“በቀጣይ እኔን የሚረከቡ አሰልጣኞች አሁን የታየውን ጥሩ ነገር ያስቀጥላሉ ብዬ አስባለሁ” ውበቱ አባተ

በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ቅድመ ማጣርያ የመጀመርያ ጨዋታ አዛምን የገጠመው ፋሲል ከነማ 1-0 አሸንፏል። በፋሲል አሰልጣኝነት የመጨረሻ ጨዋታቸውን አድርገው ድል ያስመዘገቡት አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ስለ ጨዋታው እና ተያያዥ ጉዳዮች በስፍራው ለተገኙ ጋዜጠኞች አስተያየት ሰጥተዋል።

ስለ ጨዋታው

ጨዋታውን ማሸነፍ ችለናል። ከዛ በተረፈ ግን
አንድ ለሀገር እንደሚያስብ ሰው፤ እንደ አሰልጣኝም ያየሁትን በጣም ብዙ ጥሩ ነገሮች የበለጠ ብናስቀጥል ደስ ይለኛል። ከግቡ በላይ እስከ 70 ደቂቃ የነበረን እንቅስቃሴ፣ የሄድንበት መንገድ እና ጨዋታውን ለመቆጣጠር ያደረግነው ነገር አዋጭ እንደሆነ አይቼበታለሁ። አዛም ትልቅ እና በደንብ የተደራጀ ቡድን ነው። ከዚህ ቡድን ጋር ተጫውቶ በዛ ላይ ብልጫ ወስደህ ማሸነፍ ትልቅ ነገር ነው። 90 ደቂቃ አስጠብቆ ለመውጣት የሚጎድል ነገር እንዳለ አይቻለሁ። የመጨረሻ አስር አስራምስት ደቂቃ እነሱ ብልጫ ወስደው ተጫውተዋል። እኛ ከዛ ጫና ለመውጣት ተጨማሪ ሥራ እንደሚያስፈልገን አይቻለሁ። ሆኖም ግን ለኛ ትልቅ ጨዋታ ነበር። እነሱ ከውድድር ነው የመጡት፤ የሴካፋ ውድድር ነበራቸው። ከሴካፋ በኋላም ብዙ የወዳጅነት ጨዋታ አድርገዋል። እኛ የወዳጅነት ጨዋታ አላደረግነም። ሊነጋችን አቁሞ ነው ያለው። የጨዋታ አቅማችን ምን ድረስ እንደነበር አናውቅም። ለቀጣይ ምን መስራት እንደምንችል አይተናል። በኔ በኩል ጥሩ ጨዋታ ነው።

በቀጣይ ውጤት አስጠብቆ ወደ ቀጣይ ስለማለፍ

ያለው ነገር የልምድ ልዩነት ነው። እነሱ በጣም ብዙ ጨዋታ ማድረጋቸው ያስታውቃል። እኛ የወዳጅነት ጨዋታ ከትንሽ ቡድን ጋር እንኳን አለማግኘታችን ትልቅ ጉዳት ነው። በሊግ ውድድር ላይ እያለን እንደዚህ አይነት ጨዋታ ብንጫወት የተሻለ ነገር ማሳየት እንደምንችል አይተናል። ከሜዳ ውጭ ነው ቀጣይ ጨዋታ። አዛም ጥሩ ቡድን ነው ከቪዲዮ ከመረጃዎቹ በተጨማሪ በአካል አይተናቸዋል። ምን አይነት አቀራረብ ይዘው ሊመጡ እንደሚችሉ መገመት ይቻላል። እኔ የቤት ስራዬን ጨርሻለሁ። በቀጣይ እኔን የሚረከቡት ደግሞ ያንን ያስቀጥላሉ ብዬ አስባለሁ።

ክለቡ መልቀቂያህን ተቀብሎሀል?

ከክለቡ ጋር በይፋ ተለያይቻለሁ። ውሌ እስከዚህ ጨዋታ ብቻ ነበር። ለዚህ ደግሞ ብዙ መስዋትነት ከፍያለሁ፤ የትምህርት እድሌን አጥቻለሁ። ይህን ያደረግኩት ደጋፊውን እና ክለቡን ለማክበር ነው። እነሱም የአሰልጣኝ ቅጥር ሂደት ላይ እንደሆኑ አውቃለሁ። በርግጠኝነት ቀጣዩ ሰው ስራውን ይረከበዋል ብዬ ነው የማስበው። በኔ በኩል ግን ያለኝን ነገር ጨርሻለሁ፤ ምንም እንኳን ሳልፈልገው ቢሆንም። ከጅምሩ እቅዴ ረጅም ጊዜ ለመቆየት ነበር የመጣሁት፤ የነበረውም ከባቢ ሁሉም ለሥራዬ ጥሩ ድጋፍ ያደርጉልኝ ነበር። በዛ ላይ ቡድኑ ተሰርቷል። ፍንጭ የሚያሳይ አንድ ቡድን ለመስራት ሞክረናል። ይህንን እዚህ ቆይቼ፤ ጊዜ አግኝቼ ማሰደግ ብችል ደስ ይለኝ ነበር ።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡