰለሞን አዳነ ውጤታማ ቅያሪ ተሳክቶ ተቀይሮ በገባው ስንታየሁ አሥራት አማካኝነት ሦስተኛ ጎል አስቆጥረዋል። ይህች ጎል ስትቆጠር በሜዳ ላይ ያልተገባ ባህሪ ያሳይ የነበረው ሁለቱን የሱሉልታ ጎሎች በፍፁም ቅጣት ምት ያስቆጠረው ፍሬዕዝራ መንግስቱ አስቀድሞ የቢጫ ካርድ የተመለከተ ቢሆንም በቀጥታ ቀይ ካር ከሜዳ እንዲወጣ ተደርጓል። ፍሬዕዝራ የተመለከተው ቀይ ካርድም የውድድሩ የመጀመርያ ቀይ ካርድ ሆኖ ተመዝግቧል። በዚህም ጨዋታው በአስገራሚ ሁኔታ በሱሉልታ 3 –2 አሸናፊነት ተጠናቋል።

05:00 ናኖ ሁርቡ ከ ባቱ ከተማ ያገናኘው ጨዋታ አከራካሪ በሆነ የዳኝነት ውሳኔ ባቱ ከነማ ባገኘው የፍፁም ቅጣት ምት ጎል 1-0 አሸንፎ ወጥቷል። በርከት ያለ ተመልካች በተከታተለው እና መልካም የጨዋታ እንቅስቃሴ በተመለከትንበት በዚህ ጨዋታ ውስን የሆኑ የጎል ዕድሎች ተመልክተናል። 20ኛው ደቂቃ በቡሌ ሆራ በኩል ከቀኝ መስመር የተሻገረለትን በጥሩ ሁኔታ ተረጋግቶ ጎል አስቆጠረ ሲባል ሳይጠቀምበት የቀር ኳስ የሚያስቆጭ ነው። ብዙም ሳይ ቆይ ባቱዎች በመልሶ ማጥቃት ያገኙትን አጋጣሚ አንበሉ ብርሃኑ ሆራ ከርቀት በግራ እግሩ የመታው ኳስ ለጥቂት ወደ ውጭ ወቶበታል።

በርከት ያሉ የጎል እድሎች አይፈጠሩበት እንጂ የሁለቱም ቡድኖች እንቅስቃሴ ለተመልካቹ አዝናንቶ ወደ ሁለተኛው አጋማሽ ተሻገረ ሲሆን በዕለቱም ብዙ ውዝግብ እና በተመልካቾች ዘንድ አከራካሪ የሆነ ፍፁም ቅጣት ምት ባቱ ከተማ አግኝቶ 2007 ድሬዳዋ ከነማ ወደ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሲያድግ ትልቁን አስተዋፆ ከተወጡት ተጫዋቾች መካከል አንዱ የነበረው እና አሁን የባቱ ከተማ አምበል ብርሃኑ ሆራ ወደ ጎልነት ቀይሮት ባቱዎች መምራት ችለዋል። ይህ የዕለቱ ዳኛ ውሳኔ ያላስደሰታቸው የናኖ ሁርቡ አሰልጣኞች እና ተጫዋቾች ከዕለቱ ዳኛ ጋር እሰጣገባ ገብተው ግርግር ተፈጥሯል። ጨዋታውም ምንም የተለየ ነገር ሳያስመለክተን ባቱ ከተማ 1–0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

07:00 በቀጠለው የዕለቱ ሦስተኛ ጨዋታ የጁ ፍሬ ወልዲያ ከ ሰሜን ሸዋ ደብረ ብርሃን ተገናኝተው ደ/ብርሀኖች በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች አከታትለው ባስቆጠሯቸው ሁለት ጎሎች 2-0 አሸንፈው ወጥተዋል። ደካማ እንቅስቃሴ በተመለከትንበት ጨዋታ ሰሜን ሸዋዎች ባላቸው ልምድ ታግዘው ጎሎች ማስቆጠር የጀመሩት ገና 2ኛው ደቂቃ ነበር። ከግራ መስመር የተሻገረትን ከሆሳዕና ፕሮጀክት ጀምሮ በ2007 ፕሪምየር ሊግ ሲገባ የነበረውና ዘንድሮ ከቡድኑ ጋር ተለያይቶ ደብረብርሃን እየተጫወተ የሚገኘው ዋቴሮ ኤልያስ ባስቆጠራት የግምባር ኳስ ቀዳሚ መሆን ችለዋል። የቀድሞ የአርባምንጭ ከተማ ተጫዋች እና በቅርቡ አሰልጣኝ የሆነው እየብ ማለ (አሙካቺ) የሚመራው ሰሜን ሸዋ በ7ኛው ደቂቃ ኃይሉ ነጋሽ በተመሳሳይ የግንባር ኳስ ሁለተኛ ጎል አስቆጥረዋል። በተከታታይ የተቆጠረባቸው ሁለት ጎሎች ምክንያት መረጋጋት ያልቻሉት የጁዎች አልፎ አልፎ ካልሆነ ወደ ጨዋታው የሚመልሳቸውን የጎል አጋጣሚ መፍጠር አልቻሉም።

በመጀመርያዎቹ 10 ደቂቃዎች የተጠናቀቀ የሚመስለው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ደብረ ብርሃኖች በመከላከል ላይ አተኩረው በመልሶ ማጥቃት የጎል እድል ለመፍጠር ሲጥሩ በአንፃሩ የጁ ፈሬ ወልድያዎች ኳሱን ተቆጣጥረው ወደ ፊት ለመሄድ ጥረት ቢያደርጉም ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ በሚቆረጥ ኳስ ምክንያት ጎል ሳያስቆጥሩ በሰሜን ሸዋ ደብረብርሃን 2-0 ተሸንፈው ሊወጡ ችለዋል።

09:00 በተካሄደ የዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ መተሐራ ስኳር ከ ሶሎዳ ዓድዋ በማጠቃልያ ውድድሩ ጎል ያልተቆጠረበት እና በአቻ ውጤት የተጠናቀቀ የመጀመርያው ጨዋታ ሆኖ 0-0 ተጠናቋል። ሰሎዳ ዓድዋ ጥሩ ቡድን መሆኑን ባስመለከተን ጨዋታ ምን አልባትም ጨዋታውን አሸንፈው ሊወጡበት የሚችሉበትን የጎል አጋጣሚዎች ማምከናቸው የሚያስቆጫቸው ይሆናል። በተለይ አብራር መርዙቅ ከግብ ጠባቂ ጋር ብቻውን ተገናኝቶ ጎል አስቆጠረ ሲባል ከውሳኔ ችግር የተነሳ የመተሐራው ግብ ጠባቂ ኤፍሬም ወርቁ የያዘበት የሚያስቆጭ አጋጣሚ ነበር። በአንፃሩ መተሐራዎች ሀብታሙ ከበደ ሳይጠቀምበት የቀረው ለጎል የቀረቡ ሙከራቸው ነበር። በመጀመርያው አጋማሽ በሁለቱም በኩል አንድ አንድ ግልፅ የጎል አጋጣሚ ተመልክተናል።

ከእረፍት መልስ ሰሎዳ ዓድዋዎች በተሻለ መንቀሳቀስ ችለው ተጭነው የተጫወቱ ሲሆን ኃፍቶም ገ/ሄር ከርቀት ኳስ መቶ የመተሐራው ግብ ጠባቂ ኤፍሬም እንደምንም አድኖታል። ብልጫ እንደመውሰዳቸው እና ተከላካዩ ሄኖክ ገብሬ ባጋጠመው ጉዳት ምክንያት ተቀይሮ እንዲወጣ የህክምና ባለሙያው ቢያሳውቅም በፍጥነት ሦስት ተጫዋቾችን አስቀድመው ቀይረው የጨረሱ በመሆኑ መተሐራዎች ለ7 ደቂቃ በጎዶሎ ለመጫወት ተገደው ምንም ማድረግ ባለመቻላቸው ህመሙን ታግሶ የጨዋታውን ቀሪ 10 ደቂቃ ለመጨረስ ችሏል።

86ኛው ደቂቃ ላይ በጥሩ ቅብብል ወደ ፊት ገብተው ከቀኝ መስመር የተሻገረንውን ኳስ ከኃፍቶም ሳጥን ውስጥ የተቀበለውን ወደ ጎልነት ቢቀይረውም የዕለቱ ዳኛ ጎሉ ከጨዋታ ውጭ ነው በማለት ሳያፀድቁት በመቅረታቸው ከፍተኛ ውዝግብ አስነስቶ ጨዋታው ለተወሰኑ ደቂቃዎች ሊቋረጥ ችሏል። ጎሉ የተሻረበትም መንገድ አሳማኝ አይደለም በማለት ሰሎዳ ዓድዋዎች ቅሬታቸውን አሰምተዋል። ጨዋታው የተለየ ነገር ሳያስመለክተን 0-0 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።

የነገ ጨዋታዎች መርሐ ግብሮች

03:00 ኮልፌ ቀራንዮ ከ አዲስ አበባ ፖሊስ

05:00
ላስታ ላሊበላ ከ ቢሸፍቱ ከተማ

07:00
ዳሞት ከተማ ከ ቂርቆስ ክ/ ከተማ

09:00
መቱ ከተማ ከ ከራያ አዘቦ

*ሁሉም ጨዋታዎች በሼር ሜዳ የሚደረጉ ይሆናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡