“መንግስት ትዕግስት እንድናደርግ ገልጾልናል” አቶ አብነት ገብረ መስቀል

ኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ በዛሬው ዕለት በሸራተን ሆቴል በወቅታዊ ጉዳይ ዙርያ በጋራ በመሆን ያዘጋጁት ጋዜጣዊ መግለጫ ሳይካሄድ ቀርቷል።

በአጭር ንግግር በተጠናቀቀው በዚህ ጋዜጣዊ መግለጫ አቶ አብነት ገብረ መስቀል (የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ሰብሳቢ)፣ መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ (የኢትዮጵያ ቡና ክለብ ሰብሳቢ) እና ኃይለየሱስ ፍስሀ (ኢንጅነር) የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝደንት፣ ጥናት አቅራቢው አቶ ገዛኸኝ ወልዴ እና ሌሎች የሁለቱ ክለቦች ተወካዮች እና ጥሪ የተደረገላቸው የሚዲያ አካላት በቦታው ተገኝተዋል።

በመግለጫው ንግግር ያደረጉት አቶ አብነት ገብረመስቀል መግለጫው ስላልተካሄደበት ምክንያት በዚህ መልኩ ገለፃ አድርገዋል።

” የተከበራቹ የሚዲያ አባላት እንደምታውቁት ትኩረት ሰጥተን መግለጫ ለመስጠት የፈለግነው ሰሞኑን የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ዙርያ በተነሱት ጉዳዮች እኛም ሁላችንም ለመወያየት እና በእግርኳሱ ህግ ወጥ ነገሮች እየተበራከቱ፣ አንድነታችን እና የስፖርት መንፈስ የሚረብሹ ነገሮች እየመጡ በመሆኑ ያንን ለመቋቋም ያለንን አቋም ለመግለፅ ነበር። ሆኖም ከሁለት ሰዓት በፊት ከመንግስት አካል ይህ ስብሰባ እንዲዘገይ እና ትዕግስት እንድናደርግ ተገልፆልናል። መንግስት በአስቸኳይ በጉዳዩ ላይ ትኩረት ሰጥቶ በአጭር ቀን ውስጥ ጠቅለል ያለ ስብሰባ በመጥራት ችግሩን እንደሚመረምርም ገልጿል። በመሆኑም ፊፋ ሆነ ካፍ ባስቀመጠው ደንብ መሠረት አንድነታችን፣ የሀገር ሠላም፣ ወንድማማችነታችን ተጠብቆ ሳንለያይ ውድድሩ ሕግ እና ደንቡን ጠብቆ እንዲካሄድ መንግስት የሚያደርገውን ጥረት እንጠብቃለን።”

በዚህ መሠረት የታሰበው ጋዜጣዊ መግለጫ ሳይካሄድ ተጠናቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ