ኢትዮጵያ ቡና ራሱን ከኢትዮጵያ ዋንጫ አገለለ

ሐሙስ ከሀዋሳ ከተማ ጋር የኢትዮጵያ ዋንጫ (ጥሎ ማለፍ) ግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ የነበረው ኢትዮጵያ ቡና ራሱን ከውድድሩ ማግለሉ ታውቋል፡፡ ሀዋሳ ከተማም ወደ ፍፃሜው በፎርፌ የሚሸጋገር ይሆናል።

የሚሰጠው ትኩረት በእጅጉ እየቀነሰ የመጣው እና ክለቦች ራሳቸውን እያገለሉበት ያለው የኢትዮጵያ ዋንጫ ቦታው ባይገለፅም ሐምሌ 14 ፍፃሜውን ያገኛል፡፡ ሆኖም እስካሁን የክለቦችን ከውድድሩ መውጣት ተከትሎ በፎርፌ ለግማሽ ፍፃሜ የበቃው ኢትዮጵያ ቡና የፊታችን ሐሙስ ከሀዋሳ ጋር አዳማ ላይ ሊያደርግ የወጣለትን መርሐ ግብር እንደማያካሄድ ታውቋል።

ተጫዋቾቹን ሐምሌ 1 የበተነው ኢትዮጵያ ቡና ከሦስት ቀናት በፊት ተጫዋቾቹን በድጋሚ ጠርቶ ወደ ልምምድ የገባ ቢሆንም የበርካታ ተጫዋቾች ውል የተጠናቀቀ በመሆኑ እና ወደ ልምምድ የተመለሱት ጥቂት በመሆናቸው ለፌዴሬሽኑ ደብዳቤን በማስገባት ራሱን ያገለለ መሆኑን ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል፡፡

ውሳኔው ኢትዮጵያ ቡናን ራሱን ያገለለ ሰባተኛ ክለብ ሲያደርገው በፎርፌ ለፍፃሜ አላፊ የሚሆነው ሀዋሳ ከተማ ሐምሌ 14 ከመቀለ እና ፋሲል አሸናፊ ጋር ወደፊት በሚገለፅ ሜዳ እንዲጫወት ፌዴሬሽኑ ለክለቡ ትላንት በፋክስ እንዳሳወቀ ተገልጿል። 


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡