”… ለዚህኛው ጨዋታ ይበልጥ ተዘጋጅተናል ” ያሬድ ባዬ

የ2019/20 የካፍ ኮንፌደሬሽን ዋንጫ ተሳተፊ የሆነው ፋሲል ከነማ ነገ በባህር ዳር ኢንተርናሽናል ስታዲየም የቅድመ ማጣርያ የመጀመሪያ ጨዋታውን 10፡00 ላይ ያደርጋል። ስለ ጨዋታው እና ስለ ዝግጅታቸው የቡድኑ አምበል ያሬድ ባዬ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል።

ለውድድሩ እና ለጨዋታው ያደረጋችሁት ዝግጅት ምን ይመስላል?

ጥሩ ተዘጋጅተናል። ተጋጣሚያችን እንዴት ይጫወታል የሚለውን በቪዲዮ በማየት ነው እየተዘጋጀን ነው የምንገኘው። ከዛ አንፃር የምንታወቅበትን አጫጭር ኳሶች ተጫውተን ጨዋታውን ለማሸነፍ ነው የምንገባው።

በዚህ ሰዓት ያለው የቡድናችሁ ስሜት ምን ይመስላል?

የቡድኑ ስሜት ያው እንደተለመደው ጥሩ ነው። የቡድኑ መንፈስ ጥሩ ስለሆነ ለሁሉም ጨዋታ አንድ አይነት ዝግጅት ነበር የምናደርገው። ለዚህኛው ጨዋታ ግን ይበልጥ ተዘጋጅተናል። ቡድኑም ኢንተርናሽናል ጨዋታ የመጀመሪያው ነው። አንድ የወዳጅነት ጨዋታ ነው ከአልሜሪክ ጋር ያደረግነው። ከዛ አንፃር ጥሩ እየተዘጋጀን ነው ብለን እናስባለን ።

የቡድኑ አምበል እንደመሆንህ በዚህ ጨዋታ ላይ በውጤት ደረጃ ምን ይዛችሁ ለመውጣት ተዘጋጅታችኋል?

ቡድኑን በመምራት በማረጋጋት ጥሩ ውጤት ይዘን እንድንወጣ ነው እቅዴ። እኔ አምበል ብሆንም እንደሌሎቹ ሁሉ ተጫዋች ነኝ እና የተጫዋቾችን ስሜት አንድ ላይ ይዤ ለመውጣት ዝግጅት አድርጌያለሁ።

ጨዋታው በሜዳችሁ ከመሆኑ አንፃር ምን ያህል የተሻለ እድል አለን ብለህ ታስባለህ?

ጨዋታው በሜዳችን ከመሆኑ ባሻገር ባህር ዳር ስታዲየም ላይ በመሆኑ ብዙ ደጋፊዎች ይገባሉ። ደጋፊዎቻችን 12ኛ ተጫዋች ስለሆኑ ያንን አድቫንቴጅ እንጠቀማለን። ደጋፊዎች የተለመደው ድጋፋቸውን እንዲሰጡን ነው የምፈልገው። ያው ሜዳ ላይ ምንም ነገር ሊፈጠር ይችላል። ያንን ተቋቁሞ ሙሉ በሙሉ 90 ደቂቃ እንዲደግፉን ነው የምንፈልገው። በርግጥ ከዚህ በፊትም አሳፍረውን አያውቁም።

ስለ ተጋጣሚያችሁ ምን የምትለን ይኖራል?

እነሱ ጉልበት ላይ ጠንከር ያሉ ናቸው። ረዣዥም ኳሶች ይጠቀማሉ። በዛ ላይ ሊጋቸው ላይ ሦስተኛ ነው የወጡት፤ እናም ጠንካራ ቡድን ነው። ያንን ተቋቁመን በጥሩ ሁኔታ ለመወጣት እቅዳችን ነው።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡