ሉሲዎቹ ነገ ከኬንያ ጋር የወዳጅነት ጨዋታቸውን ያደርጋሉ

የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ለ2020 የቶኪዮ ኦሊምፒክ የሴቶች እግርኳስ አፍሪካ ዞን ሁለተኛ ዙር ማጣርያ ዝግጅት እንዲረዳው በነገው ዕለት ከኬንያ ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ያደርጋል።

የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ሠላም ዘርዓይ ለ23 ተጫዋቾች ጥሪ በማድረግ ዝግጅት ማድረግ ከጀመሩ ከሳምንት በላይ ያስቆጠሩ ሲሆን በትላንትናው ዕለት ወደ ኬንያ ከማምራታቸው ቀደም ብሎ በአዳማ ዝግጅት ሲያከናውኑ ቆይተዋል።

በቅድሚያ ከተመረጡ ከ23 ተጫዋቾች መካከል በጉዳት ምክንያት ከስብስቡ ውጪ የሆነችው ግብ ጠባቂዋ ማርታ በቀለን ተክታ የነበረችው ከምባቴ ከተሌ በፓስፖርት ምክንያት ወደ ኬንያ ካልተጓዙት መካከል ስትገኝ ሴናፍ ዋቁማ ከታዳጊ ቡድን ጋር በተደረገ የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ላይ በመጎዳቷ፣ ሎዛ አበራ ደግሞ የዝውውር ጉዳይ ለማጠናቀቅ ወደ ማልታ በማቅናቷ ከወዳጅነት ጨዋታው ጉዞ ውጪ የሆኑ ሌሎች ተጫዋቾች ናቸው።

ሉሲዎቹ ትናንት ወደ ኬንያ ከተጓዙ በኋላ ዛሬ ጨዋታው በሚደረግበት ማቻኮስ ልምምዳቸውን ያከናወኑ ሲሆን የቡድኑ አሰልጣኝ ሠላም ዘርዓይ ለኬንያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ሚዲያ በሰጠችው አስተያየት ” እዚህ የተገኘነው ለማሸነፍ ወይም ለመሸነፍ አይደለም። ለካሜሩኑ ጨዋታ የሚጠቅመንን አንዳች ነገር ለመማር ነው። ከጨዋታው ጥሩ ነገር እንደምናገኝም ተስፋ አደርጋለሁ። ” ብላለች።

የኬንያው አሰልጣኝ ዴቪድ ኦውማ በበኩሉ ጠንካራ ልምምድ ስንሰራ እንደመቆየታችን ተጫዋቾቻችን ምን ያህል እንደሚያበረክቱ የምንመለከትበት ነው። ኢትዮጵያ ጥሩ ቡድን አላት። በሴካፋ ውድድር ላይም አሸንፈውናል። ስለዚህ ጨዋታው ጠንካራ ይሆናል፤ ከጨዋታው ጥሩ ውጤት ይዘን እንምንወጣ እርግጠኛ ነኝ።” ብለዋል።

ከነጥብ ጨዋታዎች በፊት በወዳጅነት ጨዋታዎች እጥረት የምትቸገረው ኢትዮጵያ ከካሜሩን ጋር ነሀሴ 19 ለምታደርገው የኦሊምፒክ ማጣርያ የመጀመርያ ጨዋታ ዝግጅት የኬንያው የወዳጅነት ጨዋታ እንደሚጠቅማት ይጠበቃል።

የሁለቱ ቡድኖች የወዳጅነት ጨዋታ ነገ (ቅዳሜ) ማቻኮስ በሚገኘው ኬንያታ ስታዲየም 9:00 ላይ ይካሄዳል። ከጨዋታው በኋላም ሉሲዎቹ በባህር ዳር ዝግጅታቸውን የሚቀጥሉ ይሆናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡