ወልዋሎዎች የቅድመ ውድድር ዝግጅትታቸውን ጀምረዋል

በዝውውሩ በስፋት በመሳተፍ አስራ አራት ተጫዋቾች ያስፈረሙት ወልዋሎዎች በትናንትናው ዕለት የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን ጀምረዋል።

በቀጣይ ቀናት ለቅድመ ውድድር ዝግጅት እና ጨዋታዎች ወደ ዱባይ ያቀናሉ ተብለው የሚጠበቁት ቢጫ ለባሾቹ በቀን ሁለት ጊዜ ልምምድ በማድረግ ጠንካራ ዝግጅት እያደረጉ ሲሆን በቀጣይ ቀናትም አዲስ ፈራሚዎቹ ዓይናለም ኃይለ እና ጃፋር ደሊልን ወደ ቡድናቸው ይቀላቅላሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ወደ ወልዋሎ ከመጡበት ግዜ ጀምሮ ለታዳጊዎች ዕድል እየሰጡ የሚገኙት አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ በዓዲግራት የተለያዩ ፕሮጀክቶች አድገው ባለፈው ዓመት ከሶሎዳ ዓድዋ ጋር ቆይታ ላደረጉት ጠዓመ ወልደኪሮስ እና ክብሮም ዘርዑ የሙከራ ዕድል ሲሰጡ በቀጣይ ሁለት ቀናትም ሃያ የሚደርሱ ታዳጊዎችን ለመመልከት ዕድሎች እንዳመቻቹ ለማወቅ ተችሏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ