“የሜዳ ውጭ ጨዋታዎች ወሳኝ ስለሆኑ በጥንቃቄ ነው የምንጫወተው” ገብረመድህን ኃይሌ

የ2011 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አሸናፊ መቐለ 70 እንደርታ ነገ አመሻሽ ላይ ከሜዳቸው ውጭ የኢኳቶርያል ጊኒው ካኖ ስፖርትስ አካዳሚን ይገጥማሉ። በተከታታይ ዓመት የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ያነሱት እና ከዚህ ቀደም ከመከላከያ ጋር በአፍሪካ የክለብ ውድድሮች ላይ ልምድ ያላቸው አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ስለቡድናቸው እና ስለነገው ጨዋታው ሁኔታ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

ለጨዋታው ያደረጋችሁት ዝግጅት

የተለየ ዝግጅት አልነበረንም። የተለመደው ዝግጅታችን እንዳለ ሆኖ ይህ የአህጉር ውድድር ነው፤ ከዛ በተጨማሪም ከሜዳ ውጭ የሚደረግ ጨዋታ እንደመሆኑ ከዚ ጨዋታ ነጥብ ይዘን በምንመለስበት አጨዋወት ላይ ነው ስንዘጋጅ የቆየነው። የሊግ እና የጥሎ ማለፍ ውድድር ሥነ-ልቦናዎች ይለያያሉ፤ ይሄ የደርሶ መልስ ውድድር ስለሆነ ከሜዳ ውጭ ጨዋታ ላይ ጥቅምህን አስከብረህ የምትጫወታቸው ጨዋታዎች ናቸው። ለዚ እንዲያግዘን ደግሞ ጥሩ ዝግጅት አድርገናል።

ጨዋታው ከሜዳ ውጭ እንደመሆኑ ምን የተለየ የሥነ-ልቦና ዝግጅት አድርጋችኋል?

በዛ በኩል ምንም የተለየ ነገር የለውም። ቡድኑ ብዙ ጊዜ ያስቆጠረ አይደለም። በአጭር ግዜ የሃገሩን ሊግ ያነሳ ቡድን ነው። ከሥነ-ልቦናው ይልቅ ግን ቡድናቸው የተሰራው በወጣቶች ላይ ስለሆነ በእንቅስቃሴ እና የጨዋታውን ፍጥነት በመጨመር ሊያስቸግሩን ስለሚችሉ ለዚ ያግዘናል ያልነውን በቂ ቅድመ ዝግጅት አድርገናል። ከዛ ውጭ ልምዳችንንም እንጠቀማለን። በሃገር ደረጃም በክለብ ደረጃም ብዙ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች ስለሉን እነሱን ተጠቅመን ጥሩ ውጤት ይዘን ለመመለስ ጥረት እናደርጋለን።

ስለ ተጋጣምያችሁ በቂ መረጃ አግኝታችኃል?

እንደሚፈለገው አላገኝንም። በብዙ መንገዶች መረጃዎች ለማግኘት በርካታ ጥረት አድርገናል። ግን በቂ መረጃ ማግኘት አልቻልንም። ቪድዮዎች በዩትዩብ ፈልገን ያገኘነው በጣም ውስን ነው፤ እሱም ግልፅ የሆነ መረጃ አይደለም። በሌላ መንገድም መረጃ ለማግኘት ጥረት ብናደርግም እንደምንፈልገው ግን አላገኘንም። በአጠቃላይ ባየናቸው መረጃዎች ግን ቡድኑ በስሜት እና በተነሳሽነት እንደሚጫወት ለማየት ችለናል፤ ስለ ቡድኑ አጨዋወት መንገድ ግን መረጃ ለማግኘት አዳጋች ነው።

በነገው ጨዋታ በውጤት ደረጃ ምንድነው እቅዳችሁ?

በውጤት ማስቀመጥ ከባድ ነው። በእንደዚ ዓይነት ውድድር ላይ የሜዳ ውጭ ጨዋታዎች ወሳኝ ስለሆኑ በጥንቃቄ ነው የምንጫወተው። በነገው ጨዋታ የቡድናችን ጥቅም ማስቀደም የሚችለው አጨዋወት ነው የምንመርጠው። በውጤት ደረጃ እንዲ ነው እንዲያ ነው ብለን የምናስቀምጠው ነገር የለም። በዚ ጨዋታ በቀጣይ በሜዳችን ለምናደርገው ጨዋታ ጥሩ የማለፍ ዕድል ይዘን ነው መቅረብ የምንፈልገው። ከቻልን ማሸነፍ፤ ጨዋታው ከከበደ ደግሞ አንድ ነጥብ ይዘን ለመመመስ ነው እቅዳችን።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡