ፋሲል ከነማ ቀጣይ አሰልጣኙን ለመቅጠር ተቃርቧል

ፋሲል ከነማ ዛሬ በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ አዛምን 1-0 በዛብህ መለዮ ባስቆጠረው ብቸኛ ግብ ማሸነፉ ይታወቃል። ቡድኑ ዳሬሰላም ላይ በሚያደርገው የመልስ ጨዋታም በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ እንደማይመራ ተረጋግጧል።

ይህን ተከትሎ ቀጣዩን አሰልጣኝ ለመቅጠር ከቀናት በፊት የቅጥር ማስታወቂያ አውጥቶ የነበረው ፋሲል ከነማ ሥዩም ከበደን በዋና አሰልጣኝነት ለመቅጠር ምርጫው ማድረጉን የሚያሳዩ ፍንጮች ተገኝተዋል። አሰልጣኙ ዛሬ ፋሲል ከነማ ከአዛም ያደረገውን ጨዋታ በባህር ዳር ኢንተርናሽናል ስታድየም በመገኝት የተከታተሉ ሲሆን በቀጣይ ቀናትም የክለቡ ዋና አሰልጣኝ ሆነው የመሾማቸው ዜና ይፋ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ ከዚህ ቀደም ለአፍሪካ ዋንጫ ባለፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የሠውነት ቢሻው ምክትል በመሆን እንዲሁም የሴቶች ብሔራዊ ቡድን፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ አዲስ አበባ ከተማ፣ መከላከያ እና በአል-ሳቅር ክለቦች መስራታቸው የሚታወስ ነው።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡