“ጨዋታውን እንዳስብኩት አላገኝሁትም” የአዛም አሰልጣኝ ኤቲዬን ንዳዪቭጊጄ

ከ2019/20 ካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ቅድመ ማጣርያ ጨዋታዎች መካከል ዛሬ ባህር ዳር ላይ የተከናወነው የፋሲል ከነማ እና አዛም ጨዋታ በዐፄዎቹ 1-0 አሸናፊነት ከተጠናቀቀ በኋላ የእንግዳው ቡድን አሰልጣኝ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ስለ ጨዋታው

ጨዋታው በተወሰነ መልኩ ጥሩ ነው። ጥሩ ተጋጣሚ እና ጥሩ ጨዋታ አይቻለሁ። ለተጋጣሚያችን ክብር አለኝ፤ ጥሩ ኳስ ይጫወታሉ። ለማንኛውም አሸንፈዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ጨዋታውን ቢቆጣጠሩም ግብ ስላለማስቆጠራቸው

እግርኳስ ብልጫ መውሰድ ብቻ አይደለም፤ ግብ ማስቆጠርም አለብህ። መጀመሪያ እንዴት እንደሚጫወቱ ታጠናለህ። ከዛ አጨዋወትህን ትቀይራለህ፤ ለዛ ነበር ብልጫ የወሰድነው ።

ስለ ቡድናቸው አጨዋወት

ጨዋታውን እንዳስብኩት አላገኝሁትም። ማሸነፍ ነበር እቅዴ። በመጀመሪያው አጋማሽ አንድ ስህተት ሰራን፤ እሱም ወደ ግብነት ተቀየረ። ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ዕድሎች አግኝተን ነበር። ሆኖም መጠቀም አልቻልንም። ነገር ግን የአቅማችንን ሞክረናል።

የቀጣይ ጨዋታ እቅድ

በቀጣይ ጨዋታ የተሻለ ለመጫወት ነው እቅዳችን። ዛሬ በሁለተኛው አጋማሽ የሰራነውን ነገር ቀጣይ በመጀመሪያም በሁለተኛውም አጋማሽ ላይ ተጭነን ለመጫወት ነው እቅዳችን።

ስለ ስታዲየም ድባብ

ሀገሬ፣ ሩዋንዳ፣ ኪንሻሳ፣ ካምፓላ ላይ አይቻለሁ። ይህ ግን የተለየ ነው፤ ወድጄዋለሁ። ቆንጆ እግርኳስ ይገባቸዋል። ሜዳው ጥሩ ነው። የኛም ሜዳ እንደዚህ ነው። ሰዎቹም ጥሩ ናቸው። ጥሩ ማኅበረሰብ ነው የገጠመኝ፤ ወድጄዋለሁ።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡