ሲዳማ ቡና ተከላካይ ሲያስፈርም የግብ ጠባቂውንም ውል አራዝሟል

ሲዳማ ቡና ተከላካዩ ጊት ጋትኮችን አዲስ ፈራሚ አድርጎ ወደ ክለቡ ሲቀላቅል የግብ ጠባቂው ፍቅሩ ወዴሳን ውል ለተጨማሪ ዓመት አራዝሟል።

ከጋምቤላ የተገኘው ቁመተ ረጅሙ ጊት ጋትኮች በአዲስ አበባ ከተማ ያለፉትን ሦስት ዓመታት ቆይታ ያደረገ ሲሆን ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ሲያሳይ ቆይቷል። የሁለት ዓመት የውል ስምምነት ሲዳማን የተቀላቀለው ጊት ክለቡን የለቀቀው ዳግም ንጉሴን ቦታ እንደሚሸፍን ይጠበቃል።

ፍቅሩ ወዴሳ በክለቡ ለአንድ ተጨማሪ ዓመት ውሉን ያራዘመ ተጫዋች ሆኗል። ደቡብ ፖሊስን ለቆ ያለፉትን አራት ዓመታት የሲዳማ ቡናን ግብ ሲጠብቅ የነበረው ፍቅሩ ከመሳይ አያኖ ጋር ለዳግም የቋሚነት ዕድል ለመፎካከር ወስኖ በክለቡ ቆይታውን አረጋግጧል።

በተያያዘ የክለቡ ዜና በቅርቡ ውላቸው ተራዝሞላቸው የነበሩት ሐብታሙ ገዛኸኝ እና ፈቱዲን ጀማል እንዲሁም አዲስ ፈራሚዎቹ ፍቅረየሱስ ተ/ብርሃን እና ብርሀኑ አሻሞ በቅርቡ ከደሞዝ ጣሪያ ውሳኔ ጋር በተገናኘ ሲዳማ ቡና ህጉን ተግባራዊ ለማድረግ በማሰቡ ምክንያት መስማማት ባለመቻላቸው ወደ ሌላ ክለብ ሊያመሩ መቃረባቸውን ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡